ኮቪድ 19 ያስከተለው የውሀ ችግር በዲሞክራቲክ ኮንጎ

ኮቪድ 19 ያስከተለው የውሀ ችግር በዲሞክራቲክ ኮንጎ

በፍሬድ ምዋሳ እና ሲሊዶ ሰቡሃራራ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሰሜን ኪቩ ክልል ዋና ከተማ የሆነችው ጎማ 1.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የሚኖሩባት ሲሆን፤ ለሰው ልጆች የሚሆን ንጹህ ውሀ የላትም፡፡

ከተማይቱ በእርግጥ ከ1,000 ስኩዌር ማይልስ በላይ ስፋት ካለውና ከአፍሪካ ታላላቅ ሀይቆች አንደኛው ከሆነው ከኪቩ ሀይቅ ድንበር ትጋራለች፡፡ ነገር ግን ሀይቁ ለሰው ልጅ የማይሆን በከፍተኛ ደረጃ ጨዋማ ነው፡፡ በአካባቢው ደግሞ የተፈጥሮ የውሀ ምንጭ የሚሆኑ ገባር ወንዞች የሉም፡፡

በመሆኑም የጎማ ህዝብ ለበርካታ ዘመናት ከትንሽዋ ጎረቤት ሀገር ከርዋንዳ በድንበር በኩል በሚሻገርለት ውሀ ላይ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ርዋንዳዎች እና ኮንጎዎች ለእለት ፍጆታ የሚሆናቸውን ውሀ በብስክሌት እና ሞተር ብስክሌት እንዲሁም በከጭነት መኪኖች ማመላለስ ይችሉ ነበር፡፡ ሩባቩ ላይ በማንኛውም ቀን ወደ ጎማ ከተማ የሚጓዙ ጀሪካኖችን ማየት የተለመደ ነበር፡፡

በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው የፖለቲካ ግንኙነት ብዙ ጊዜ ጤናማ ባይሆንም፤ የውሀ ፍሰቱ እና ቢዝነስ ግን በተለመደው መንገድ ይቀጥላል፡፡

በሩዋንዳ የተፈጸመው የ1994 የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የውሀ ግብይቱን አላቆመውም፡፡ በ2000ዎቹ ላይ ምስራቃዊ ኮንጎ ጦርነት ውስጥ ብትገባምና የፖለቲካ ግንኙነቶች ቢላሽቁም የንግድ ስራዎች ግን አልተቋረጡም፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋት ግን የንግድ ስራዎችን አቀዛቅዟል፡፡ በዚህም የተነሳ የርዋንዳን ውሀ ለመጠጥ፣ ለመታጠቢያና ለፋብሪካዎች አቅርቦት በመጠቀም ጥገኛ የሆኑትን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጎማ ነዋሪዎችን ህይወት ስጋት ላይ ጥሏል፡፡

IMG 20200601 210002

የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በሚል በርዋንዳ መንግስት የተወሰዱ የድንበር አካባቢ ቁጥጥሮች፣ የእንቅስቃሴዎች እገዳ እና አካላዊ ርቀት ህጎች ሁሉ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውሀ በመላክ ኑሯቸውን የሚገፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና አስከትሏል፡፡

ከርዋንዳው የውሀ አገልግሎት ሰጪ ተቋም (Statistics from Rwanda’s water utility) የተገኘ አሀዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው ሁለቱ ሀገሮች የኮቪድ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ድንበራቸውን በመዝጋታቸው የተነሳ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚሔደው የውሀ መጠን በ73 በመቶ ቀንሷል፡፡

በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር ርዋንዳ የጎማ እና የሩባቩ ግዛት ጋር የሚዋሰኑ ሁለት ዋና ዋና ድንበሮቿ ላይ ክልከላ መጣል የጀመረችው፡፡ በመቀጠልም ድንበሩ እቃ ለጫኑ ተሸከርካሪዎች በስተቀር ሙሉ ለሙሉ ተዘግቷል፡፡

በርዋንዳ በሌሎች ግዛቶች የኮቪድ 19 ክልከላዎች ሲነሱ፤ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የተጣለው ክልከላ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ነው፡፡ ከኮንጎዋ ጎማ ከተማ ጋር የሚዋሰነው የሩባቩ አውራጃ እና ከኮንጎ ቡካቩ የሚዋሰነው የሩሱዚ አውራጃ ከሌሎቹ የርዋንዳ አካባቢዎችም ተዘግተዋል፡፡

