በውሀ የበለጸገችዋ ኢትዮጵያ በዝቅተኛ መስኖ ልማት የምግብ ዋስትናዋ ስጋት ገጥሞታል

በውሀ የበለጸገችዋ ኢትዮጵያ በዝቅተኛ መስኖ ልማት የምግብ ዋስትናዋ ስጋት ገጥሞታል

በቴዎድሮስ ካሳ

አብዲ አሰፋ በኢትዮጵያ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኝ ገበሬ ሲኾን፤ በአመት ከነጭ ሽንኩርት ምርቱ በአመት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ያገኛል፡፡ በሶስት ሔክታር የእርሻ መሬቱ ላይ ከ200 በላይ ወጣቶችን ቀጥሮ ያሰራል፡፡ በተለይ በዝናብ አጠር ወቅት መስኖን በመጠቀም እርሻውን ያለማል፡፡ ለእርሻው የሚሆን ውሀን ለማውጣትም ጄኔሬተርን ይጠቀማል፡፡ 

“ውሀ ለእኛ ሁሉም ነገር ምንጭ ነው፡፡ ይሁንና ይህ በምድር ላይ ጠቃሚ የሆነው ሐብት በፍላጎትና አቅርቦት መካከል አለመመጣጠን የተነሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው” ይላል፡፡ ውሀን በዘላቂነት ጠብቆ መጠቀም እንዲቻል ደግሞ የውሀ ሐብቶችን ለመጠበቅ የሚያስችሉ አስፈላጊ የመፍትሔ አማራጮችን አለማችን መፈለግ እንዳለባት ያሳስባል፡፡ 

ከግብርና የሚያገኘው ገቢ እርሱን በየጊዜው እየናረ የሚገኘውን የነዳጅ ዋጋን ለመቋቋም ቢያስችለውም በክልሉ የሚገኙ ብዙ ገበሬዎችን ደግሞ ከመስኖ እርሻ ስራቸው አግዷቸዋል፡፡ ይሁንና መስኖ አሁንም ድረስ ያለውን የውሀ እጥረትንና የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመቋቋም የሚስችል ዋንኛ መንገድ ነው፡፡ 

እንደ አብዲ አሰፋ ገለጻ፤ አሁን ላይ ግብርና አዋጪና ወጣቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን እየሳበ የመጣ ዘርፍ በመሆኑ ብዙ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ዘመናዊ የመስኖ ዘዴን በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡ 

Farmer Abdi Assefa 2 scaled
አብዲ አሰፋ ገበሬ

በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የአፈር ምርታማነት እየቀነሰ በመምጣቱ ኑሮን ለማሸነፍ፤ ያለውን ውስን የሚለማ መሬትና የውሀ ሀብቶችን በአግባቡና መጠቀም ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነም ይናገራል፡፡ 

ብዙ ገበሬዎች ደግሞ እንደ አብዲ አሰፋ የገቢ አቅም ያላቸው አይደሉም፡፡ 

እንየው ኃይሌ በአማራ ብሔራዊ ክልል ለእርሻ ለም በሆነው ሰሜን ጎንደር ዞን ገበሬ ሲኾን፤ የነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ሩዝ፣ ጤፍና ስንዴ እንዲሁም ሌሎች ምርቶቹን የሚያለማበትን ውሀ ማግኘት ተቸግሯል፡፡

“ባለፈው አመት ውሀ መሳቢያ ጄነሬተር ገዝቼ ነበር፡፡ ይሁንና የነዳጅ ዋጋ እጅግ እየናረ በመሆኑ ገዝቼ መጠቀም አልቻልኩም” ይላል፡፡

ምንም እንኳን በአካባቢው ለመስኖ ሰፊ የሆነ የውሀ ሐብት መኖሩን ቢረዳም፤ የመስ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙት ለጄኔሬተር ነዳጅ የመግዛት አቅም ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ 

Farmer Enyew Haile 2 1
እንየው ሀይሌ

እንደ እንየው ገለጻ፤ በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች በመስኖ ማልማት የሰብል ምርትንና ገቢን እንደሚያሳድግ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ተራራማ አካባቢ ይህንን ቴክኖሎጂ መጠቀም አሁንም ድረስ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡

ከሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ መሬት እምብዛም በመስኖ የለማ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ሀገሪቱ ከግብጽና ሱዳን ቀጥላ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡

እንዲሁም ያንብቡ; Burundi: Local irrigation, a substitute for skyrocketing prices of new watering supplies

በተፈጥሮ የታደለ ግን ብዙ የሚፈልግ 

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ስትሆን ( ህዝቧወደ 120 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል) ያልተነካውን በመስኖ የመልማት አቅሟን በመጠቀም በምግብ ራሷን በመቻል የማደግ ፍላጎት አላት፡፡

ይሁንና ሀገሪቱ ተከታታይ ለሆነ ድርቅ እና የውሀ እጥረት የተጋለጠች ናት፡፡ ይህች የአፍሪካ ቀንድ ሀገር፤ አባይን ጨምሮ የብዙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መገኛ ናት፡፡ ታዲያ ይህ ወንዝ በከፍተኛ ሁኔታ ወቅት የሚጠብቅ ወንዝ ሲኾን፤ 70 በመቶ ያህል ውሃ የሚፈሰው ከሐምሌ እስከ መስከረም ወር ድረስ ነው፡፡ ዋንኛ ገባር ወንዞቹም ተከዜ እና ባሮ አኮቦ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ በወቅታዊነታቸው የሚታወቁ መሆናቸውን የአባይ ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ የመረጃ ቋት እና ዝርዝር መረጃ (WRM 2020-04) ያመለክታል፡፡

ሀገሪቱ ባለፉት አመታት ባለ ሁለት አሃዝ ምጣኔ ሀብት እድገት ብታስመዘግብም፤ አሁንም ድረስ ዝናብን በመጠቀም የማምረት ልማድ ጥገኛ ናት፡፡ ዝናብ እየጠበቁ በአመት አንድ ጊዜ ማረስ ደግሞ ለሰፊው ህዝቦቿ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡

“በጣም ሰፊ የሆነ የተፈጥሮ ሐብት፣ ምቹ የአየር ንብረት ለም መሬት እና ሰፊ የውሀ ሐብቶች እንዲሁም የሰው ሐይል ነው ያለን፡፡ እነዚህን ያልተጠቀምንባቸው ሐብቶችን በማቀናጀት ምርታችንን መጨመር አለብን፡፡ በምግብ እና መሰረታዊ ሸቀጦች ራስን የመቻል ጉዞው የምርታማነት ባህላችንን በማስፋፋት መታገዝ ይኖርበታል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ትዊተራቸው ላይ ሐሳባቸውን ገልጸው ነበር፡፡ 

በኢትዮጵያ የስራ አጥ ቁጥር በየአመቱ ቢጨምርም የግብርናው ዘርፍ በሀገሪቱ ዋንኛ የስራ ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን የማዕከላዊ ስታስቲክ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡

ይሁንና ለእርሻ የሚሆን ለም መሬት መራቆት እና ለእርሻ የሚሆን መሬት የማዘጋጀት ተግባር የደን መመንጠር በፍጥነት እንዲጨምር አድርጓል፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ከ70 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የሚለማ መሬት ያላት ቢሆንም፤12 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ ነው የለማው፡፡

የአለምአቀፉ የውሀ ማኔጅመንት ማዕከል በሳተላይት የተደገፈ መረጃ ላይ እንደሚገምተው በ2015 በናይል ተፋሰስ አጠቃላይ በመስኖ ከሚለማው መሬት በኢትዮጵያ በኩል የለማው 489,000 ሔክታር ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ አመታዊ አማካይ የመስኖ እድገት መጠን ከ1989 እስከ 2018 ባሉት አመታት 35.01 በመቶ የነበረ ሲኾን፤ ይህ መጠን ከአማካይ በታች ቢሆንም እንኳ የሱዳን፣ ግብጽ፣ ኬንያ እና ርዋንዳ አንድ ላይ ተደምሮ እንኳ የተሻለ ነበር፡፡

የአባይ ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ የማመሳከሪያ የመረጃ ቋት እና ማብራሪያ ሪፖርት (WRM-2020-04) በኢትዮጵያ በርካታ አሰራሮች አጥጋቢ ባልሆነ የውሀ አጠቃቀም እንደሚገለጹ አመልክቷል፡፡ ይህም ደግሞ የሚጀምረው ከመጠን በላይ የሆነ ውሀ ወደ ውሀ ማስተላለፊያ ከሚደርሱበት ቦታ ነው፡፡ 

