የኮቪድ 19 ፈተና እና እድል – በአዲስ አበባ

የኮቪድ 19 ፈተና እና እድል – በአዲስ አበባ

በመኮንን ተሾመ እና ተስፋዬ አባተ

ኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ለማሳካት ለረጅም ጊዜ ስትታገል ቆይታለች፡፡ ነገር ግን የኮቪድ 19 የ133 አመት የእድሜ ባለጸጋ በሆነችው መዲና በአዲስ አበባ በንጽህና እና ጤና አጠባበቅ ዘርፉ ላይ ያተኮረው ኮቪድ 19 የሰዎችን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንዲተገበሩ የሚያስችል እድልን ፈጥሯል፡፡ 

በአዲስ አበባ የኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያ በሆነው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የጥበቃ ሰራተኛ የሆነው በቀለ ባልቻ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ለሆስፒታሉ እና ለአካባቢው ማህበረሰብ የውሀ አቅርቦት በጣም ጥሩ መሆኑን ይገልጻል፡፡

“የቧንቧ ውሀ የሚቋረጥ ከሆነ የከተማው ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን በመኪና ውሀ ያቀርባል፡፡ ከውሀ ጋር በተያያዘ ለሚገጥሙን ችግሮች በማንኛውም ሰአት ይደርስልናል፡፡”

“ከውሀ ጋር በተያያዘ ችግሮች የሚገጥሙ ከሆነ በነጻ የስልክ ጥሪ 804 የተሰኘ ቁጥር ስላለ መደወልና ሁኔታውን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ይቻላል፡፡ በኮቪድ 19 ወቅት የውሀ አገልግሎት አቅርቦትን በተመለከተ ጥሩ የሆኑ ምላሽ መሰጠታቸውን ተመልክቻለሁ” ብሏል፡፡

ምንም እንኳ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ፈተናዎች ቢኖሩም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን የመከላከል ተግባር የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች አቅምን ባገናዘበ ሁኔታ በስፋት እንዲኖር እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ የንጽህና አጠባበቅ ባህል እንዲዳብር አስችሏል፡፡ መሰል የንጽህና አጠባበቅ ተግባሮች ወደፊት ከንጽህና አጠባበቅ ጋር ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ጥሩ መሰረት ሊገነቡ ይችላሉ፡፡ 

ያልተመጣጠነ የውሀ ፍላጎት

ኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ንጹህ ውሀ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት እንደሚመክረው ከሆነ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ በህዝብ እና በግለሰብ የንግድ ህንጻዎች፣ እንዲሁም በሁሉም የህዝብ የጉዞ ማዕከሎች ፊት ለፊት ሰዎች በመደበኛነት እጃቸውን እንዲታጠቡ የሚያስችሉ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ መገልገያዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

ይሁንና ይህንን ወረርሽኙን በመከላከሉ ረገድ አንደኛው ፈተና ንጹህ ውሀ ማግኘት አለመቻል ሲሆን፤ በአብዛኞቹ የአለማችን ሀገሮች የውሀ ፍላጎትና አቅርቦት የማይመጣጠን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መዲና የሆነችው አዲስ አበባም ይህንን ችግር ትጋራለች፡፡ አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎቿ በቂ ውሀ የማግኘት ችግር አለባቸው፡፡ 

እንደ የአለም ባንክ ጥናት ከሆነ ከኢትዮጵያ 108,113,150 ከሚሆነው ህዝብ (በ2020 የተገመተ) 63 በመቶ ያህሉ ብቻ እና 24,463,423 ከሚሆነው የከተማ ህዝብ 4 በመቶ ያህሉ ብቻ (ከአጠቃላይ ህዝብ 21.3 በመቶ ያህሉ) ያልተበከለ ደህንነቱ የተጠበቀ ውሀን ያገኛሉ፡፡ 

በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ድርቆች፤ ጎርፎች፤ እና የሙቀት መጨመር የመሳሰሉ ገፊ ምክንያቶች የውሀ ሀብቶችን በአግባቡ ለማስተዳደር እና የውሀ አቅርቦት አገልግሎትን ለማረጋገጥ እንዳይቻል አድርገዋል፡፡

በአዲስ አበባ ውሀ አቅርቦትን በቧንቧ መስመሮች የሚያያቀርበው የህዝብ ተቋም የአዲስ አበባ ውሀ እና ፍሳሽ ባለስልጣን በየእለቱ 575,000 ኪውቢክ ሜትር የተጣራ ውሀን የሚያወጣ ሲሆን፤ ይህም ሁለት ሶስተኛ ለሚሆነው የከተማዋ ህዝብ ብቻ ነው ደህንቱ የተጠበቀ ውሀ ማቅረብ የሚችለው፡፡ ቀሪው አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የከተማዋ ነዋሪ የውሀ ፍላጎት ደግሞ ማሟላት አልተቻለም፡፡ እናም ውሀ ለማግኘት ያላቸው ብቸኛ አማራጭ እስከ 2ኪ.ሜ. በእግር መጓዝ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ የውሀ ምንጮች ደህንነታቸው ያልተጠበቁ ናቸው፡፡ 

ሰርክአለም ጌታቸው የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሆኑ፤ “በከተማዋ ያለው የውሀ ፍላጎትና አቅርቦት መካከል አለመጣጣም ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል” ይላሉ፡፡ 

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ በሆነው በዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የውሀ ንጽህና እና ጽዳት (ዎሽ) ኃላፊ ኪቲካ ጎዮል እንዳስታወቁት የውሀ ችግር መሰረታዊ ለእጅ መታጠቢያ የሚሆን የውሀ አቅርቦት ችግር ከመኖሪያ ቤት አልፎ በትምህርት ቤቶችና የሥራ ቦታዎች እና የጤና መጠበቂያ መገልገያዎች ላይም ጭምር ነው፡፡

“የገበያ እና የመጓጓዣ ቦታዎችን በመሳሰሉ ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎችም የውሀ አቅርቦት እጥረት አለ፡፡ በእነዚህ ቦታዎች መምህራን፣ ሐኪሞች፣ ነርሶች እና ሌሎች ሰራተኞች ከኮቪድ 19 እንዲጠበቁ ለማድረግ የእጅ ንጽህናን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው” ያሉ ሲሆን፤ “ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ (45 ሚሊዮን ህዝብ) እጁን በሳሙና የሚታጠብበት ቦታ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የለውም” ብለዋል፡፡ 

ዝናቡ አሰፋ፣ አለሙ እና ማይክል ዲዮሃ በአዲስ አበባ በዘላቂ የውሀ አቅርቦት እና ፍላጎት ዙሪያ ባተኮረው ‘Modelling scenarios for sustainable water supply and demand in Addis Ababa city, Ethiopia’  በተሰኘው ጥናት ላይ ተመሳሳይ የውሀ እጥረት ፈተና መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ “አዲስ አበባ ከተማ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያለውን የቤት ውስጥ ፍላጎቶችን ለማሟላት በጣም ጠቃሚ ሚና ያላቸው ውስን የከርሰ ምድርና ገጸ-ምድር የውሀ ሐብቶች ነው ያላት፡፡”

በእርግጥ የአቅርቦት ችግር ያለው ደህንነቱ የተጠበቀ ውሀ ብቻ ሳይሆን ሳሙናም ጭምር ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚያዝያ 2020 በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የማህበረ-ኢኮኖሚ ተጽዕኖን በመዳሰስ ለህትመት ባበቃው ሪፖርት ላይ የንጽህና አጠባበቅ ብዙ ጊዜ የሚቻል እንዳልሆነ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ውሀ እና ሳሙናን በቀላሉ ማግኘት ወይም ማቅረብ የማይቻል መሆኑ ነው የተጠቀሰው፡፡

የንጽህና ጉድለት ዋጋ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የንጽህና እና የአካባቢያዊ ጤና ስትራቴጂ እንዳመለከተው ከሆነ የንጽህና ጉድለት ኢትዮጵያን ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢዋ 2.1 በመቶ ያህል ወጪ ይጠይቃታል፡፡ ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት ደግሞ 6 ሚሊዮን መጸዳጃ ቤቶችን መገንባትና መጠቀምን ይጠይቃል፡፡

ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ እንዳመለከተው ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ በንክኪ የሚተላለፉ በሽታዎች የሚከሰቱት ደህንነቱ የተጠበቀ ውሀ ባለማግኘት እና በቂ ባልሆነ የጤና አጠባበቅና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በንጽህና አጠባበቅና መቀንጨር መካከል ጠንካራ ትስስር መኖሩን ያመለከተ ሲሆን፤ ሜዳ ላይ መጸዳዳት ደግሞ ለተቅማጥና ትውከት ለሚያስከትለው ለሆድ ህመም ሊዳርግ ይችላል፡፡ ይህም የአመጋገብ ጉድለት መንስኤ እና አባባሽ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ 

“የተቅማጥ በሽታ በኢትዮጵያ ከአምስት አመት በታች ለሆናቸው ህጻናት ሞት ዋንኛው መንስኤ ነው፡፡ ከአምስት አመት በታች የሆናቸው ህጻናት አጠቃላይ ሞት 23 በመቶውን ሲይዝ፤ ይኸውም በየአመቱ ከ70,000 በላይ ህጻናት ሞት ማለት ነው” ሲል የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ባለሞያ እና የቁሻሻ አወጋገድ አስተዳደር ቡድን አባል የሆኑት አብረሀም ምስጋናው እንደሚናገሩት እድሜያቸው ከ1 እስከ 9 የሆናቸው ህጻናት በአይን ማዝ (በትራኮማ) የመያዝ መጠን 40 በመቶ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ መንስኤው በኢትዮጵያ ደህንነቱ የተረጋገጠ ውሀ እና የንጽህና አጠባበቅ ጉድለት ነው፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ውሀ ኮቪድ 19 እና ውሀ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል በጣም አስላፈላጊ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ውሀ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች እጥረት ባለባቸው አካባቢዎችም ጭምር ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችል መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

የኮቪድ 19 ፈተናዎች ወደ እድል መቀየር

በኢትዮጵያ ኮቪድ 19 መከሰቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጋቢት 2020 ከታወቀ በኋላ ወዲያውኑ የኢትዮጵያ መንግስት እና የልማት አጋሮች የቅርብ ጊዜ የስነ ህዝብ እና ጤና ጥናትን መሰረት በማድረግ የህዝቦችን የውሀ፣ ጽዳት እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎት አቅርቦትን በተመለከተ ዳሰሳ አድርገው ነበር፡፡

Hygine 1

በዳሰሳው ግኝት መሰረትም በአሁኑ ወቅት የእጅ መታጠብ መመሪያዎችን ለመተግበር የህብረተሰቡ ውሀና ሳሙና የማግኘት ሁኔታ እጅጉን አነስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡  

በአዲስ አበባ ምንም እንኳ ደህንነቱ የተጠበቀ ውሀ እጥረት ቢኖርም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት በከተማዋ የውሀ መቋረጥ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ የተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች በከተማዋ የውሀ አቅርቦት እንዳይቋረጥ በተለይ ለእጅ ንጽህና አስፈላጊ የሆነው ውሀ እጥረት እንዳይከሰት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡

በአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰርካለም ጌታቸው እንዳስታወቁት ኮቪድ 19 መከሰቱ ከታወቀ ሰአት ጀምሮ የከተማዋ አስተዳደር ውሀ በከፍተኛ መጠን እንዲመረት እና እንዳይቋረጥ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡

እስከ አሁን ድረስም በከተማዋ ብዙ ወረዳዎች በተለይም ደግሞ የኮቪድ 19 የለይቶ ማቆያ ማዕከሎች በሚገኙባቸው ወረዳዎች ውሀ ሳይቋረጥ መቆየቱንና ሌሎቹ ከ116 ወረዳዎች 104 ወረዳዎች ደግሞ በተቻለ መጠን በአጭር ቀናት ተራ ውሀ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም ኃላፊዋ እንዳስታወቁት ባለስልጣኑ በከተማዋ የውሀ እና ጽዳት አገልግሎት ዘርፍን ለማቀናጀት ልዩ የውሀ፣ የፍሳሽ አገልግሎቶች መረጃ እና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ እንዲሁም የሎጂስቲክ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል፡፡

ኃላፊዋ እንዳስታወቁት በሁሉም የከተማዋ የህዝብ መጓጓዣ ጣቢያዎች፣ የህክምና ተቋሞች፣ ለይቶ ማቆያ ማዕከሎች እና ሌሎች የህዝብ መገኛ ቦታዎች የውሀ አቅርቦት እንዲኖር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል፡፡ ይህም የተደረገው የባለስልጣኑን 28 የውሀ ታንከር መኪኖች እና ሌሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጽህፈት ቤት እና የውሀ ሚኒስቴር የተበረከቱ የውሀ ማጠራቀሚያዎችን በመጠቀም ነው፡፡

“አሁን እየተሰራበት ያለውን የማህበረሰቡን የውሀ አቅርቦት ከመከለስ ባሻገር የከተማዋ አስተዳደር አገልግቱን ለማሻሻል ተጨማሪ የከርሰ ምድር ውሀ (የጉድጓድ ውሀ) ከሰባት ቦታዎች በላይ እያለማ ነው” ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባለስልጣኑ ውጤታማ የሆነ የፍሳሽ አወጋገድን እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ለእጅ መታጠብ እና ንጽህና መጠበቂያ የውሀ ምርት መጠን ማሳደጉን ነው የጠቀሱት፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል የላቀ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ አጋሮች መካከል የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ ዩኒሴፍ አንደኛው ነው፡፡ 

ከተቋሙ እንቅስቃሴ አንደኛው “አሁን እየተሰራበት ያለውን የተቀናጀ የመገናኛ መልዕክቶችን ማሳደግ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የመንግስት ድጋፍ ታክሎበት ብሔራዊ የቴሌኮም ኩባንያ በስልክ ጥሪዎች ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ መልዕክቶች እንዲተላለፉ አድርጓል፡፡ ይህም በመላ ሀገሪቱ የስልክ ተጠቃሚዎችን በሙሉ ተደራሽ ያደረገ ነው” በማለት በዩኒሴፍ የዎሽ water, sanitation, and hygiene (WASH) ኃላፊ ኪትካ ጎዮል ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የድሀ ድሀ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ የእጅ መታጠብ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ዩኒሴፍ እየሰራ እንደሆነም ነው ኃላፊው ያስታወቁት፡፡

Hygine 2

“እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትም ቢሆን የውሀ፣ የንጽህና እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎት የማግኘት ችግር ያለባቸው ናቸው” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የድሀ ድሀ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ የእጅ መታጠብ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ዩኒሴፍ እየሰራ እንደሆነም ነው ያስታወቁት፡፡

“እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትም ቢሆን የውሀ፣ የንጽህና እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎት የማግኘት ችግር ያለባቸው ናቸው” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ዩኒሴፍ አዲስ አበባ ውስጥ 10,000 ሊትር ውሀ የሚይዙ ስድስት የውሀ ማጠራቀሚያ ሮቶዎችን፣ በየማዕከሎቹ የውሀ አቅርቦት ለማሳደግ አምስት የተለያዩ የገጸ ምድር ውሀ ማውጫ ሞተሮችን ያቀረበ ሲሆን፤ 13,050 ደረቅ ሳሙናዎችን፣ ባለ 150 ሚሊ 250 ጠርሙስ የዕጅ ማጽጂያ (ሳኒታይዘር) ጨምሮ የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያዎችን ለጤና ባለሞያዎች አቅርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 250 የፕላስቲክ ባልዲዎች፣ 130 ጀሪካኖችን፣ መክፈቻና መዝጊያ የተገጠመላቸው 95 የእጅ መታጠቢያዎችን፣ 12 አካባቢን ለማጽዳት የሚረዱ በጀርባ የሚታዘሉ የኬሚካል መርጪያዎች ቦርሳዎችን፣ ለጽዳት እና አካባቢዎችን ለማጽዳት የሚረዱ 30 የውሀ ማከሚያ በርሜሎች ክሎሪን ድጋፎችም ይገኙበታል፡፡

ዩኒሴፍ በከተማ የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ጋር በመተባበር በሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ቤተሰቦች 210,000 ደረቅ ሳሙናዎችን የለገሰ ሲሆን፤ እና እጅን በሳሙና የመታጠብን አስፈላጊነት የሚያስረዱ የጤና አጠባበቅ መልዕክቶችንም አብሮ አስተላልፏል፡፡ 

የአለም ባንክ በበኩሉ በኢትዮጵያ ሁለተኛው የከተማ ውሀ አቅርቦት እና ንጽህና ፕሮጀክቱ  “Second Urban Water Supply and Sanitation Project in Ethiopia” የከተማዋን የውሀ አቅርቦት ለማሳደግ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር በቅርበት እየሰራ ነው፡፡ 

“ከስራዎቹ መካከል በከተማዋ ነባሩን የከርሰ ምድር የውሀ ምንጮች የማሻሻል እና ህዝብ በብዛት ለሚኖርባቸው አካባቢዎች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ያልተቆራረጠ የውሀ አገልግሎቶችን ለመስጠት 20 የከርሰ ምድር ውሀ ማውጫዎችን የመቀየር ስራዎች ይገኙበታል” በማለት የአለም ባንክ አስታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከ3ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያኖች መሰረታዊ የውሀ አቅርቦት እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያገዘ ሲሆን፤ በከተሞች አካባቢ ከ623,000 በላይ ህዝብን  የተሻሻሉ የውሀ ማግኛ ምንጮች እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በየቤቱ 61,000 አዳዲስ የቧንቧ ውሀ መስመሮች ዝርጋታ፤ በከተሞች ለ2.7 ሚሊዮን ሰዎች ጥንቃቄ የተሞላበት የሰገራ አወጋገድ፣ በአዲስ አበባ ከ50,000 በላይ ለፍሳሽ ቁሻሻ ማስወገጃ መስመሮች ዝርጋታ፣ እና 1,000 ለህዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ ድጋፍም አድርጓል፡፡ 

በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የውሀ፣ የጽዳትና እና ንጽህና አጠባበቅ ዋና ኃላፊ ኪትካ ጎዮል እንደገለጹት፤ ዩኒሴፍ በቀጣዩ የኢትዮጵያ የበጀት አመት በመላው ሀገሪቱ የተለያዩ የጽዳትና ጤና አጠባበቅ እንቅስቃሴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ የስራ እቅዶች ላይ ለመስራት ከውሀ፣ ከጤና እና ከትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከክልል ቢሮዎች ጋር ተስማምቷል፡፡

ይሁንና አንዳንድ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ለበርካታ ወራት ከፍተኛ ጥረት ከተደረጉ በኋላ በአዲስ አበባ የውሀ አቅርቦት አገልግሎቶች በቅርቡ መቀነሱን ነው፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የመንገድ ላይ ነጋዴ የሆነችው ወርቄ ደበበ ሰዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላል የሚያደርው ጥንቃቄ አሁን ላይ እንደቀነሰና በተመሳሳይ መልኩም በአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን በኩልም የውሀ አቅርቦቱ እንዲሁ መቀነሱን ነው የምትናገረው፡፡

“በከተማችን አዲስ አበባ በየመንገዱ ለእጅ መታጠብ አገልግሎት በአነስተኛ የውሀ ማጠራቀሚያ የሚቀርበው ውሀ ቀጣይነት ያለው አልሆነም፡፡ በፊት ላይ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች በየእለቱ ውሀ በቦቴ መኪና እየመጣ ይሞላ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በአብዛኛው ይህ አገልግሎት ተቋርጧል” ብላለች፡፡

ይህም ቢሆን ግን በርካታ ነዋሪዎች የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በቂ የውሀ አቅርቦት እንዲኖር የከተማዋ አስተዳደር ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር በመሆን ያደረገውን የተቀናጀ ጥረት ያደንቃሉ፤ አመራሮቹ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው የሚጠይቁት፡፡ 

በየካ ክፍለ ከተማ በኢ-መደበኛ የንግድ ስራ ላይ የተሰማራችው ላቀች ዘለቀ፤ የውሀ አቅርቦት እንደ ሆስፒታል፣ የባቡር ጣብያዎች፣ እና የገበያ ቦታዎችን በመሳሰሉ በተመረጡ ቦታዎች የውሀ አቅርቦት መሻሻሉን ነው የምትናገረው፡፡ “በከተማዋ መንግስትና በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት በከተማችን የውሀ አቅርቦትን ለማሳደግ በተደረጉ ጥረቶች በጣም ደስተኛ ነኝ” 

“በእኔ አመለካከት አሁን ላይ በአዲስ አበባ የተስፋፋው የእጅ መታጠብ እና ንጽህና ባህል እና በከተማዋ አስተዳደር የተደረገው የውሀ አቅርቦት ወደፊትም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ካበቃም በኋላ ቢሆን ሊቀጥል የሚገባው ባህል መሆን አለበት፡፡ ለራሳችንም ሆነ ለልጆቻችን ጤንነት በጣም ጠቃሚ ነውና” ብላለች፡፡

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts