በዱስዴዲዝ ካሃንግዋ – ዳሬሰላም
በዳሬ ሰላም ኪቩኮኒ የባህር ዳርቻ በባራክ ኦባማ መንገድ በኩል ታንዛኒያ ቤተ-መንግስት በስተ ሰሜን ሶስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ የምሲምባዚ ዳርቻ ይገኛል፡፡ በዚህ ቦታ ነው በታሪክ ስመ ጥር የሆነው የምሲምባዚ ወንዝ ከህንድ ውቅያኖስ ጋር የሚገናኘው፡፡
በአንድ ወቅት ለአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚ ሀብት የነበረው ይህ ወንዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በየአመቱ ከጎርፍ ጋር በተያያዘ ሰብአዊ ቀውስ በማስከተል እዳ ሆኖባቸዋል፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው በምሲምባዚ ወንዝ ተፋሰስ ከጎርፍ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳቶች መከሰት የጀመረው በ1997 ኤልኒኖ ዝናብ ነው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየአመቱ ጎርፍ ይከሰታል፡፡ እስከአሁን ድረስም ዳሬ ሰላም በ2010፣ በ2011፣ በ2014፣ በ2015፣ በ2017፣ በ2018፣ በ2019 እና በ20202 ቢያንስ አንድ የጎርፍ አደጋ አስተናግዳለች፡፡ ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜም በጥቂት ሰአታት ውስጥ የውሀው ከፍታ ከወንዙ ዳርቻዎች በላይ ሁለት ሜትር ወይም ከዚያ በላይ በላይ ይሆናል፡፡ (WB 2018b: 17)
ይህ ለመጨረሻ ጊዜ የተከተሰተው በዲሴምበር 17 ቀን 2019 ሲሆን፤ ከባድ ዝናብ በምሲምባዚ ወንቅ ተፋሰስ እና በዳሬሰላም ዙሪያ በሙሉ ከፍተኛ ጎርፍ ባስከተለ ጊዜ ነው፡፡ ያን ግዜ ጎርፉ በሸለቆው ውስጥ ያሉ መኖሪያ ቤቶችን በማጥለቅለቅ ብዙዎችን ቤት አልባ አደረገ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጃንግዋኒ ድልድይ፣ የምክዋጁኒ ድልድይ፣ ከሼኪናንጎ መንገድ ጋር ያለው የሙጋቤ ድልድይ፣ እና ኪጎጎ ድልድይ ጨምሮ በወንዙ ተፋሰስ አካባቢ ያሉ ብዙ ድልድዮችም በውሀ ተሸፈኑ፡፡ ሁሉም የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተቋረጡ፡፡ የህዝብ መጓጓዣም ቀኑን በሙሉ ተቋረጡ፡፡ የተወሰኑ ቤቶች ፈረሱ፣ የቤት እቃዎች በውሀ ተወሰዱ፤ በርካታ ንጹሀን ነፍሶችም ተነጠቁ፡፡
በረዳት ኮሚሽነር ፖሊስ ጁማ ንዳኪ የሚመራው የፖሊስ ሀይል ቢዘያ ቀን የነዋሪዎችን ደህንነት እና ንበረታቸውን ለመጠበቅ የሂሊኮፕተር ቅኝት አድርጎ ነበር፡፡
“ትልቁ ተጽዕኖ የደረሰው በምሲምባዚ ወንዝ ተፋሰስ ነው፡፡ በዚያ አካበቢ የደረሰው ሁኔታ እጅግ ልብ ሰባሪ ነው፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች በፍጥነት መውጣት እንዳለባቸው መንግስታችን ያስተላለፈውን ትዕዛዝ አበክረን መግለጽ እንወዳለን፡፡ የውይይት ጊዜው አብቅቷል” ሲሉ ከአካበቢ ቅኝታቸው በኋላ ንዳኪ ተናግረዋል፡፡
የጎርፉ መከሰት ለታንዛኒያ መንግስት ያስታወሰው ነገር ቢኖር በምሲምባዚ ተፋሰስ ተደጋጋሚ ጎርፍን ለማስቀረት የሚያስችል መፍትሔ በአስቸኳይ የመቅረጽ እና የመተግበርን አስፈላጊነት ነው፡፡
ምንም እንኳን በከተማዋ እንደ ድልድዮች እና ፈጣን ተንቀሳቃሽ አውቶብሶች የሚከንፉበት መንገድ አይነት ዘመናዊ መሰረተልማት ለመገንባት በመንግስት የሚደረጉ የቅርብ ጊዜ ጥረቶች ቢኖሩም፤ ዳሬሰላም አሁንም ለሁሉም ዜጎች አስተማማኝ ከተማ አይደለችም፡፡ በከፍተኛ ህዝብ ብዛት እና አካባቢያዊ ጉዳት የተነሳ የወንዙ ተፋሰስ የሰው ልጆች ህይወትና ንብረትን፤ እንደ ድልድይ፣ ትምህርት ቤቶች ሆስፒታሎች እና እስከ 9,000 የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶች የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ለአደጋ አጋልጧል፡፡ (WB 2018b: 18, 39)
የታንዛኒያ መንግስት ሰላማዊ የሆነች ከተማን ለመገንባት በ2018 ከብሪቲሽ ልማት ድጋፍ ኤጀንሲ፣ ከአለም ባንክ እና ሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር “የምሲምባዚ እድል፤ የምሲምባዚ ተፋሰስን ወደ ተረጋጋ የከተማ ወደብነት መቀየር” (“Msimbazi Opportunity: Transforming the Msimbazi Basin into a Beacon of Urban Resilience.” ) ተብሎ የሚጠራ ፕሮጀክት አጠናቆ ነበር፡፡
ይህ እስከ 200ሚ የአሜሪካን ዶላድ ድረስ የሚፈጀው የምሲምባዚ ፕሮጀክት የምሲምባዚ ተፋሰስን በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚደርሰውን ሰብአዊ ቀውስ እስከ መጨረሻው የማስቀረት እቅድን የያዘ ነው፡፡ (WB 2018b: 95) የ30 አመቱ ፕሮጀክት፤ ከያዛቸው አቅጣጫዎች መካከል አካባቢውን ከጎርፍ ለመከላከል ስነ-ምህዳሩን መጠበቅ፣ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ያሉ ሰዎችን መልሶ ማስፈር፣ እና አካባቢውን ለመጠበቅም ሆነ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል በመስጠት በአዲሱ የከተማ ፓርክ ቫይብራንት የቢዝነስ ተቋማትን መገንባት የሚሉት ይገኙበታል፡፡ (WB 2018b: 19; )
የምሲምባዚ ተፋሰስ፤ በመሀል ዳሬ ሰላም
የምሲምባዚ ተፋሰስ የሚገኘው በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ የአለማችን 30 ከተሞች አንዷ በሆነችው ዳሬ ሰላም ነው፡፡ እንደ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሴኩሪቲስ ስተዲስ (the Institute of Security Studies) ጥናት በ2030 ከአለማችን 41 ትልልቅ ከተሞች አፍሪካ የስድስቱ መገኛ ስትሆን፤ ዳሬ ሰላም ደግሞ ከስድስቱ ከተሞች አንዷ ትሆናለች፡፡
በ2019 የታንዛኒያ ብሔራዊ ቢሮ ስታስቲክስ ይፋ ባደረገው የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሀገሪቱ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት የዳሬ ሰላም የህዝብ ብዛት እድገት መጠን 5.6 ከመቶ ነው፡፡ ይህም ማለት በ2030 የህዝብ ብዛቷ ቁጥር ከአሁን ካለበት 5,147,070 ወደ 10 ሚሊዮን ያድጋል ማለት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ትልቋ የአለማችን ከተማ ያደርጋታል፡፡ (NBS 2019:17)
የምሲምባዚ ወንዝ ውሀ በሲላንደር ድልድይ በኩል ወደ ህንድ ውቅያኖስ ይፈሳል፡፡ ውሀው ወደ ውቅያኖሱ የሚገባው ኪኖንዶኒ፣ ላላ እና ኪሳራዌ የተባሉ ሶስቱን ወረዳዎች የሚያገናኘውን ሸለቆ በማቋረጥ ረጅም ጉዞ ካደረገ በኋላ ነው፡፡
የምሲምባዚ ወንዝ ተፋሰስ 271 ኪሎ ሜትሮችን ያህል የሚሸፍን ሲሆን፤ ይህም የዳሬ ሰላምን ህዝብ 27 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ (WB 2018b:19) ተፋሰሱ በአራት ዋና ዋና አካባቢዎች የተከፈለ ሸለቆ ሲሆን እነሱም፤ የላይኛው ተፋሰስ፣ የላይኛው መካከለኛ ተፋሰስ፣ የታችኛው መሀል ተፋሰስ እና የታችኛው ተፋሰስ ናቸው፡፡ የመንገድ ኔትወርክ እና ሌሎች ግዙፍ መሰረተልማቶች ተፋሰሱን ያቋርጣሉ፡፡
የፕሮጀክቱ ሰነድ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ (the Project document) በምሲምባዚ ወንዝ ተፋሰስ 1.6 ሚሊዮን ነዋሪዎች፤ በላይኛው የተፋሰሱ ክፍሎች በሲላንደር ድልድይ እና ማንዴላ መንገድ መካከል በታችኛው የተፋሰሱ ክፍሎች ደግሞ 250,000 ነዋሪዎች ይገኛሉ፡፡ በ2030 የምሲምባዚ ወንዝ ተፋሰስ 2.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች መገኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ (WB 2018b,19)
ምንም እንኳ ፈጣን የህዝብ ብዛት እድገት ቢኖርም በዳሬ ሰላም መደበኛው የህዝብ ሰፈራ መጠን 30 በመቶ ብቻ እንደሆነ የምሲምባዚ ፕሮጀክት ሰነድ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ይኸውም አብዛኛውን ህዝብ ኑሮውን የሚገፋው መደበኛ ባልሆነ መሰረተልማት እንደሆነ ነው፡፡ (WB 2018b,17)
በ9,000 መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ 50,000 ነዋሪዎች በየአመቱ በጎርፍ አደጋ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እንደ ፕሮጀክቱ ሰነድ ከሆነም ይህ ለሰው ልጆች ህይወት ምቹ አይደለም፡፡ (WB 2018b:7)
በምሲምባዚ ወንዝ ጎርፍ ከተጥለቀለቁ መሰረተ ልማቶች መካከል የሙሂምቢሊ ብሔራዊ ሆስፒታል፣ የሞሮጎሮ መንገድ፣ የካዋዋ መንገድ፣ ሼኪላንጎ መንገድ፣ ታንዳሌ መንገድ፣ ማንዴላ መንገድ፣ የተወሰነው የብሔራዊ ባቡር መንገድ፣ የዳሬ ሰላም ፈጣን መሻገሪያ፣ የአሁኑ ሲሚንቶ ፋብሪካ እና በማንዴላ መንገድ አቅራቢያ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ቦታ ይጠቀሳሉ፡፡
ለችግሩ አስተዋጽኦ ካደረጉ አይነተኛ ምክንያቶች መካከል በወንዝ አካባቢ የሰዎች ሰፈራ፣ በወንዞች ዳርቻ የአፈር መሸርሸር፣ የዝናብ ውሀን ፍሰት የሚያግዱ መሰረተ ልማቶች ግንባታ፣ በወንዙ ላይ ደረቅ ቁሻሻ ማስወገድ፣ እና አጠቃላይ የአካባቢ መራቆት እንደሚገኙበት በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ (WB 2018b:27-38)
ባለፉት አስርት አመታት በምሲምባዚ ወንዝ የተፈጥሮ ስነ ምህዳሩን እና አየር ንብረትን ሚዛናዊነት እስኪያባብስ ድረስ ያልተጠበቀየአየር ንብረት ለውጥ ነበረ፡፡ (WB 2018b:7) በተመሳሳይ ጊዜ በምሲምባዚ ወንዝ ተፋሰስ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰላማዊ የአየር ንብረት ለውጥ በበቂ ሁኔታ አግኝተው አያውቁም፡፡ የዚህም ውጤት በህይወታቸውና አካባቢ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡
ያልተሳካው መፍትሔ፤ ማባረርና መልሶ ማስፈር
ጎርፎች በሚከሰቱ ጊዜ በአብዛኛው የሚወሰደው መፍትሔ ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች ጨርሶ እንዲወገዱ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዘላቂ መፍትሔ ሆኖ አያውቅም፡፡ የ2011 ጎርፍ ከተከሰተ በኋላ ወዲያውኑ 680 ተጎጂ መኖሪያ ቤቶች ተወግደው መልሶ ሰፋሪዎቹ ከዳሬ ሰላም 25 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው በማብዌፓንዴ መሬት ተሰጣቸው፡፡ ወደ 1,007 የሚጠጉ መሬቶች የወደሙ ሲሆን 3,400 ሰዎች ተዛውረውም ነበር፡፡ የቧንቧ ውሀ መስመርም ተዘርግቶላቸው ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶችም ተገንብተው ነበር፡፡ (WB 2018b:21)
ይሁንና አብዛኞቹ ተፈናቃይ ሰዎች ልክ ዝናቡ እንደቀነሰ ወዲያውኑ ወደ ምሲምባዚ ተፋሰስ ተመልሰዋል፡፡ ምክንያቱም ለስራ ፈላጊዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ባለመኖራቸው፣ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ማህበራዊ አገልግሎቶችና የመጓጓዣ አገልግሎቶች ባለመኖራቸው ነው፡፡
በ2015 መንግስት በኪኖንዶኒ ወረዳ በሀናናሲፍ ከወንዙ 60ሜ ነጻ እንዲሆን የታሰበውን አካባቢ የወረሩ ሰዎችን ለማባረር ሲል 700 የሚሆኑ ቤቶችን አፍርሷል፡፡ በህዝብ ቅሬታ እና ፍርድ ቤትም ድርጊቱን በህገ-ወጥነት ከሰየመ በኋላ መንግስት ሰዎችን ማባረሩን አቋርጧል፡፡ (WB 2018b:23)
የምሲምባዚ እድል እቅድ
የታንዛኒያ መንግስት በ2018 ኦገስት ወር ላይ “የምሲምባዚ እድል እቅድ” የሚል ፕሮጀክትን ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን፤ ከጎርፍ ጋር በተያያዘ በየአመቱ በቀጠናው የሚከሰቱ አደጋዎችን ለማስቀረት፣ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ እና ተፋሰሱን ለነዋሪዎች የኢኮኖሚ እድሎች መገኛ ለማድረግ ያሰበ ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ በ2018 በጃንዋሪ እና ኦገስት ወር መካከል 30 የምርምር ጊዜዎች፣ ውይይት እና አርትኦት ስራዎች ለማከናወን የተገናኙ ከ200 በላይ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ጥረቶች ውጤት ነው፡፡ እነዚህ ባለድርሻ አካላት በብሪቲሽ መንግስት እና በምክትል ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ተቆጣጣሪነት ፕሮጀክቱን የቀረጹ 60 የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተቋማት ናቸው፡፡
ሒደቱን ለማስጀመር ከመንግስት እና ልማት አጋር ተወካዮች ጋር ስብሰባ የተደረገው በህዳር ወር ነበር፡፡
የምሲምባዚ ፕሮጀክት ተፋሰሱን ከአደገኛ ሸለቆነት የከተማዋ ልብና ሳምባነት በመቀየር ለነዋሪዎች ምቹ ወደ ሆነ ተስማሚ አካባቢነት ለመቀየር የሚሻ ነው፡፡
አካባቢውን ለመጠበቅም እቅዱ ችግኞችን ለመትከል፣ የተፋሰሱን የዝናብ ውሀ የመያዝ አቅም ለመጠበቅ፣ ወደ ወንዙ የሚሉ ቁሻሻዎችን ለማስቆም እና በወንዙ ላይ የሚካሔዱ የሰዎችን እንቅስቃሴዎች ለመግታት፣ በወንዙ ግድግዳዎች የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና ለጎርፍ የሚዳርጉ ደለልን ለመቀነስ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የነደፈ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከአደገኛ ጎርፍ ለመጠበቅ፣ ወንዙን ጥልቀቱን በማስፋት፣ ስፋቱን በመጨመር እና የውሀ ማውረጃ ደረጃዎችን በመስራት ወደ ምሲምባዙ ዳርቻ ውሀ የማጓጓዝ አቅሙን ለመጨመር ያቀደ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እቅዱ የባህር ዳርቻዎችን በማሳደግ እና ጎርፍ ሲከሰት በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን እና የቢዝነስ ሰዎችን አስነስቶ ከጎርፍ ስጋት ነጻ በሆነ ቦታ በመውሰድ በሸለቆው አካባቢ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ የጎርፍ አደጋ እንዲቀስ ይተጋል፡፡
በመጨረሻም የአካባቢውን የኢኮኖሚ እድገት አቅም ለማጠናከር፤ ፕሮጀክቱ በሴላንደር ድልድይ እና ካዋዋ መንገድ መካከል የመጫወቻ ሜዳዎች፣ የመኖሪያ ህንጻዎች፣ ቢዝነስ እና ኮንፈረንስ እና ቢሮዎችን ያካተተ የከተማ ፓርክ የመገንባት እቅድ አለው፡፡
ፕሮጀክቱ 12,000 ቢዝነስ፣ የቢሮዎች፣ የገበያ ማዕከሎች እና የመኪና ማቆሚያዎችን እንዲሁም 2,500 የመኖሪያ ክፍሎችን ለመገንባት ያቀደ ነው፡፡ ከእነዚህ ግንባታዎች ሊገኝ የሚችለው ገቢ ግምት ለምሲምባዚ ወንዝ ተፋሰስ ኢንቨስትመንት የወጣውን ወጪ በየአመቱ 18 በመቶ በመመለስ ሙሉ ለሙሉ በ12 አመት እንደሚመልስ ነው፡፡ (WB 2018a:17)
ከዚህ አመት ጀምሮ በየደረጃው ተግባራዊ እየሆነ እስከ 2050 አመት ድረስ ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀውን አጠቃላይ ፕሮጀክቱን ለመቆጣጠር ከሁሉም ኤጀንሲዎችና ክፍሎች የተውጣጣ አዲስ አስተዳደራዊ አሰራርን ለማቋቋም የፕሮጀክቱ ሰነድ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
በፕሬዝዳንቱ ቢሮ የሀገሪቱ ሚንስትር ስሌማኒ ጃፎ ከ2018 ጀምሮ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ በይፋ ቃል ገብተዋል፡፡ እስከ አሁን ግን የገንዘቡ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ አልተገኘም፡፡ ፕሮጀክቱ በአለም ባንክ ትረስት ፈንድ በኩል በብሪታንያ የልማት ኤጀንሲ የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቱን ለመጀመር 100 ሚሊዮን ዶላር ከአለም ባንክ በብድር መልክ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ ፕሮጀክቱ ሰነድ ከሆነ የፕሮጀክቱ ሙሉ ወጪ ከ120 እስከ 200ሚ ዶላር ይሆናል፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥም ሌላ የፕሮጀክት ሰነድ እንደሚገልጸው 55ሚ ዶላር የታችኛውን የምሲምባዚ ተፋሰስ አጋማሽን ለመጠገን ያስልጋል፡፡ 49ሚ ዶላር ደግሞ የላይኛውን የተፋሰሱን አጋማሽ ለማደስ ያስፈልጋል፡፡ በላይኛው የወንዙ አጋማሽ ችግኞችን ለመትከል እና ደረቅ ቁሻሻዎች ለማጽዳት 10ሚ ዶላር ያስፈልጋል፡፡ (WB 2018a:18)
ከምሲምባዚ ፕሮጀክት አስተባባሪ ከኢንጂነር ንያሪሪ ናናይ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ላይ እንደተመለከተው ፕሮጀክቱ ብድር ከተፈቀደው የሀገሪቱን የብድር መጠን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ለማወቅ የገንዘብ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ደረጃ የተግባራዊነት ጥናት በማድረግ ላይ ነው፡፡
መንግስትም ለፕሮጀክቱ ምን ያህል እንደሚያዋጣ እስከአሁን ይፋ አላደረገም፡፡ የመጨረሻው የፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ውሳኔን በተመለከተ በጁን ወር ላይ በ2020/2021 በጀት ሒደት ወቅት ሊታወቅ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ
የኪጂቶንያማ ነዋሪ እና በካምፓላ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርስቲ በዳሬሰላም ካምፓስ መምህር የሆኑት ዶክተር ዊልሰን ቤቤዬቦኔላ የፕሮጀክቱን እቅድ በተመለከተ ግንዛቤው እንዳላቸው እና ለተግባራዊነቱም ድጋፍ እንደሚሰጡ ነው የተናገሩት፡፡
ለዶክትሬት ጥናታቸው ባዘጋጁት የዳሰሳ ጥናቶቻቸው ላይም የምሲምባዚ ወንዝ ከገባር ወንዞቹ በኩል ደረቅ ቆሻሻዎችን እንደያዘ አቋርጦ በሚሔደው በኪኒንዶኒ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ ችግርን ለይተዋል፡፡
“በምሲምባዚ ወንዝ እና በገባሩ በሲንዛ ወንዝ ላይ ደረቅ ቁሻሻን የመጣል ችግር በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የምሲምባዚ ተፋሰስ ፕሮጀክት የተወሰነውን ባጀቱን ለዚህ አካባቢ በማሰቡ ደስተኛ ነኝ” ሲሉ ዶክተር ቤቢዬንላ ተናግረዋል፡፡
የአይላላ ነዋሪ የሆነው መሐመድ ካይሊ በምሲምባዚ ወንዝ እድሳት ፕሮጀክት በጣም መደሰቱን ነው የገለጸው፡፡ ምክንያቱም ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ሲባል ለሚነሱ ለሁሉም ነዋሪዎች ካሳ ለመክፈል እቅድ በመኖሩ ነው፡፡
“እነዚህን ቤቶችን ስንገነባ በአግባቡ አልተመራንም ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የወንዙን ወሰን ምልክቶች እንኳ አላየንም፡፡ ነገር ግን አሁን መንግስት ለእኛ ካሳ ከሰጠን በኋላ ተፋሰሱን መልሶ እንዲያገግም ማቀዱ በጣም ጥሩ ነገር ነው” ብሏል፡፡
የታባታ ነዋሪ የሆነው ፕሪቫቱስ ካሩጌንዶ በበኩሉ የዳሬ ሰላም ከተማ ሀፍረት እንዲያበቃ የምሲምባዚ ፕሮጀክት በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን ለመንግስት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
“ከ1970ዎቹ ጀምሮ መንግስት የምሲምባዚ ተፋሰስ ለሰው ልጆች ህይወት አደገኛ ቦታ መሆኑን የሚያሳይ የከተማ እቅድ ካርታ ነበረው፡፡ በብሔራዊ የአካባቢ አስተዳደር ካውንስል የተዘጋጀው የአካባቢ ጥበቃ ህጉ ከወንዙ መሀል ጀምሮ 60 ሜትር ራዲየስ ከሰው ልጆች እንቅስቃሴ ነጻ መሆን እንዳለበት ደንግጓል፡፡ ይሁንና ተግባዊነቱ ግን ደካማ ነው፡፡ ነገር ግን አሁ መንግስት ራሱ ለማስተካከል እንደተዘጋጀ ይሰማኛል” በማለት ካሩጌንዶ ይናገራል፡፡ የመንግስት ማስተር ፕላን 1979 የወጣ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ተጠራጣሪዎች የገንዘቡን ጣሪያ መንካት ይጠይቃሉ
ምንም እንኳን ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ ድጋፍ ቢኖርም፤ የምሲምባዚ ፕሮጀክት የተቃውሞ ድምጾችና ፈተናዎች ሳይደርሱበት አልቀረም፡፡ በዋናነትም ደግሞ ከሀገሪቱ በጀት አንጻር ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት እጅግ ከፍተኛ ሀብት የሚያስፈልግ መሆኑ ነው፡፡
አንዳንዶች መንግስት የፕሮጀክቱን ወጪ መቀነስ እንዳበት፤ ነገር ግን በላይኛው የተፋሰሱ አካባቢ የደን ጥበቃውን እና በታችኛው ተፋሰስ ደግሞ የከተማ ፓርክ ልማት እቅዶቹን ማስቀረት እንዳለበት ያምናሉ፡፡
ጃሚፎረምስ በተባለ ድረገጽ ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ የምሲምባዚ ፕሮጀክት ዘገባ በቀረበበት ዳሚኮን አግሪፋርም ላይ እንደተናገሩት፤ በምሲምባዚ ተፋሰስ ፕሮጀክት በኩል ቀጥተኛ የውጭ ሀገር ኢንቨስትመንትን መፍቀድ የኢኮኖሚ ኢምፔሪያሊዝም እንደመቀበል የሚቆጠር ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ኤዲ በሚል ስም ሀሳቡን ያቀረበ ግለሰብ በበኩሉ፤ የምሲምባዚ ፕሮጀክት “ምንም የማይረባ” እንደሆነ ነው የገለጸው፡፡
በፕሮጀክቱ ዲዛይን ላይ የተካተተቱ አብዛኛዎቹ መልስ ሰጪዎች ከሀገር ውስጥ እና እንደ አለም ባንክ ካሉ የውጭ ሀገር የገንዘብ ምንጮች የፕሮጀክቱ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚገኝ ተስፋ አድርገዋል፡፡ ምንክንያቱም እነዚህ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪ አካላት በምሲምባዚ ፕሮጀክት ዲዛይን ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ስለነበራቸው ነው፡፡ በታንዛኒያ መንግስትም በኩል የገንዘብ ብድር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁነታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና ገለልተኛ አስተያየት ሰጪዎች መንግስት ትኩረቱን ከአየር ንብረት አስተዳደር ጉዳዮች ወደ በኢንደስትሪው ዘርፍ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች በመለወጡ የተነሳ የፕሮጀክቱ ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን ይጠራጠራሉ፡፡
ሮበርት ኪዩንሲ በታንዛኒያ በአርድሂ ዩኒቨርስቲ በኢንቫይሮመንት ሳይንስ እና ቴክኖሊጂ ትምህርት ቤት ከፍተኛ መምህር እና የአደጋ መቆጣጠር ስልጠና ማዕከል ዳይክሬተር ናቸው፡፡ እንደ ዳሬ ሰላም ባሉ የግዙፍ ልማት እጥረት ባለባቸው ከተሞች የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለመስራት ፈተና በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት አድርገዋል፡፡
በመሆኑም የአሁኑ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያተኩረውን የምሲምባዚ ተፋሰስ ፕሮጀክት ትግበራ በገንዘብ ለመደገፍ ከፍተኛ የሆነ ተነሳሺነት ላይኖረው እንደሚችል ኪዩንሲ ያምናሉ፡፡
የፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ሊገኝ እንደማይችል ሌላኛው ተጠቃሽ ምክንያት በታንዛኒያ መንግስት እና በፕሮጀክቱ ዋንኛ የገንዘብ ደጋፊ በአለም ባንክ በኩል ያለው ጠንካራ ግንኙነት እየላላ መምጣቱ ነው፡፡ ከ2015 ጀምሮ የአለም ባንክ በታንዛኒያ መንግስት የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍ ነፍሰ ጡር ሴት ተማሪዎችን ከትምህርታቸው በማባረሩ የቀረበለትን የብድር ጥያቄ መልስ ሳይሰጥ አቆይቶቷል፡፡
ኪዩንሲ ባለፉት ቅርብ ጊዜያት የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲው ከብሔራዊ ፖለቲካ አጀንዳ የመጨረሻውን ደረጃ መያዙን በመግለጽ ይሞግታሉ፡፡ መንግስት እንደ መንገድ ስራ እና እንደ ሴለስ ጌም ሪዘርቭ ያሉ የተፈጥሮ ስነ ምህዳርን የሚረብሹ እንደ ንሬሬ ሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ያሉ ከፍተኛ የካርበን ልቀት ባላቸው የኢንዱስትሪ እና መሰረተልማት ፕሮጀክቶች ትኩረት መስጠቱን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
ለአምስተኛ ተርም በሚመራው በታንዛኒያ መንግስት ህግ መሰረት አንዲት ተማሪ ነፍሰ ጡር ከሆነች ትምህርቷን በመደበኛው የትምህርት ስርአት መቀጠል አትችልም፡፡ ይህንን በተመለከተ ለዴቬክስ ኒውስ ኤጀንሲ የሚጽፈው ማይክል ኢጎን ጨምሮ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዘጋቢዎች በታንዛኒያ እና በአለም ባንክ መካከል የሻከረ ግንኙነት መፈጠሩን ዘግበዋል፡፡
ጃሚፎረምስ ላይ ቫፕስ በሚል ስም አስተያየቱን ያሰፈረ አንድ ግለሰብ በታንዛኒያና የአለም ባንክ መካከል እንዲህ ያለ የላላ ግንኙነት እያለ የታንዛኒያ መንግስት የምሲምባዚ ተፋሰስ ፕሮጀክት ድጋፍ ከአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው ብሏል፡፡
“እንደዚህ ያለ የመልቲ ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክትን ለመተግበር ለአምስተኛ ተርም ከሚመራ መንግስት ጋር የሚተባበር የቢዝነስ አጋር የለም” ሲል አስተያየቱን አስፍሯል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ንያሪሪ ናናይ በሰጡት አስተያየት “የመንግስት ገንዘቡን የመበደር ውሳኔ ከሀገሪቱ ብድር ሂሳብ የሚበልጥ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ጥብቅ የሆነ ጥናት የሚደረግበት ጉዳይ ነው፡፡
የዚህ ዘገባ ጥንቅር የተዘጋጀው በኢንፎናይል እና በናሽናል ጂኦግራፊክ ሶሳይቲ ድጋፍ ነው፡፡