ይህ ከመጠን በላይ የሆነ ውሀን አቅጣጫ ማስቀየስ ወይም መሳብ የሚመነጨው ከውሀ አጠቃቀም አቅም ማነስ እና ውሀ ልኬት ወይም መቆጣጠሪያ መገልገያዎች እጥረት የተነሳ ነው፡፡

የግብርና ሆርቲካቸር ልማትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት አብደላ ነጋሽ በበኩላቸው የውሀ አጠቃቀምና የሀገሪቷን ሰፊ የመስኖ መሬት አቅም በተመለከተ ተጨባጭ የሆነ ልዩነት እንዳለ ይናገራሉ፡፡

“የኢትዮጵያ መንግስት ከምንግዜውም በላይ እያደገ ለመጣው የህዝብ ብዛት ዘላቂ የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ደህነትን ለማረጋገጥ ውጤታማ አግሮኖሚክ ስራዎች ለማረጋገጥ እየሰራ ነው፡፡ ይሁንና ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር የመስኖ አቅም አሁንም ቢሆን በአነስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው” ብለዋል፡፡

DSC 0252 2
በመስኖ በመጠቀም የሚበቅል እርሻ

ኃላፊው አክለውም፤ ከ12 በላይ የወንዝ ተፋሰሶች በላይ ያላት ኢትዮጵያ “ይህንን አቅም ለማሳደግ እና ለመጠቀም ትላልቅ ኢንቨስትንቶችና ካፒታል ያስፈልጋታል” በማለት ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ከያዘችው የ10 አመት የልማት አቅጣጫ እቅድ ግብርና ዋንኛው ዘርፍ ነው፡፡

ደመናን ማዝነብ፣ ከጥልቅ ጉድጓድ ውሃን የማውጣት ስራ እና የዝናብ ውሀን ለረጅም ጊዜ እንዲጠቅም ማጠራቀምን የመሳሰሉ ስራዎች የኢትዮጵያ መንግስት መስኖ ልማት እጥረትን ለማቃለል ከያዛቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መከከል እንደሚጠቀሱም አስታውቀዋል፡፡

የአባይ ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ መረጃ በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ የመስኖ እርሻን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ የምታደርጋው ጥረቶች አዝጋሚ መሆናቸውን ነው የጠቀሰው፡፡

በአባይ ወንዝ ተጋሪ ሀገሮች መካል እያደገ የመጣውን የውሀ ፍላጎት ለማሟላት እና አሁን ያለውንና ወደፊት ሊከሰት የሚችልን የውሀ ችግር ለማስቀረት በማሰብ በ2015 ላይ የአባይ ተፋሰስ ኢንሺዬቲቭ ጽህፈት ቤት የውሀ ሐብቶች ትንተና ጥናት አካሒዶ ነበር፡፡ 

 በተመሳሳይ ሁኔታም ድርቅን ለሚቋቋሙ ሰብሎች ቅድሚያ መስጠት እና የተፋሰስ ውሀ አቅርቦት አስተዳደርን ማሳደግ የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን በመፍትሔነት ጠቁሞ ነበር፡፡ 

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአባይ ተፋሰስ ቀጣይነት ያለው የውሀ እጥረት በየአመቱ ከ5-29 ማግኒቲውድ እንደሚከሰት አመልክቷል፡፡ 

የጥናቱ ሪፖርት አክሎም “ይህ የሚያስገነዝበው የተሻሻሉ አሰራሮችንና ተክኖሎጂዎችን በመጠቀም የውሀ አጠባበቅንና የውሀ አጠቃቀም ብቃትን ለማሳደግ አስቸኳይና ቀጣይነት ያለው ያላቸው ጥረቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው” ሲል በአጽንኦት አሳስቧል፡፡ 

የግብርና ምርትንና የእርሻ ገቢን ከማሳደግ ባሻገር፤ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ የውሀ አጠባበቅንና በቂ ውሀን አጠቃቀምን ማስተዋወቅ በቀጣይ ሊከሰት የሚችልን የውሀ ችግር ለመከላከል ተጨባጭ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ይህ ዘገባ የተጠናከረው በኢንፎናይል እና ሚዲያ ኢን ኮኦርፖሬሽን ኤንድ ትራንዚሽን (MiCT)  ከአባይ ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ (NBI) ጋር በመተባበር እና ከጀርመኑ  እና በአውሮፓ ህብረት እና ከጀርመን መንግስት ን በመወከል ከ Deeutche Gesellschaft fur International  Zusammenarbeit (GIZ) GmbH በተገኘ ድጋፍ ነው፡፡

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts