በመኮንን ተሾመ (ከዩጋንዳ ፣ ካምፓላ ከተማ)
እ.አ.አ. ከመጋቢት-ግንቦት 2024 ዓ.ም. በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተራዘመና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ይጠበቃል ሲል የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና አፕሊኬሽንስ ማዕከል (ICPAC) አስታወቀ።
በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት እውቅና ያለው የአየር ንብረት ማዕከል ICPAC ለ11 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ትንበያና ተያያዥ አገልግሎቶች ይሰጣል።
እንደ ማዕከሉ ከሆነ፣ ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ሁኔታዎች በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በሶማሊያ፣ በብሩንዲ እና በታንዛኒያ የአየር ሁኔታዎችን ሊወስን ይችላል። ይህንን ወቅታዊ ትንበያ ግምት ውስጥ በማስገባት ማዕከሉ አሁን የተጠናከረ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲደረጉ ጠይቋል።
ይህ የተገለፀዉ በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ “የቅድመ ማስጠንቀቂያ ለቅድመ መከላከል እርምጃ” በሚል መሪ ቃል ከፌብሩዋሪ 20 – 21 ፣ 2024 በተካሄደው የICPAC 66ኛው የታላቁ አፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ መድረክ (GHACOF 66) ሲሆን ትንበያዉም የሚሸፍነዉ እ.አ.አ. ከመጋቢት እስከ ግንቦት 2024 ያለዉን ጊዜ ነዉ።
የንዑስ አህጉራዊዉን የአየር ሁኔታ ትንበያ ያቀረቡት የአይ.ሲፒ.ኤ.ሲ (ICPAC) ተመራማሪ እና የአየር ንብረት ሞዴሊንግ ኤክስፐርት ዶ/ር ሁሴን ሰኢድ እንድሪስ እንዳሉት ከሆነ የሙቀት መጠኑ በአጠቃላይ በክልሉ ከአማካይ በላይ እንደሚሆን እና በተለይ በክልሉ ሰሜናዊ ክፍሎች ደግሞ የሙቀት መጠኑ ይበልጥ እንደሚጠናከር ይጠበቃል።
በማዕከላዊ ኬንያ ባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ እና በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አንዳንድ ክፍሎች ይህ ሁኔታ ዘግይቶ ሊከሰት ይችላል ሲሉም ዶክተር ሁሴን አክለዉ ተናግረዋል።
በአብዛኛዎቹ የታላቁ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ከወትሮው የበለጠ እርጥበታማ ሁኔታዎች እንደሚጠበቁም አስታዉቀዋል። በንፅፅር፣ በምስራቅ ታንዛኒያ አንዳንድ ክፍሎች እና በምዕራብ ደቡብ ሱዳን ባሉ አከባቢዎች ላይ ደረቃማ አየር ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።
የእንግሊዝ የሚቲዎሮሎጂ ቢሮ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ስቴፋን ሊነስ
የእንግሊዝ የሚቲዎሮሎጂ ቢሮ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ስቴፋን በፎረሙ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ሰለሚኖረዉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ስቴፋን እነደሚሉት በውሃ አካላት ላይ የሚፈጠሩ የአየር ሁኔታ ተለዋዋጭነት (MJO) እና የከባቢ አየር ሂደቶች በአጭር ጊዜ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ሊያስከትሉ ይችላል ብለዋል።
“ባለዉ ትንበያ መሰረት ከመደበኛው በላይ የሆነዉ ደረቃማ ሁኔታ ደግሞ ሪከርድ የሚሰብር ዝናብ ሊያመጣ ይችላል” ዶ/ር ስቴፋን ብለዋል።
በዚህ ምክንያት ከብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ እና ከንዑስ አህጉራዊዉ ተቋም ICPAC ጋር በመተባበር ትንበያዎችን በወቅቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ባለሞያዉ ይህም ሰዎች ለሚኖሩ ሁኔታዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ዶ/ር ስቴፋን እንዳመለከቱት ሁለት የዝናብ ወቅቶች በፍፁም አንድ አይነት ሊሆኑ አይችሉም – በዝናብ አጠቃላይ መጠን፣ ጥንካሬ እና ቦታ ይለያያሉ።
“በአንዳንድ የምስራቅ አፍሪካ ቦታዎች ሰሜናዊው ሞንሱን ከሰኔ እስከ መስከረም፣ እና ከጥቅምት እስከ ታህሣሥ አጭር ዝናብ የሚያስከትል ሲሆን፣ የደቡባዊ ኤልኒኖ ንቅናቄ (ENSO) እና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሚከሰቱ ለዉጦች ደግሞ ለወቅታዊ ዝናብ መጨመር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ይህ ሁኔታ ከዓመት ወደ ዓመት ተለዋዋጭነትም የታይበታል” ሲሉም አብራርቷል።
ብዙ ጊዜ ያልተጠበቁ ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ለዉጦች የሚያስከትሉት የደቡባዊ ኤልኒኖ ንቅናቄ ፣ የውቅያኖስ ወለል መሞቅ ወይም በምስራቅ እና መካከለኛው የፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ከአማካኝ በላይ የባህር ወለል የሙቀት መጠን ሲከሰት እና በህንድ ውቅያኖስ የሚከሰቱ ለዉጦች ሲሆኑ እንዲሁም በሁለት አካባቢዎች ወይም ምሰሶዎች መካከል ያለው የባህር ወለል የሙቀት ልዩነት መሆናቸዉን ጠቁመዋል።
ዶ/ር ስቴፋን አክለዉም “የተራዘሙ የዝናብ ትንበያዎችን በባህላዊ መንገድ በትክክል ለመተንበይ በጣም ከባድ ነው። የICPAC የትንበያ ዘዴ ከነዚህ ከተለመዱ መለኪያዎች ባሻገርም ወቅታዊ ትንበያዎችን ለማድረግ በጣም ጥሩ የሆኑ ዘመናዊ የትንበያ ሞዴሎችን ይጠቀማል።” ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ስቴፋን ትልቅ ፈተና የሆነው እነዚህ የታወቁ አየር ፀባይ ለዉጥ መለኪያዎች ከዝናብ ጋር ያላቸዉ ተፅዕኖ በትክክል አለመታወቁ ነው። ስለዚህ፣ ምንም እንኳን ENSO በረጅም ዝናብ ውስጥ ሊቆይ የሚችል ቢሆንም፣ ሁኔታዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ግን በርግጠኝነት መናገር አይቻልም ሲሉ ዶ/ር ስቴፋን ለአፍሪካ ዲሚስቲፊየር ተናግረዋል።
“በ 2023 የአለም ሙቀት መዛግብት ታይቷል፣ እና የሙቀት መጠኑ በ2024 በተመሳሳይ የሚቀጥል ይሆናል አልፎ ተርፎም ከዚህ ሊበልጥ ይችላል” ሲሉም ተናግረዋል።
በሰዉ ሰራሽ የአየር ንብረት ለውጥና የኤልኒኖ ክስተት ምክንያት በታኅሣሥ ወር የሚኖረዉ የሙቀት መጠን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የከባቢ አየር ሙቀቱን ይበልጥ ሊያባብሰዉ እንደሚችልመ ዶ/ር ስቴፋን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያ ዶ/ር አሳምነው ተሾመ በበኩላቸው፣ ከየካቲት እስከ ግንቦት የሚቆየው የኢትዮጵያ የ“በልግ ወቅት” ለደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ዋና የዝናብ ወቅትም ነው ይላሉ። ይህ የዝናብ ወቅትም ለሰሜን ምስራቅ፣ ለምስራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡባዊው የአገሪቱ ክፍሎች ድግሞ ዋና የዝናብ ወቅት ባይሆንም በጣም ተለዋዋጭ እና ብዙም ሊገመት በማይችል የዝናብ ሊያሳይ ይችላል ይላሉ።
እ.አ.አ. በ2024 የበልግ ወቅት ላይ ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ሊከሰት ይችላል፣ ከመደበኛ በላይ እና ከመደበኛው የተቀራረበ የሙቀት መጠን በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚጠበቅ የተናገሩት ዶ/ር አሳምነው ለንዑስ አህጉራዊዉ ትንበያ ተጨማሪ ሀሳብ ሰተዋል ።
የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት አስፈላጊነት አሉታዊ ተፅእኖዎችን ለመቋቋም
የግብርና ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ” የ2024 የሴክተሮች የበልግ የአየር ፀባል ተጽእኖ እቅድ እና ተግባራት” ላይ ተወያይተዉ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመዉ ለዚህም የአደጋ መከላከል ስራዎች እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል። በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የ”በልግ” ወቅት ከየካቲት እስከ ግንቦት ያለውን የዝናብ ወቅት ነዉ የሚያመለክተዉ።
እንደ ሴክተር መስሪያ ቤቶቹ አተያይ የወቅቱ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ጎርፍ፣ የተፈናቃዮች መበራከት፣ የሰብል ተባይ እና የሽታ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ያልተጠበቀ ዝናብ እና የሰብል ውድመት ሊያስከትል እንደሚችል አሳስበዋል። እንዲሁም በምስራቃዊው የአፍሪካ ቀንድ ደግሞ የበረሃ አንበጣዎች ፣ ተላላፊ በሽታዎች (ወባና ኮሌራ) እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሊያስከትል ይችላል።
ስለዚህ ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይመክራል፣ይህም ወቅታዊ ትንበያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና ምላሽ እቅዶችን ማጠናከር፣ ይህም በጤና ስርዓቱ ውስጥ ቅድሚያ በመስጠት እና ግንዛቤን በመፍጠር እንዲሁም የተግባር ስራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል።
በተጨማሪም የወባና ሌሎች ከአየር ንብረት ጋር በተያያዙ ህመሞች በተከሰተባቸው አካባቢዎች የክትትል ስራን ማሳደግ እና ከትራንስፖርት ጋር በተያያዙ የጂኦግራፊያዊ ተደራሽነት ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ የጤና አገልግሎት ቁሳቁሶችን በወቅቱ ማቅረብ እና የጋራ እቅድ አዉጥቶ ተግባራትን ማከናወንና መከታተል እንደሚገባ ተጠቁሟል ።
የ ICPAC ዳይሬክተር ጉሌይድ አርታን በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ ክልል የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የቅድመ ማስጠንቀቂያና እርምጃ እንዲሁም ወቅታዊ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እንደሚያስፈልግ አስምረዉበታል።
በተጨማሪም በአካባቢው ዘላቂ ልማት ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአየር ንብረት ትንበያ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደዘገበው ባለፉት ሁለት ዓመታት በኤልኒኖ ምክንያት የጣለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በቡሩንዲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ህይወት ጠፍቷ፣ ሰዎች ከኑሮአቸዉ ተፈናቅለዋል እንዲሁም ከፍተኛ ንብረትም ወድሟል።
በመስከረም እና በታህሳስ 2023 አጋማሽ መካከልም በነበረዉ ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ በምስራቅ አፍሪካ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሷል፣ እንዲሁም በኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ኢትዮጵያ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ይህ ታሪክ የተዘጋጀው በInfoNile የአርትኦት ድጋፍ ነው።