በጄራልድ ቴንይዋ እና ኢስኤል ካሱሃ
በምዕራባዊ ዩጋንዳ በኪኩቤ ወረዳ ወደሚገኘው ወደ ቡጎማ ደን ለመግባት ዳገታማውን መንገድ ስንያያዘው የወጣችው ጸሐይ አስጎብኚያችንን በላብ አጥምቃው ነበር፡፡ ከጫካው እምብርት ስንደርስ ስንገባ ቀኑ ገና ልጅ ነበር፡፡ ወፎቹ ህብረ ዜማቸውን ሲያሰሙ የቡጎማ ደን እኛን እያወራን እንደሆነ አስጎብኛችን ነገረን፡፡
የደኑ የእግር መንገድ የሆይማ ስኳር አምራች ኩባንያ የሸንኮራ አገዳ ለመትከል እየመነጠረ ወዳለው ወደ እሾኻማው የደኑ ክፍል እንደሚያደርሰን ነበር ተስፋ ያደረግነው፡፡
ላለፉት ሶስት ወራት የሆይማ ስኳር ፋብሪካ ለሸንኮራ አገዳ ተክል ማስፋፊያ በማለት ቡጎማን እያወደመ ቆይቷል፡፡
የእኛ የእግር ጉዞ ታዲያ አስፈሪ አልነበረም፡፡ ወደ ቡጎማ የሚወስደንን ቀጭን መንገድ የዘጉትን ተፋሰሶችንና የወዳደቁ ዛፎችን በጀግንነት አልፈናል፡፡ ከአንድ ሰአት በኋላም ወደ “ቀዩ መስመር” መቃረባችንን መንገድ ጠቋሚያችን ነገረን፡፡ ብዙም ሳይርቅ ሆይማ ስኳር ፋብሪካ የያዘው ግዛት ይጀምራል፡፡ በዚያም ሰዎች እንዳይገቡ ጠባቂ ወታደሮች ይገኛሉ፡፡ በህገ ወጥ የደን መንጣሪዎች የተተወ ክፍት ቦታ ደግሞ አለ፡፡ በዚህ ቦታ ሆነን ነው ድሮናችንን ለመልቀቅ የፈለግነው፡፡ የሆይማ ስኳር ፋብሪካን ጥፋቶች ማየት እንችላለን ብለን የገመትነው ከላይ በድሮን አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ በሁለት ጊዜ የአየር ላይ ቅኝት ድሮኗ የውቡን ደን ምስል ብቻ ነው ይዛ የተመለሰችው፡፡
የባዶነት ስሜት እንደተሰማን በፊታችን ገጽታ ላይ በግልጽ ይነበብ ነበር፡፡ ነገር ግን የአካባቢው ህብረተሰብ የውሀ፣ የእንጨት እና የእንጉዳይ ማግኛ ምንጫቸው የሆነው ቡጎማን ሊያጡ እንደሆነ የነገሩን ስጋታቸው እኛን ወደ እውነታው እንድንጓዝ ብርቱ አደረገን፡፡
ቀጣዩ መዳረሻችንም የሆነው የአካባቢው ነዋሪዎች የስብሰባ ጥሪ ያደረጉበት በኪቡቤ ወረዳ በካብዎያ ክፍለ ግዛት ንያሮንጎ ነበር፡፡
ዲስሬ ሙሬንዚ የቀበሌው ሊቀመንበር ሲሆን፤ የሆይማ ስኳር ፋብሪካ የቡጎማ ደንን ለምን እንደሚያጠፋ ምርመራ በማድረጉ በኖቬምበር 2020 በወታደሮች ተይዞ ከግማሽ ቀን እስር በኋላ ተለቋል፡፡ ወታደሮች ሆን ብለው ህገ ወጥ ደን መንጣሪ ነው ብለው እንዳሰሩት ይናገራል፡፡
ሙሬንዚ እንደሚናገረው፤ የጸጥታ አካላቱ የከሰል አክሳዮች እና ህገ ወጥ የደን መንጣሪዎችን መለየት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እሱ እንደ ማሲን፣ ማዩጌ፣ ልጋንጋ እና ቡክዌ ካሉ ሩቅ ቦታዎች የሚመጡ በመሆናቸው፡፡
“ለመሆኑ ወታደሮቹ ምንድናቸው?” ሲልም በመገረም ይጠይቃል፡፡
“ወታደሮቹ ማን ስለሆኑ ነው ለቡጎማ እንክብካቤ የሚያደርጉትን ነዋሪዎችን እንዳይገቡ ሊከለክሉ የሚችሉት? ግን ደግሞ ድጋፍ የሚያደርጉት ተፈጥሮን እያጠፉ ላሉት አካላት ነው”
በኪቡቤ ካሲታ የካብዎያ ክፍለ ግዛት አስተያየት የሚሰጡት ተናጋሪ ሮቪሳ ናማቶቭ በበኩላቸው፤ ቡጎማ ግብርናውን የሚያግዝ ዝናብን የሚለግስ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቡጎማ የእንጉዳይ ማፍሪያ ምንጭ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
“እኛ ከደኑ የምናገኘውን እንጉዳይ በመሸጥ በምናገኘው ገቢ ነው ልጆቻችን የምናስተምረው” በማለትም የደኑን ጥቅም አስረድተዋል፡፡
የቪዥን ቡድን አባላት በርቀት ላይ ሆነው ደግሞ በቡጎማ ደን ውስጥ በሆይማ ስኳር ፋብሪካ እንቅስቃሴ የተነሳ ሁለት ተራራማ ቦታዎች ምድረ-በዳ ሆነው አይተዋል፡፡
የቪዥን ቡድን አባላት የእጅ ካሜራ እና ድሮን በመጠቀም ውድመት የደረሰበትን የደኑን ክፍል ልክ ቀዶ ህክምና እንደሚሰሩ ሐኪሞች በፍጥነትና በጥንቃቄ በፎቶግራፍና በቪዲዮ ቀርጸዋል፡፡
የቡድኑ አባላትን ወደ ሩቶማ ኪባል እየመሩ የወሰዱት የአካባቢው ነዋሪዎች የሆይማ ስኳር ፋብሪካን የሚጠብቁ ወታደሮች ሩቅ እንዳልሆኑ ጠቁመው ነበር፡፡ ስለዚህ በወታደሮቹ ቁጥጥር ስር ላለመዋል በፍጥነት መስራት ነበረብን፡፡
ድሮናችን ወደ መሬት ተመልሳ እንደመጣችም ወዲያውኑ ዱላ የያዙ ሰዎች ዙሪያችን ወረሩን፡፡ በኋላ ላይ እንደተረዳነው የአካባቢው ሰዎች መሬት ለመውረር የመጣን መስለናቸው ነበር፡፡ አንድ በአካባቢው ጋዜጠኛ የሆነ አንድ ሰው ታዲያ ነጻነታችንን እንድናገኝ አደረገ፡፡ ጋዜጠኛው እኛ ደኑን ለመታደግ የሚታገሉ የአካባቢው ሰዎችን ለማገዝ እየሰራን እንደሆነ ነበር የነገራቸው፡፡ እነርሱም እውነታውን ሲረዱ በፍጥነት ነበር ከጠላትነት ወደ ወዳጅነት የተቀየሩት፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥም ባለ አራት ጎማ ሚስቲቡሺ ፔጆ መኪናችን የካብዎያ ተራራን እያጓራች ወጣች፡፡ 12፡00 ሰአት ሲሆንም የስኳር ፋብሪካው ጠባቂ ወታደሮች መኪና እየተከተለን እንደሆነ ሳናውቅ ሆይማን ለቀን ወጣን፡፡
“በጣም እድለኛ ናችሁ፡፡ ምክንያቱም ወታደሮቹ እናንተን ለመያዝ እየጠበቋችሁ ነበር” በማለት በክያንግዋሊ የኮሎሎ ቀበሌ ሊቀመንበር የሆነው ዴቪድ ቤይማትሲኮ ነገረን፡፡
“ምናልባት 10 ደቂቃ ብትዘገዩ ኖሮ በቃ በወታደሮቹ እጅ ገብታችሁ ነበር” አለን፡፡
ከሰል የሚያከስሉ ሰዎች ትልልቅ ዛፎችን ወደ ከሰልነት እንደሚቀይሯቸው ሁሉ፤ የሆይማ ስኳር ፋብሪካ ቡልዶዘሮች ደግሞ የደኑን መልክዐምድር እያረሱ ወደ ሸንኮራ አገዳ እርሻ ማስፋፊያ መሬትነት እየቀየሩት ነው፡፡
ይህ ደግሞ የሀገሪቱ የአካባቢ ሚኒስትር ቢያትሪስ ኤኒይዋር አካባቢውን ጎብኝተው ለነበሩ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ከሰጡት ገለጻ ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው፡፡ የቡጎማ ወሰንን በድጋሚ ከማጥናት ጋር በተያያዘ የሆይማ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ ሁሉም እንቅስቃሴዎች እንደተቋረጡ ነበር ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
“ካቢኔያችን የሆይማ ስኳር ፋብሪካን እንቅስቃሴን በማስቆም መንግስት የቡጎማ ወሰኖችን በድጋሜ እንዲጠና ያደርጋል” ነበር ያሉት፡፡
ኤኒይዋር ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ስምንት አምባሳደሮችን ያካተተውን የአውሮፓ ህብረት ልዑካንን ያናገሩት ኖቬምበር 2 ቀን 2020 ላይ ነበር፡፡
በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት መካከልም የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ዋና ኃላፊ አቲሊዮ ፓስፊክ፣ በዩንዳ የፈረንሳይ አምባሳደር ጁሊየስ አርማንድ አኒምቦሶ፣ የቤልጂየም አምባሳደር ቪስትራቴን ሩዲ፣ የጀርመን አምባሳደር ማቲያስ ሾር፣ የጣሊያን አምባሳደር ማሲሚላኖ ማዛንቲ፣ የስዊድን አምባሳደር ፐር ሊንድጋዴ፣ የዴንማርክ አምባሳደር ኒኮላጅ ኸበርግ ፒተርሰን እና የአውስትሊያ አምባሳደር ዶክተር ሮስዊታ ክሬምሰር ይገኙበታል፡፡
“በቡጎማ ደን የሸንኮራ አገዳ ሰብል ማልማት ምንም አይነት ትርጉም የሚሰጥ ነገር አይደለም” ያሉት የልዑኩ መሪ ፓሲፊክ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት እውነት መሆኑን ገልጸው ቡጎማ የተቃጠሉ ጋዞችን አምቆ በመያዝ ጥቅም እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡
በመሬት ሚንስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ኮሚሽነር የሆኑት ዊልያም ኦጋሮ፤ በዲሴምበር ወር መጀመሪያ ላይ የቡጎማ ወሰንን ለማስጠናት የደህንነት ሁኔታው ዋስትና እንደሌለው አስታውቀው ነበር፡፡ ጥናቱም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጃንዋሪ 14 ቀን 2021 ከተከናወነ በኋላ እንዲካሔድ መሻገሩን ነው ያታወቁት፡፡
ለሆይማ ስኳር የተፈቀዱ መሬቶች
ከብሔራዊ የአካባቢ አስተዳደር ባለስልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በምዕራባዊ ዩጋንዳ በክያንግዋሊ በኪኩቤ ወረዳ የሆይማ ስኳር ፋብሪካ 9.24 ስኩዌር ማይልስ ሳር የለበሰ መሬት ተሰጥቶታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለስኳር ፋብሪካው 1.2 ስኩዌር ማይልስ መሬት ላይ የከተማ ማዕከል እንዲያቋቁም፣ 1.97 ስኩዌር ማይልስ መሬት ደግሞ ለኢኮ ቱሪዝም፤ እንደዚሁም የቡጎማን 3.13 ስኩዌር ማይልስ መሬትን እንክብካቤ እንዲያደርግለት ፈቃድ ሰጥቶታል፡፡
በአካባቢ ጉዳይ አንድ ከፍተኛ የመንግስት አካል ደግሞ ሆይማ ስኳር ፋብሪካ 0.156 ሔክታር መሬትን የባህል መስክ ሆኖ እንዲጠብቀው እና 6.17 ስኩዌር ማይልስ መሬትን ደግሞ የተፈጥሮ ደን ሆኖ እንዲቀጥል ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ይህም ሆይማ የያዘው መሬት በአጠቃላይ ሲሰላ ወደ 21.54 ሔክታር መሬት (ወደ 22 ስኩዌር ማይልስ አካባቢ) ወይም ደግሞ 5,779 ሔክታር መሬት ማለት ነው፡፡
የሆይማ ስኳር ፋብሪካን “ለአካባቢ ደህንነት ተስማሚ” ሲሉ የሚገልጹት የፋብሪካው የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር ሼይላ ንዱሁኪሬ፤ “ከቡንዮሮ ኪንግደም ያገኘነው22 ስኩዌር ማይልስ መሬት የደኑ መሬት አይደለም፡፡ ኩባንያችን ራሱ አረንጓዴያማ በመሆኑ የደን ዛፍ የምንቆርጥበት ምንም ምክንያት የለንም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የቡጎማ ደን ውዝግብ መነሻ
ሆይማ ስኳር ለሚትድ 5,799 ሔክታር መሬትን በኦገስት 4 ቀን 2016 ከቡንዮሮ ኪታራ ኪንግደም በሊዝ መውሰዱ ተመልክቷል፡፡ ኦሙካማ ሶሎሞን ጋፋቡሳ ኢጉሩ ደግሞ የመሬቱን የባለቤትነት መብት ያገኘው ኦገስት 1 ቀን 2016 ነው፡፡
ምንም እንኳን ቡጎማ ለቡንዮሮ ንጉስ ከተመለሱ ንብረቶች ዝርዝር ውስጥ ባይታይም የዩጋንዳ የመሬት ኮሚሽን ግን መሬቱን ለቡንዮሮ-ኪታራ ንጉስ ለሰለሞን ጋፋቡሳ ኢጉሩ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
“እንግዲህ እኔ የማውቀው ነገር ቢኖር መሬቱ ለቡንዮሮ መንግስት አለመሆኑን ነው፡፡ እንዳሆነ ነው መሬቱ ከተመላሽ ንብረቶች መካከል አይደለም” ያለው የሲቪል ሶሳይቲ አክቲቪስቱ ጃክሰን ዋብዮና ነው፡፡
“ይህንን መሬት ንጉሱ ከየት ነው ያገኘው? የህዝብ መሬት ነው? ይህ መሬት በደን ልማት ስር በደንነት ተመዝግቦ እንዳለ ማን ያውቅ ነበርና ነው የባለቤትነት ሒደቱን ጨርሶ ከአራት ቀን በኋላ ለሆይማ ስኳር ፋብሪካ በሊዝ ያስተላለፈው?” በማለትም ዋብዮና ይጠይቃል፡፡
የቡጎማ ጸጋዎች
የቡጎማ ደን የአልበርት ሐይቅ የውሀ ማከማቻን ለመጠበቅ ተጠባባቂ ደን ሆኖ በ1932 የተመዘገበው ቡጎማ፤ 600 ቺምፓንዚዎች መኖሪያችን የሚሉት በሀሩራማ አካባቢ ዝናብ አምጪ ደን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቡጎማ በዩጋንዳ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ዝንጀሮዎች የሚገኙበት ነው፡፡ ከዘህ በተጨማሪም የዩጋንዳ በመጥፋት ላይ የሚገኙት የወፍ ዝርያዎች የሆኑት የናሃን ፍራንኮሊን እና የአፍሪካ ነጭ በቀቀኖች መኖሪያም ነው፡፡
ይህ ዘገባ የተጠናከረው ከኢንፎናይል (InfoNile) በተገኘ ድጋፍ ነው፡፡