በጆርጅ አቺያ
ኬንፍሬይ ካቱይ በ26 አመቱ ትምህርቱን ከሞይ ዩኒቨርስቲ በ2010 ሲያጠናቅቅ የሚያውቀው ነገር ቢኖር በዩኒቨርስቲ ካጠናው ተቃራኒ በሆነ የሙያ ዘርፍ ላይ እንደሚሰማራ ነበር፡፡
እንደ ማህበረሰብ ሳይንስ ባለሞያ ኬንፍሬይ፤ በዩኒቨርስቲ ያገኘውን ክህሎትና እውቀት እንዴት ወደ ተግባር እንደሚለውጠው በማሰብ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በፍላጎቱ መርጦ ያጠናው የትምህርት ዘርፍ ባለመሆኑና በዘርፉ ውስን የስራ እድል መኖሩ ነው፡፡
“የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ዩኒቨርስቲ ሳመለክት ከሒሳብ ስራ ጋር ተያያዥ የሆኑ ኮርሶችን ለማጥናት ነበር የፈለኩት፡፡ የማህበረሰብ ሳይንስ የመጨረሻ ምርጫዬ ነበር፡፡ ለበጎ ይሁን አይሁን እንጃ የተቀበሉኝ እሱን ነበር” በማለት አጋጣሚውን በተለየ ሁኔታ ያስታውሳል፡፡
በእግርጥ ይህ በኬንፍሬይ ላይ ብቻ የተከሰተ ታሪክ አይደለም፡፡ ምስጋና ተማሪዎችን በዘፈቀደ ለሚመድበው ለኬንያ ዩኒቨርስቲዎች ጥምር የቅበላ ቦርድ ይሁንና አብዛኛዎቹ የኬንያ ተማሪዎች ራሳቸውን የሚያገኙት ያላመለከቱትን የትምህርት ዘርፍ ሲያጠኑ ነው፡፡
ነገር ግን የእሱ ወሳኝ ለውጥ የተፈጠረው ከካምፓስ ህይወት በኋላ ምን ለመስራት እንደሚችል ሲያስብ ነበር፡፡ ይህ በእርግጥ ለእሱ የሚገርም አይደለም፡፡
“እያደኩ በመጣሁ ቁጥር በዙሪያዬ የሚገኙ ደኖች እየጠፉ መምጣታቸውን፣ የመሬት ውበትም እየቀነሰ መገኘቱን እና በዚህም የተነሳ የልጆቻችን የወደፊት እጣ ከፍተኛ ስጋት እንደገጠመው መረዳት ቻልኩ” በማለት የሚናገረው ኬንፍሬይ፤ “በልጅነቴ በጣም የምወዳቸው የጫካ ፍራፍሬዎችም በፍጥነት ጠፉ፤ አየራችንም በየቀኑ በጣም ቁሻሻ እየሆነ መጣ፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ሌላው ቀርቶ ጥላ እንኳ እንደሚኖረው እርግጠኛ አይደለሁም” ይላል፡፡
ይህ ደግሞ ለእሱ በፍጥነት ሊሰራ የሚገባው አንገብጋቢ ጉዳይ ነበር፡፡
ከዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ የሚኖርበት ማህበረሰብ ዙሪያ ወቅታዊ የአካባቢ ሁኔታ ሰፊ ጉዳት ደርሶበት እና የተፈጥሮ አካባቢዊ ሁኔታን ከአደጋ ለመጠበቅና መልሶ ለማልማት እና የህብረተሰቡን ለድህነትና አየር ንብረት አደጋ የማገገም አቅምን ለማሻሻል በፍጥነት በማስፈለጉ በምህጻረ ቃል “ስኮፕ ኢንተርቬንሽን” ተብሎ የሚጠራውን (Saving and Conservation of Our Planet Earth Intervention) ድርጅት ማቋቋም እንዳስፈለገም ተናግሯል፡፡
ስኮፕ ኢንተርቬሽን የተመሰረተው አሁን የአንድ ወንድ ልጅ አባትና እድሜውም 35 አመት በሆነው ኬንፍሬይ በ2012 ነው፡፡ ደርጅቱ በወጣቶች የሚመራ ሲሆን፤ አላማውም ማህበረሰብ ተኮር የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎችን ለማጎልበት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት፣ የማህረሰቡን የአየር ንብረት ለውጥን የመታገል አቅምን ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመዋጋትና ማህበረሰቡ የእጣ ፈንታው ወሳኝ መሪ እንዲሆን ለማብቃት ነው፡፡
በኬንያ ከ47 ግዛቶች አንደኛው በሆነው በኤልጊዮ ማራክዌት ግዛት በኬሪዮ ወንዝ ከፍታና ዝቅታማ ቦታዎች ያደገ በመሆኑ ኬንፍሬይ ከፊቱ ፈታኝ ሀላፊነት እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር፡፡ ፈተናውን ለመጋፈጥም ዝግጁ ነበር፡፡
በዚያን ወቅቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በመላው አለም ታውቆ ነበር፡፡ እንደ ኬንያ ባሉ አዳጊ ሀገሮች ደግሞ ሙቀቱን መረዳት የጀመሩበት ጊዜ ነበር፡፡
እንደሌላው አካባቢ ሁሉ በኬንያም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምናልባትም በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቀስ የዘመናችን አካበቢያዊ ፈተና ነው፡፡ በስነ ምህዳሩ፣ በውሀ እና ምግብ ሀብቶች እና ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ የዚህ ጎጂ ውጤቶችንም ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እና ድርቆች መከሰት እንዲሁም አካባቢያዊ ጥፋት ጨምሮ የኬንያ የመሬት ገጽታ ራሱ ይመሰክራል፡፡
የመሬትና አካባቢ መራቆት ኬንያን ከገጠሟት ፈተናዎች መካከል አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ ሀገሪቱን በየአመቱ 390 ሚሊዮን ዶላር (38.9 ቢሊዮን ሽልንግ) ወይም ከአመታዊ ጠቅላላ ገቢዋ 3 በመቶ ያህል አመታዊ የኢኮኖሚ ጉዳት እንደሚያስከትልባት ይገመታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ በሰዎች ሰፈራ፣ በግብርና ስራዎች እና ህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተነሳም የሚፈጠረው የውሀ ማከማቻ ቦታዎች መራቆት በአካባቢ ጥበቃ ጥረቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረው፡፡
የአካባቢና አየር ንብረት ኤክስፐርቶችም እንደሚስማሙት ከሆነ፤ ደኖች እንደ ውሃ ማከማቻነትና ካርበን ማጠራቀሚያነት ማገልገልን ጨምሮ ከፍተኛ የሆነ አካባቢያዊ ጥቅሞችን ይሰጣሉ፡፡ ይህም የአየር ንብረት ለውጥን የሚታል ጥሩ መፍትሔ ነው፡፡
“የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መታወቅ የጀመረው በዝናብ ፍሰት መጠንና ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ እና የዝናብ ወቅት በድርቅ ወቅቶች የመለወጡ ነገር ተደጋግሞ መከሰት ሲጀምር ነው፡፡ ኬንያ በኢኮ-ሲስተም ላይ ቀጥተኛ ጥገኛ ስለሆነች የሀገሪቱ የውሀ ማማዎች መራቆትም በኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲሉ በናይሮቢ ዩኒቨርስቲ የአየር ንብረት ኤክስፐርትና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሼም ዋንዲጋ ያስረዳሉ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ እና የተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደር ጠቀሜታን፤ ከኢኮኖሚው ማህበረ ኢኮኖሚ ልማት በመነጠል ሊገኝ እንደማይችልም ፕሮፌሰር ዋንዲጋ አስገንዝበዋል፡፡
ኬንፍሬይ ‹‹ስኮፕ ኢንተርቬንሽን›› በሚለው የድርጅት መጠሪያ ስም በአምስት አጎራባች ግዛቶች በናኩሩ፣ ባሪንጎ፣ ኤልጌዮ ማራክዌት፣ ኡሲን ጊሹ፣ ናሮክ እና ናንዲ በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት ከተከሰቱ አካባቢያዊ ፈተናዎች መካከል የተወሰኑትን ለመድረስ ቆርጦ ተነሳ፡፡
ድርጅቱም የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል እና ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማስተዋወቅ በህብረተሰብ ደረጃ ይሰራል፡፡
“አስተማማኝና የተረጋጋች ፕላኔትን ለመገንባት የሰው ልጆችን መብቶች እና ሀላፊነቶች አሰራርን ተጠቅመናል፡፡ ይህ አሰራር የሰው ልጅ መብቶች ጥበቃና ፍትህን እያስተዋወቀ፤ ህብረተሰቡ ለአካባቢው ያለበትን ሀላፊነት እንዲረዳ የሚያደርግ ነው” ሲል ኬንፍሬይ ይናገራል፡፡
ስኮፕ ኢንተርቬንሽን ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ድርጅቱ ለአካባቢው ህብረተሰብና አዋሳኝ ለሆኑትም ጭምር የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶችን ለመዋጋት የሚረዱ የተወሰኑ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለማከናወን ችሏል፡፡
ከእነዚያ የመፍትሔ አማራጮች መካከልም በደኑ 100ሄክታር ላይ የሚተገበረው የማው ደን ምድረ ግቢን እና የውሀ ማማዎችን መልሶ ማልማት ስራ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ጥረትም የማው ደን ጨርሶ እንዳይጠፋ መታደግ ተችሏል፡፡
የማው ደን በኬንያ በትልቅነቱ የሚጠቀስ ሀገር በቀል ደን ሲሆን፤ ከ400,000 ሄክታር መሬት በላይ ይሸፍናል፡፡ ከሀገሪቱ አምስት የውሀ ማማዎች መካከልም ረጅሙ ነው፡፡ ምድረ ግቢው የላይኛውን የውሀ ማከማቻ የሰራ ሲሆን፤ ለቪክቶሪያ ሀይቅ እና ለነጩ አባይ የማከማቻ ምንጭም ነው፡፡ የማው ውሀን ይዘው በሰሜን ከቱርካና ሀይቅ በደቡብ ወደ ናትራን ሀይቅ አድርግው በመላው ምዕራባዊ ኬንያ የሚፈሱ የብዙ ወንዞች መነሻም ነው፡፡
በወንዝ ፍሰት ደንብ፣ በጎርፍ መከላከል፣ ውሀ ማጠራቀም፣ የከርሰምድር ውሀን መልሶ በማልማት፣ የአፈር መሸርሸርና ደለልን በመቀነስ፣ በውሀ ማጣራት እና ብዝሀ ህይወትን በማስተዋወቅ ረገድ ደኑ በዋጋ የማይተመን ከፍተኛ ስነ ምህዳራዊ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡
“የማው ደንን ከጥፋት ለመመለስ የኬንያ የደን አገልግሎት በሚባለው መስሪያ ቤት አማካኝነት ከኬንያ መንግስት እና ሀገር በቀሉ የደን ማህበረሰብ ማህበርን ጨምሮ ከሌሎችም የአካባቢው ቡድኖች ጋር በ100 ሄክታር የመልሶ ማልማት ስራ ለመስራት 2015 ላይ ትብብር ፈጥረናል” ሲል ኬንፍሬይ ያስረዳል፡፡
ይህ ስራም ዛፎችን መትከል እና በራሳቸው መቆም እስኪችሉ ድረስ መንከባከብን ያካተተ መሆኑንም ጨምሮ አስታውቋል፡፡
እስከ አሁን ድረስም ከ100,000 በላይ ሀገር በቀልና የውጭ ሀገር ዝርያ ያላቸው ዛፎች ችግኞችን በ100 ሄክታር መሬት ላይ መትከል ችለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ ስኮፕ ኢንተርቬንሽን በዘላቂ የደን ልማት እና የደን ጥበቃን በሚያጎለብቱ አማራጭ የስራ ዘርፎች ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ በመርዳት አካባቢው ማህበረሰብን አቅም ግንባታ ላይ ይሰራል፡፡
“ፍሩት ኤንድ ትሪ ፕሮጀክት” በአካባቢው በስኮፕ ኢንተርቬንሽን አማካኝነት የሚተገበር ሌላኛው ተስማሚ የመፍትሔ ስራ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የተቀረጸው ኑሯቸውንና አመጋገባቸውን በማሻሻል አካባቢያዊ ገጽታን ለማሻሻል ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ከሆኑ ግዛቶች አንደኛው በሆነው በባሪንጎ ወረዳ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት የሚተገበር ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የፍራፍሬ እርሻዎችን ለማቋቋም የፍራፍሬ ዛፍ ዘሮችን መለገስን እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በትምህርት ቤቶቻቸውና መኖሪያ ቤታቸው እንዲሰሩ ለማነሳሳትና ለማስተዋወቅ ወደ ትምህርት ቤት የሚሔዱ ልጆችን አቅም ማሳደግን ያካትታል፡፡
“በረጅም ጊዜ ሒደት ደግሞ የተተከሉት የፍራፍሬ ዛፎች ችግኞች የአካባቢውን ሁኔታ ለማሻሻል፣ የአረንጓዴ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ፣ ለትምህርት ቤታችን እና በዙሪያችን ለሚገኘው ማህበረሰብ ተጨማሪ የምግብ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሀገር በቀል ፍራፍሬዎችን ለማፍራት እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በሚሸጡበት ጊዜም ገቢ ያስገኛሉ” ሲሉ የተናገሩት ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ትምህርት ቤቶች አንደኛው የሆነው የሎሎቶሮክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ትግልን ለማገዝ በስኮፕ ክላይሜት ሊደርሺፕ ፕሮግራም በኩል ድርጅቱ የትምህርት ቤት ልጆችን እና ማህበረሰቡ አስፈላጊ ክህሎቶች እንዲኖራቸው ማብቃት ችሏል ሲሉም ታረስ ይናገራሉ፡፡
ይሁንና ዘግየት ብሎ ስኮፕ ኢንተርቬንሽን ከስኬት ያደናቀፉት የተወሰኑ ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር የሚናገሩት የድርጅቱ ኮሙኒኬሽን እና አድቮኬሲ ኦፊሰር ግላዲይስ ቼርዮት፤ በኬንያ የስድስት ግዛቶችን አካባቢ በመጠበቅ ተጠቃሽ እድገት ማሳየቱን ይገልጻሉ፡፡
እነዚህ ጥረቶች የዛፍ ሽፋን መጠንን ለማሳደግ እና የካርበን ዝቅጠቶችን ለማጎልበት የኬንያ መንግስት የሚከናወኑ የደን እና የደን ማልበስ ስራዎችን ለማገዝ ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡ ይህም የደን ሽፋንን በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ካለበት 7 ከመቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደሚጠይቀው አነስተኛ መስፈርት ወደ 10 በመቶ ለማሳደግ በዝግጅት ላይ ነው፡፡
እንዲህ አይነት በወጣቶች የሚመራ መፍትሔዎች በወጣቶች የሚመሩ እና ማህበረሰብ ተኮር እንቅስቃሴዎች እናቶችና ህጻናትን ጨምሮ የአካባቢው ማህረሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥረውን የአየር ንብረትን ለመዋጋት ያላቸውን አይነተኛ አስተዋጽኦ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሀገሪቱን ከአየር ንብረት ለውጥ ጎጂ ባህሪዎች ለአጭርም ሆነ ረጅም ጊዜ የሚጠብቁ መሆን መቻል ይኖርባቸዋል፡፡