የሰሜን ኪቩ ግዛት መንግስት በሚያዝያ 4 ድንበሩን ከእቃ ማመላለሻዎች በስተቀር ድንበሩን በመዝጋት ጎማን ያገለለ የሚባለው ዘዴ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የምሽት ሰአት እላፊ የተጣለ ሲሆን፤ ሱቆችና መድሀኒት ቤቶች ብቻ ናቸው በራቸውን እንዲከፍቱ የተፈቀደላቸው፡፡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በመጨመሩ የተነሳም ክልከላው ሁለት ጊዜ ተራዝሟል፡፡ ይህ ዘገባ እስኪጠናከር ድረስም በሰሜን ኪቩ 65 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ 43 ሰዎች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን፤ 5 ሞቶች ደግሞ ተመዝግቧል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዲሞክራቲክ ኮንጎ 6,000 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 861 የሚሆኑት ሲያገግሙ፤ የ135 ሰዎች ህይት አልፏል፡፡ በርዋንዳ ደግሞ 798 ሰዎች ላይ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን፤ 371 ሰዎች አገግመዋል፡፡ 2 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡

የጎማ ሲቪል ሶሳይቲ በግንቦት 19 ባወጣው መግለጫ ላይ የአካባቢው መንግስት ጎማ ከተማ ላይ ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ አለማድረጉን አድንቋል፡፡ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ብትዘጋ ኢኮኖሚዋ እገዳውን መቋቋም ስለማይችል ለከፍተኛ ችግር ትጋለጥ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡

ነገር ግን አዋሳኝ ድንበሮች በመዘጋታቸው የተነሳ የከተማዋ ዋንኛ የንጹህ ውሀ ምንጭ ተዘግቷል፡፡

ከውሀ ችግሩ ጀርባ ያለው ሳይንስ

የጎማ ከተማ ህዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታሪኩ ከፍተኛ የውሀ ችግር በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ በአካባቢው ምን አይነት የተፋሰስ ውሀ የለም፡፡ ጎማ ሰፊውን የኪቪ ድንበር ላይ ብትሆንም፤ የሐይቁ ውሀ ግን ለመጠጥ የሚሆን አይደለም፡፡ የአሜሪካን ጆኦፊዚካል ዩኒየን በ2007 ባሳተመው ጥናት ላይ እንደተገለጸው የኪቩ ሐይቅ ከስሪቱ አንስቶ ውሀው በከፍተኛ ደረጃ ጨዋማ ነው፡፡ በ2002 የንይራጎንጎ እሳተ ጎመራ መከሰት ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ አስከፊ አድርጎታል፡፡

ከኪቩ ሐይቁ የሚወጣው ውሀ ለሰው ልጅ ፈጽሞ እንደማይሆን ጎማ ውስጥ የሚታወቅ እውነት ነው፡፡ ይህንን እውነታ ማንኛውም አዋቂ ሰው ይናገረዋል፡፡ ነገር ግን ነዋሪዎቹ ምንም አይነት አማራጭ የላቸውም፡፡ አቅም ያላቸው ከርዋንዳ የሚመጣውን ውሀ በመግዛት ለመጠጥና ምግብ ማብሰያነት ይጠቀሙበታል፡፡ የኪቩ ሐይቅ ውሀን ደግሞ ለልብስ ማጠቢያነት እና ለሌሎች አገልግሎቶች ያውሉታል፡፡ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የ2017-2018 ዩኒሴፍ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ጎማ የምትገኝበት በኪቩ ግዛት ነዋሪዎች 56 በመቶ የሚሆኑት ኢ. ኮሊ ለተባለው የውሀ ውስጥ ባክቴሪያ የመያዝ እድላቸው መካከለኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ የዚህ ትርጉም ውሀው ለመጠጥ የሚሆን አይደለም፡፡

የርዋንዳ ብሔራዊ የውሀ አቅራቢ ተቋም ከሆነው የውሀ እና ንጽህና አጠባበቅ ኮርፖሬሽን በተገኘ መረጃ መሰረት በ2020 መጀመሪያ ላይ በእያንዳንዱ ወር ቢያንስ 2,100 ኪውቢክ ሜትር ወይም 21 ሚሊዮን ሊትር ውሀ በመላው ጎማ ይሰራጫል፡፡ ይህም ማለት በእየለቱ እስከ 80,000 ሊትር ውሀ ወደ ኮንጎ ይሻገራል፡፡

ይህ የውሀ መጠን ታዲያ በይፋ የሚታወቀው ነው፡፡ ይሁንና በኮንጎ በኩል ድንበር ላይ ያሉ ነዋሪዎች በዚያኛው በርዋንዳ ድንበር በኩል ከሚኖሩ ወዳጆቻቸው አማካኝነት የመጠጥ ውሀ ያገኛሉ፡፡ በመሆኑም የሚያልው ውሀ መጠን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ በሰሜን ሩባቩ ከተማ የራቁ ወደ ቪሩንጋ ተራሮች በኩል ያሉ የገጠር አካባቢዎች ውሀቸውን በሌላኛው ድንበር ካሉ ከኮንጎዎች ጋር ይጋራሉ፡፡ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምንም እንኳ የተለያየ ሀገር ዜጎች ቢሆኑም እንደ ጎረቤታማቾች የሚኖሩ በመሆናቸው የውሀ ፍሰቱ መደበኛ አይደለም፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜናዊ ኪቩ አውራጃ 5 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች የታሸገ ውሀን ከጭነት መኪኖች ወይም ከሱቆች የሚያገኙ ህዝቦች ያሉበት ብቸኛው አካባቢ እንደሆነ ዩኒሴፍ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች ብዛት ስንት እንደሆኑ የሚገልጽ መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን በግምታዊ መረጃዎች መሰረት ከመቶዎች እስከ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሆናሉ፡፡ ወደ 350 የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች በርዋንዳው  Coopérative de Transporteurs Transfrontaliers de Rubavu (COTTRARU) ውስጥ በልዩ ሁኔታ የተሰራ በተሸከርካሪ ወንበር አማካኝነት ውሀን ጨምሮ እቃዎችን ወደ ድንበር ያጓጉዛሉ፡፡ ጥሩ የገንዘብ አቅም ያላቸው ውሀ ለማጓጓዝ እቃ ጫኝ መኪኖችን ገዝተዋል፡፡ ስራው በጣም አዋጪ ነው፡፡ ስራ የሌላቸው ወጣቶች በአንድ ጊዜ ስምንት የ20 ሊትር ጀሪካኖችን የሚያጓጉዙበት ብስክሌቶችን ለመግዛት ነው የሚጣደፉት፡፡

ይሁንና ታዲያ ይህ እያደገ የመጣው የውሀ ንግድ በኮቪድ 19 መከሰት የተነሳ ተቀዛቅዟል፡፡ በመጋቢት ወር የኪጋሊ ማዕከላዊ መንግስት ሁሉም ርዋንዳውያን በቤታቸው እንዲቆዩ ጠይቋል፡፡ የወረርሽኙ ውጤት የፖሊሲ ለውጥ እንዲኖር አስገድዷል፡፡

የሩባቩ አውራጃ ከንቲባ ሀብያሪማና ጊልበርት እና የአካባቢው የውሀ እና ንጽህና አጠባበቅ ኮርፖሬሽን ቢሮ ውስን ቁጥር ያላቸው ሰዎች ውሀ የማቅረብ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ለመፍቀድ ተስማምተዋል፡፡ ይሁንና ሁሉም ቢሆኑ በህብረት ድርጅቶች የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህ ዘገባ እየተጠናከረበት ድረስ የነበሩት ኮታማሩ እና ጊሩቡዚማ የተባሉ ሁለት የርዋንዳ የህብረት ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ በውስጣቸውም ከ20 በላይ አባላት ያሏቸው ሲሆን፤ ሁሉም ርዋንዳውያን ናቸው፡፡ አባላቱ ቀደም ሲል በራሳቸው ብቻ ይንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን በአንድ ላይ ለመስራት ተገደዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮንጎዎች በግል የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ሆነው ወደ ርዋንዳ መምጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ነገር ግን በየእለቱ የሚመጡት ቁጥራቸው ከአምስት በታች ነው፡፡ ከኮቪድ 19 በፊት ግን በመቶዎች የሚቆጠር ነበር፡፡ እነዚህ ኮንጎዎች አሁንም ድረስ በጭነት መኪና የሚሰሩ በመሆናቸው ውሀን በብዛት ለመግዛት አስችሏቸዋል፡፡

Umukozi wa Girubuzima ubwo yaraje gusoresha imodoka za Goma zaje kuvoma

እንደ ርዋንዳ ውሀና ንጽህና አጠባበቅ ኮርፖሬሽን ቢሮ እና እና የአካባቢው ባስልጣናት ከሆነ የህብረት ድርጅቶቹ ስራ በድንበር የሚሻገሩ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ያስችላሉ፡፡ በዚህም አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ ህግ ይከበራል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በየእለቱ በማንኛውም ሰአት የውሀ ጀሪካኖችን የያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበር ያሻገሩ ነበር፡፡ ገደብ ባይጣል ኖሮ የኮሮና የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ለሁለቱም ሀገሮች አስቸጋሪ ይሆን ነበር፡፡

ይሁንና እነዚህ እርምጃዎች በርዋንዳ ብቻ ኑሮን የሚያዳክሙ ሳይሆን በጎማ የሚገኙ ሰዎችንም በአጠቃላይ ለውሀ ቀውስ የዳረገ ሆኗል፡፡

በሚያዝያ ወር ላይ ወደ ጎማ ውሀ የሚሔደው ውሀ በአብዛኛው የሚገኝበት ጣቢያ ያለው የውሀ መጠን 300 ኪውቢክ ሜትር ወይም 300,000 ሊትር ነበር፡፡ ይህም በድንበር በኩል ከሚሔደው ውሀ 85 በመቶ የቀነሰ ነው፡፡ እንደ ውሀና ንጽህና አጠባበቅ ኮርፖሬሽን WASAC data.መረጃ ከሆነ በግንቦት ወር ደግሞ 500 ኪውቢክ ሜትር ውሀ በድንበር በኩል እየተጓዘ ነበር፡፡ በመጋቢት ወር ቀንሶ ከነበረው መጠን 70 በመቶ ያህል የሚበልጥ ነው፡፡

የውሀ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የተነሳም የተነሳም በጎማ የውሀ ዋጋ ለአብዛኛው የኮንጎ ዜጋ የሚቀመስ አልሆነም፡፡ ከኮሮና ወረርሽን በፊት የውሀ አጓጓዦች 20 ሊትር ጀሪካን ውሀን በ150 የርዋንዳ ፍራንክ (0.07 ዶላር) ከጣቢያው (በሩዋንዳ) ይገዙ ነበር፡፡ ተመሳሳይ መጠን ያለው ጀሪካን ጎማ ላይ ከ150 እስከ 650 የርዋንዳ ፍራንክ (0.16-0.68 ዶላር) ይደርሳል፡፡ ዋጋው እንደ አካባቢው ይለያያል፡፡

IMG 20200601 210104 1

አሁን ላይ ርዋንዳ ውስጥ የሚሸጠው የጀሪካን ውሀ ዋጋ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይሁንና ጎማ ላይ ከርዋንዳ የሚመጣ የጀሪካን ውሀ ዋጋ 2,000 የኮንጎ ፍራንክ ወይም 1,000 የርዋንዳ ፍራንክ (1.07ዶላር) ደርሷል፡፡ ይህም ከቀድሞው ዋጋ አምስት እጥፍ ማለት ነው፡፡ የርዋንዳ የጀሪካን ውሀ ዋጋ ጎማ ላይ የማይቀመስ ሆኗል፡፡ ዋጋው በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታዊች ላይ ለሚገኘው ለአብዛኛው የኮንጎ ህዝብ የሚቻል አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት ውሀ ወደ ጎማ እንዲያጓጉዙ ፈቃድ ያገኙት ሁለቱ የህብረት ድርጅቶች እንዳስታወቁት ከሆነ ወደ ድንበር አካባቢ ከሚሔደው ውሀ በቅድሚያ የሚሰጠው ድንበር ላይ ለሚገኙ ፋብሪካዎች ነው፡፡ ለአብነት ያህልም የማዕድን ውሀ የሚያመርቱ እና ወይን የሚጠምቁ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ወደ ጎማ ከተማ ቢሬሬ ገበያ የሚወሰደው ጥቁት ጀሪካን ብቻ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ነው አቅም ያላቸው ሰዎች ውዱን የጀሪካን ውሀ ለቤታቸው የሚገዙት፡፡ ቀሪው ህዝብ  ግን ችግሩን በራሱ እንዲወጣው ተትቷል፡፡

አሁን ላይ ቀጠናው ትግሉ ከ20 አመት በላይ ከዘለቀው ጦርነት ለማገገም ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሌላም ሰዎች መጠለያ ፍለጋ መንደራቸውን የለቀቁ 500,000 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በጎማ ዙሪያ ይገኛሉ፡፡ ከ2018 ጀምሮ ዲሞክራክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምስራቃዊ ኢቱሪ አካባቢዎች፣ በደቡብ ኪቩ እና ጎማ በምትገኝበት ሰሜናዊ ኪቩ የኢቦላ ወረርሽን በመታገል ላይ ናት፡፡ በእርግጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ከአጠቃላይ 3,470 ሰዎች አራት ብቻ በጎማ እና ንይራጎንጎ ግዛቶች የተገኙ ናቸው፡፡

IMG 20200602 WA0005 1

ጆን ምቡይ አምስት ልጆች የሚገኙበት ቤተሰብ አለው፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው የውሀ ዋጋ እጅጉን አሳስቦታል፡፡ “የቧንቧ ውሀ በአንጻራዊነት ቅናሽ ነው፡፡ ነገር ግን ጣዕሙ ጨዋማ እና ህጻናት ሊጠጡት የማይቸሉት ነው” ይላል፡፡ ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት ጎማ በጣም ሞቃታማ በመሆኗ ለመጠጥ የሚሆን 20 ሊትር ጀሪካን ውሀ በየሶስት ቀኑ በ1,200 ፍራንክ ይገዛ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን 2,000 ፍራንክ ነው የሚከፍለው፡፡

ለብዙ አጎራባቾች ውሀ የሚያቀርቡ የውሀ ጣቢያዎች አሉ፡፡ የኮንጎ ውሀ አቅራቢ ተቋም ውሀ በሚገኝበት አካባቢ የህዝብ የቧንቧ ውሀ ጣቢያዎችን ሰርቷል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ታዲያ በየእለቱ በማንኛውም ሰአት የጀሪካን ሰልፎች ይኖራሉ፡፡ 20 ሊትር የውሀ ጀሪካን በ200 ፍራንክ ይገኛል፡፡

በዩኒሴፍ የ2017-2018 መረጃ መሰረት በሰሜን ኪቩ 44 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ውሀ ለማግኘት ከ30 ደቂቃ በላይ የእግር ጉዞ ያደርጋል፡፡ 20 በመቶ ያህሉ ውሀ ለመቅዳት ከሁለት እስከ ሶስት ሰአታት ያሳልፋል፡፡

የኮንጎው ጁማ ሙሲንዱ ስድስት አባላት ቤተሰብ አለው፡፡ ለእሱና ቤተሰቡ ውሀ ከርዋንዳ ማምጣት ከዋጋም ሆነ ከርቀቱ አንጻር የማይቻል ነው፡፡

“ከርዋንዳ የሚመጣውን ውሀ የዋጋውን ጉዳይ እንኳ እንተወውና በሙጃ የምንገኝም ሆንን እኔ የማውቃቸው በኪቡምባ እና ሙጉንጋ የሚገኙ ሰዎች ከኪቩ ሐይቅ በጣም ርቀን ነው የምንገኘው” ይላል፡፡ በእነዚህ አካበቢዎች ያሉ ሰዎች ሐይቁ ጋ ለመድረስ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር መጓዝ አለባቸው፡፡ ወይም ደግሞ የህዝብ የቧንቧ ውሀ ተራቸው እስኪደርስ ድረስ ምሽቶችን ተሰልፈው ማሳለፍ አለባቸው፡፡

ጥቂት የውሀ ሻጮች ግን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የውሀ ዋጋ በመጨመሩ አትራፊ መሆን ችለዋል፡፡

ብሪጊቴ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፤ በካቶይ አጎራባች ከርዋንዳ የሚመጣ ውሀን በመሸጥ ስራ ላይ ነው የተሰማራችው፡፡ “ዘወትር ሰኞ የውሀ አቅራቢዎቹ ባለ 20 ሊትሩን 20 ጀሪካን ውሀ ያመጡልኛል፡፡ እኔም በትንንሽ እቃ እየቀናነስኩ በአራት ቀን ሸጬ እጨርሳለሁ፡፡ ዋጋው እየጨመረ ነው የሔደው፡፡ ለእኔ ጥሩ ትርፍ አስገኝቶልኛል፡፡ ውሀ በመሸጥ ስራ ከማገኘው ገቢ ነው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ልጆቼን የማስተምረው” ትላለች፡፡

በብሪጊቴ የውሀ ሱቅ ውስጥ ያገኘነው ሌላኛው የርዋንዳ ውሀ ሻጩ ጁለስ፤ 20 ሊትር ጀሪካን ውሀ በ1,200 ፍራንክ ገዝቶ ወደ ትናንሽ የውሀ እቃዎች በማቀናነስ 2,000 ፍራንክ እንደሚሸጠው ነግሮናል፡፡

በጎማ የውሀ እጦት ታሪክ

የርዋንዳን ውሀ ወደ ጎማ የማጓጓዙ ታሪክ የሚጀምረው በ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡ ቅኝ ገዢዎቹ ቤልጂየሞች በጎማ የውሀ ችግር መፍትሔ ፍለጋ Fonds du Bien-être Indigène የተባለውን ተቋም ይመሰርታሉ፡፡ በ1947 የጎማ ህዝብ ብዛት ቁጥር 20,000 እንደነበር ነው ቅኝ ገዢዎቹ ያስቀመጡት መረጃ የሚያሳየው፡፡

IMG 20200602 WA0004

በ1993 በርዋንዳ፣ ብሩንዲ እና ያኔ ዛየር አሁን ዲሞክራቲክ ኮንጎ (ሁሉም የቤልጂየም ቅኝ ተገዢዎች ናቸው) ውስጥ ውሀና የኤሌትሪክ ሀይልን ለማቅረብ ሬጊዴሶ (Regie de Distributrion d’Eau et d’ Electricité du Congo Belge et du Ruanda- Urundi) የህዝብ ተቋም ሆኖ ተመሰረተ፡፡

በ1957 ለተከፈተው BRALIRWA, ለተባለው ለቢራ እና ለስላሳ መጠጦች አምራች በርዋንዳ ጊሴንይ በሴቤያ ወንዝ ላይ አነስተኛ የውሀ ማጣሪያ ጣቢያ ተገንብቶ ነበር፡፡ ከዚያው የውሀ ማጣሪያ ጣቢያ በጎማ ለሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እና አነስተኛ ፋብሪካዎችም ውሀ ይሰራጭ ነበር፡፡ አሁን ድረስ የውሀ ጣቢያው የደበዘዙ ምልክቶች ይታያሉ፡፡

በመስከረም ወር 1976 ላይ ቤልጂየም ነጻ ሀገሮች የሆኑትን ርዋንዳ፣ ብሩንዲ እና ዛየር የታላቅ ሐይቅ ሀገሮች ህዝብ የጋራ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ Economic Community of the Great Lakes Countries (CEPGL) እንዲያቋቁሙ አደረገች፡፡ ከዚህ ህብረት ሀሳቦች መካከል አንደኛው በጎማ ያለውን የውሀ ችግር የረጅም ጊዜ የሚቆይ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ መፍትሔውም በርዋንዳ ጊሴኒይ ያሉ ወንዞችን መጠቀም ነበር፡፡

በ1986 በሴቤያ ወንዝ ላይ ትልቅ የውሀ ማጣሪያ እንዲሁም ጊሂራ 1 የተባለ ሀይድሮኤሌትሪክ ግድብ ተገነባ፡፡ የውሀ ጣቢያው በዋናነት ለቢራና ለስላሳ መጠጦች አምራቹ ኩባንያ BRALIRWA የተገነባ ነው፡፡ ግን ደግሞ ወደ ጎማ ውሀ ለመላክ መልካም እድልንም ፈጥሯል፡፡ የጊሂራ ግድብ በሚገነባበት ወቅት ሁለት ባለ 200ሚሜ ዲያሜትር ቱቦዎች ተዘርግተው ነበር፡፡ አንደኛው አሁንም ድረስ የሚገኘውና ከሁለቱም ድንበሮች በኩል ወደ ጎማ የሚገባው ነው፡፡

ይሁንና በቤልጂየም አማካኝነት የተመሰረተው አካባቢያዊ ህብረቱ ዘላቂ ሊሆን አልቻለም፡፡ በ1991 የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሀብያሪማና ወደ ጎማ ውሀ የሚወስዱ መስመሮች እንዲቋረጡ አደረጉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የኮንጎው የውሀ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ክፍያ አለመፈጸሙ ነው፡፡

በጥር ወር 2002 በንይራጎንጎ ተራራ ላይ የተከሰተው እሳተ ገሞራ ደግሞ የጎማን በርካታ መሰረተ ልማቶች አወደመ፡፡ የውሀ ቧንቧዎችም ጭምር ጠፉ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ በ1996 በመላው ምስራቃዊ ኮንጎ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ ርዋንዳ ደግሞ ከቀድሞ የመንግስት ወታደሮችና በ1994 በቱትሲዎች ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ከፈጸሙ የጥፋት ኃይሎች ጋር እየተፋለመች ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በጎማ እና በሌሎች አካባቢዎች ጸረ- ርዋንዳ ምላሾች መፈንዳት ጀመሩ፡፡

ለጎማ ተብሎ የሚወጣ ውሀም ቀረ፡፡ በ2004 ኤሌክትሮጋዝ (አሁን የውሀና ንጽህና አጠባበቅ ኮርፖሬሽን) እነዚያን ወደ ከርዋንዳ ውሀ የሚያስተላልፉ ቱቦች ጨርሶ እንዲወገዱ አደረገ፡፡ የቱቦዎች መስመር በጊሴንይ ከተማ በመኖሪያ ቤቶች፣ በጎዳናዎች እና በኮረኮንች መንገዶች ላይ ይታያል፡፡

ነገር ግን አሁንም ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮንጎዎች በየእለቱ ውሀ ፍለጋ ወደ ርዋንዳ እንደሚያመሩ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የርዋንዳውን የውሀ ተቋምን በሐላፊነት ይመሩ የነበሩ ግለሰብ ነግረውናል፡፡ የርዋንዳ መንግስት በሀገር አቀፍ የውሀ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት መሰረት የሜታሊክ ቱቦዎቹን በከባድ የፕላስቲክ ቱቦዎች ቀይሯቸዋል፡፡ እነዚህ ውሀ አስተላላፊዎች ውሀን ከሁለቱ ድንበሮች አካባቢ ወዳሉት ሁለት የውሀ ጣቢያዎች በአንደኛው ያስተላልፋሉ፡፡

መረጃ ሰጪያችን እንደነገሩን ከሆነ ኮንጎዎች በብዛት ወደ ርዋንዳ የሚሻገሩበት ምክንያት አልነበረም፡፡ ይሁንና በ2013 የርዋንዳ መንግስት በድንበር አካባቢ ውሀ የማውጣቱን ስራ ሙሉ ለሙሉ ያቆመ ሲሆን፤ የውሀ ጣቢያዎቹንም ዘግቷቸዋል፡፡ በወቅቱ በኪጋሊና ኪንሻሳ መካከል የነበረው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርቶች ላይ ርዋንዳ በምስራቃዊ ኮንጎ ታጣቂዎችን በመደገፍ ጦርነት እንዲነሳ ማድረጓን በመግለጽ በተደጋጋሚ ከሳለች፡፡

Imodoka mbere yo kwinjira mu Rwanda ibanza gusuzumwa no guterwa imiti yica Virusi za Corona virus

ይህም ኾኖ ታዲያ ኮንጎዎች ውሀ ፍለጋ ወደ ርዋንዳ መምጣታቸውን አላቋረጡም፡፡ ይህ ሁኔታም ግለሰቦች በጭነት መኪኖች፣ በሞተር ብስክሌቶች፣ በብስክሌቶች እና በአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪዎች ውሀ የማመላለስ ስራ ላይ እንዲጨምር አድርጓል፡፡

የኮንጎ የውሀ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ውሀን ከኪቩ ሐይቅ ውሀን የሚያወጣ ጣቢያ ጎማ ውስጥ አለው፡፡ ይሁንና ውሀ ከርዋንዳ በማምጣት በጅምላ የሚሸጡ የኮንጎ ነጋዴዎች እንደሚገልጹት ጎማ ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች የርዋንዳ ውሀን ነው የሚመርጡት፡፡ ከርዋንዳ ውሀ እንዲያጓጉዙ ከተፈቀደላቸው ኮንጎዎች አንዱ ጎማ ውስጥ የማዕድን ውሀ በማሸግ በሚያቀርበው ኪሊማንጃሎ ፋብሪካ ውስጥ ይሰራል፡፡ ፋብሪካው የርዋንዳን ውሀ የሚመርጠው የማጣራት ሒደቱ አነስተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የኪቩ ሐይቅ ውሀ የጨውን ልየታ ስራን ጨምሮ የማጣራት ሒደቱ ውስብስብ ነው፡፡

በውሀ ችግር የተጎዱ የጎማ ድኾችን ለመታደግ አለምአቀፍ ተቋማት የሀገርአቀፉን አገልግሎት ሰጪ ተቋምን ጥረት ለማገዝ እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡ አለምአቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ International Committee of the Red Cross (ICRC) ጎማ ውስጥ ለሁለት አስርት አመታት የውሀ አቅርቦት አስተዳደር ላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የቅርብ ጊዜውን ብንመለከት እንኳ በ2014 በጎማ ከተማ የውሀ ክፍፍል ትስስርን ለማሻሻል የተጀመረው ስራ በተለይም ሁለት አሳሲስ የውሀ ማውጫ ጣቢያዎችን በመክፈት አሁንም እየተሰራበት ነው፡፡ ስራው ለ500,000 የጎማ ነዋሪዎችን የሚያገለግል መሆኑም ተነግሮለታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአለምአቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በዋሊካሌ፣ ማሲሲ እና በሰሜን ኪቩ ግዛት በበሩሹሩ ግዛቶች ውስጥ በገጠር አካባቢዎች ለሚኖሩ ከ85,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የውሀ አቅርቦት ፕሮግራሞች አሉት፡፡

እነዚህ ፕሮግራሞች ከርዋንዳ ከሚመጣው ውሀ ጋር ተዳምሮ ጎማ ከሌሎች የሴንትራል አፍሪካ ሀገሮች የበለጠ ንጹህ ውሀ የማግኘት እድሏ እንዲጨምር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይታመናል፡፡ በዩኒሴፍ በኩል በተገኘ መረጃ መሰረት በ2108 በዲሞክራቲክ ኮንጎዋ ሰሜን ኪቩ ክልል የሚገኙ 68.5 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች የተሻሻለ ውሀ የማግኘት እድል አላቸው፡፡ ይህም ከሀገሪቱ 26 ክፍለ ግዛቶች ከ20ዎቹ የበለጠ ነው፡፡

በ2017 በምዕራባዊ ርዋንዳ ጊሴንይን ጨምሮ ወደ 83 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የተሻሻለ ውሀ እንደሚጠቀም ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ አብዛኞቹም ንጽህናው የተጠበቀ ምንጭ ወይም የህዝብ ቧንቧን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን የርዋንዳ አምስቱም ክልሎች የተሻሻለ ውሀ አቅርቦትን ከ70 በመቶ በላይ ማሳደግ ሲችሉ፤ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አብዛኞቹ አውራጃዎች ከ50 በመቶ በታች የሚሆኑት ነዋሪዎች ብቻ ናቸው ንጹህ ውሀ የሚያገኙት፡፡

ውዱ የውሀ ንግድ

በጎማ ህዝቦች ላይ የተከሰቱት ውስጥ እነዚህ ሁሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፈተናዎች እያሉም ታዲያ ኮንጎዎች ከርዋንዳዋ ሩባቩ ውሀ መፈለጋቸው እንደቀጠሉ ነው፡፡ ይህ ሁኔታም በአካባቢው የውሀ አቅርቦት ላይ ጫና አስከትሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሩባቩ የጊሂራ 1 የውሀ ጣቢያ የሚያመርተው 8,000 ኪውቢክ ሜትር ውሀ በርዋንዳው የቢራና ለስላሳ መጠጦች አምራች ፋብሪካ እና ለጊሴኔይ እንዲሁም ለጎማ ከተሞች ይከፋፈላል፡፡

በ2012 በርዋንዳ በተሰራ ሀገርአቀፍ የህዝብ ቆጠራ መሰረት የሩባቩ አውራጃ 430,000 ነዋሪዎች ነበሩት፡፡ ቁጥሩ አሁን ላይ ሊጨምር ይችላል፡፡ የጊሂራ 1 ጣቢያ ተጨማሪ 2,00 ኪውቢክ ሜትር ውሀ እንዲያመርት ለማስቻል የርዋንዳው የውሀ አቅራቢ ተቋም የማስፋፋት ስራ እየሰራ ነው፡፡ ሌላ ሁለተኛ የጊሂራ 2 ጣቢያም በየወሩ 15,000 ኪውቢክ ሜትር ውሀን እንዲያመርት በመገንባት ላይ ነው፡፡ ይህም መንግስት 300 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ በ2024 ንጹህ የመጠጥ ውሀ ሽፋንን መቶ በመቶ ለማድረስ የያዘው እቅድ አካል ነው፡፡

እስከዚያው ድረስ ግን በጎረቤታማቾቹ ሩባቩ እና ጎማ ከተሞች የውሀ ዋጋ ጣሪያ እንደነካ ይቆያል፡፡ ወደ ጎማ የሚሔደው መጠኑ የቀነሰው ውሀ 500 ኪውቢክ ሜትር ከመቼውም ጊዜ በላይ ውድ ሆኗል፡፡

ውሀ ወደ ጎማ ለመውሰድ ከተፈቀደላቸው ከኮንጎ ነጋዴዎች መካከል አንዱ የሆነው ካሴሬካ ማካዚ ከኮቪድ 19 በኋላ ያለውን የውሀ ክፍያ መጠን ልዩነት ነግሮናል፡፡ ማካዚ በእያንዳንዱ ጉዞ 5,000 ሊትር ውሀ ያመጣል፡፡ ይሁንና ለርዋንዳዎቹ የህብረት ድርጅቶች 22,960 የርዋንዳ ፍራንክ በጥሬው መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ለአንድ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን ለርዋንዳ የውሀና ንጽህና አጠባበቅ ኮርፖሬሽን በባንክ ከሚከፍለው 73 የርዋንዳ ፍራንክ (0.08 ዶላር) በተጨማሪ ማለት ነው፡፡

umuturage wa Goma aza kuvoma amazi ku mugezi rusange mu Rwanda

 “ይህ መክፈል ያለብኝ አዲሱ ዋጋ መጠን ነው፡፡ ገንዘቡ ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እስከአሁኗ ቅጽበት ድረስ ይህን ያህል ዋጋ ለምን እንደምከፍል አላውቅም” ይላል ማካዚ፡፡ “ከርዋንዳዎቹ የህብረት ድርጅቶች ምንም አይነት አገልግሎት ሳናገኝ ለምንድነው የምንከፍላቸው?” ሲልም ይጠይቃል፡፡

ከአዲሱ ክፍያ በተጨማሪ የኮንጎ የጭነት መኪኖች በርዋንዳ ግዛት ውስጥ ባልተለመደ ጥብቅ ሁኔታዎች ውስጥም በመስራት ላይ ናቸው፡፡ የኮቪድ 19 መመሪያዎች መሰረት ከባድ መኪኖች በርዋንዳ ከድንበር ወደ ውሀ ጣቢያ ሲሔዱ እና ሲመለሱም ርዋንዳ ውስጥ በየትኛውም ቦታ መቆም አይችሉም፡፡

የርዋንዳው ህብረት ድርጅት የጊሩቡዚማ ዋና ኃላፊ የሆኑት ሙናይትዋሪ ሞሀመድ እንደሚናገሩት የኮንጎዎቹ ነጋዴዎች ገንዘብ የሚከፍሏቸው ውሀ ከርዋንዳ እንዲወስዱ ሁኔታዎችን ስለሚያመቻቹላቸው ነው፡፡

ሙሪንዳቢገዊ ጊልበርት የርዋንዳ ውሀና ንጽኅና አጠባበቅ ኮርፖሬሽን የቀጠና ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤ ድንበር ተሻግረው ውሀ እንዲያቀርቡ ሁለት የህብረት ድርጅቶች ብቻ ፍቃድ እንዲያገኙ መወሰኑ ከተቋማቸው ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ነው የሚናገሩት፡፡

“ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነቱ የአካባቢው ክልል ነው፡፡ የኛ ስራ ፈቃድ ላላቸው ውሀ መሸጥ ነው፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እንዲቻል አሁን ላይ ያሉት ሁለቱ የህብረት ድርጅቶች ብቻ ናቸው” ብለዋል፡፡

ይህ ዘገባ የተጠናከረው ከኢንፎናይል ጋር በመተባበር ከኮድ ፎር አፍሪካ እገዛ እና ከፑልቲዘር ሴንተር ኤንድ ናሽናል ጂኦግራክ ሶሳይቲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ነው፡፡ ተጨማሪ ዘገባ እና አርትኦት በአኒካ ማክጊኒስ

ኮቪድ 19 ያስከተለው የውሀ ችግር በዲሞክራቲክ ኮንጎ

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts