ከመሬት መንሸራተት የተረፉ ህጻናት የችግኝ ተከላ ዘመቻ

ከመሬት መንሸራተት የተረፉ ህጻናት የችግኝ ተከላ ዘመቻ

በጃቪየር ሲላስ ኦማጎር

በዩጋንዳ ከመሬት መንሸራተት የተረፉ ሰዎች በሰፈሩበት በቡናምቡትዬ መንደሮች መንደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ትግል ብቻ ሳይሆን የንጹህ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ውሀ እጥረት ጋርም እየታገሉ ነው፡፡

ለችግሩ ከፍተኛ ተጋላጭ ከሆኑት መካከልም ከቡዳዳ በአደጋ ተፈናቅለው በቡላምቡሊ ወረዳ በቡናምቡትዬ የሰፈራ ቦታ በምዕራፍ 2 መንደር ውስጥ ያሉ 140 ቤተሰቦች ይገኙበታል፡፡

የአለም ሀገራት መንግስታት እንዳደረጉት ሁሉ የዩጋንዳ መንግስትም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊ የሆነውን እጅ መታጠብን ያበረታታል፡፡ 

በዩጋንዳ ከማውንት ኤለጎን መሬት መንሸራተት የተረፉ ተጎጂዎች የሚገኙባት ቡላምቡሊን ጨምሮ በርካታ በርካታ የየወረዳ አመራሮችም ነዋሪዎች እጅ የመታጠብ ልምድን እንዲያዳብሩ ይመክራሉ፡፡ 

ይህን መተግበር ግን በቡናምቡትዬ በምዕራፍ 2 ነዋሪዎች ፈጽሞ የማይቻል ልምድ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ለቤት ውስጥ ፍጆታቸውን የሚያሟሉት በአቅራቢያቸው ካሉ ወንዞችና ኩሬዎች ውሀ ነው፡፡

“አገልግሎት የሚሰጡ የውሀ ጉድጓዶች፣ ምንጮች ወይም የውሀ ቧንቧዎች የሉንም፡፡ በቅርብ ያለን አማራጭ ወንዞችና ኩሬዎች ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ አማራጩ ውሀ ለመለመን 2 ኪሎሜትር ርቆ ወደ ሚገኘው ምዕራፍ 1 የሚገኙ ነዋሪዎች ጋር መሄድ ነው” የሚሉት በሰፈራው ጣቢያ ነዋሪ የሆኑት ቶም ዋቡና ናቸው፡፡ 

በአንድ ካሬ መሬት ላይ ባረፈ እያንዳንዱ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚኖረው እያንዳንዱ ቤተሰብ መንግስት ለተጎጂዎች በሰጠው መሬት ላይ የእርሻ ስራን ያከናውናል፡፡ ውሀ ለማግኘት ወደ ምዕራፍ 1 ሰፈራ መሔድ ደግሞ ለእነሱ በጣም አድካሚ ነው፡፡

Bunambutye Resettlement camp for Mt. Elgon landslides surivors 1

በአንጻሩ ደግሞ በምዕራፍ 1 የሚገኙ ነዋሪዎች ውሀ የሚያወጡበት መስመር ለቤታቸው በሚመች ሁኔታ ተሰርቶላቸዋል፡፡

በአካባቢው የምትኖረው ሳራ ኔኬሳ እንደምትናገረው ኮቪድ 19 መከሰት ባመጣው የገንዘብ ችግር የተነሳ አንዳንድ የሰፈራ ጣቢያው ነዋሪዎች ለውሀ ለማስከፈል ተገደዋል፡፡ ንጹህና ደህንነቱ የተጠበቀ ውሀ ባለመኖሩ የተነሳም ቤተሰባቸው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እጅን በአግባቡ ለመታጠብ እንደተቸገረ ኔኬሳ አልሸሸገችም፡፡

“ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የዕንቅስቃሴ ገደብ ከመጣሉ በፊት የዶሮ ምርቶችን፣ የእንስሳት ተዋጽዖዎችንና ሌሎች ምርቶቻችንን ለመሸጥ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካበቢ እንዘዋወር ነበር” ትላለች ኔኬሳ፡፡ አሁን ላይ ግን በሰፈራው መንደራቸው ወጥተው መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ 

በዚህም የተነሳ በገንዘብ ደረጃ መቸገራቸውንና መንፈሳቸውም መላሸቁን ከአደጋ የተረፉት ቤተሰቦች ይናገራሉ፡፡ 

ግሬስ ናቡቱዋ ቡዳዳ ላይ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ዘጠኝ ልጆቻቸውን ያጡ እናት ናቸው፡፡ አሁን ለህይወታቸው የሚያሰጋቸው ነገር ቢኖር የውሀ ችግር ነው፡፡ የምግብ እና የእጅ መታጠቢያ ሳሙና እጥረትም እንዲሁ ያስጨንቃቸዋል፡፡

“ይህ ቫይረስ በዚህ በእኛ የመኖሪያ ጣቢያ ከተከሰተ ሁላችንንም ሞት ጠራርጎ ይወስደናል፡፡ ምከንያቱም እኛ ምንም መከላከያ የለንምና!” ይላሉ፡፡

የአራት ልጆች አባት የሆነውና በመሬት መንሸራተት አደጋ ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን በሞት ያጣው ሞሰስ ዋምቤዴ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ወደ ሰፈራ ጣቢያቸው እንዳይገባ ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑትን የእጅ መታጠቢያ ሳሙና የእጅ ማጽጂያ ሳኒታይዘር እና የአፍና አፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን ለመግዛት እንኳ አቅማቸው እንደማይፈቅድ ይናገራል፡፡

ምንም እንኳ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩጋንዳውያን የኮቪድ 19 በሽታን በቀላሉ መከላከል የሚቻለው ቀላል በሆነው እጅን በሳሙና የመታጠብ ልምድን በማዳበር እንደሆነ ቢሰብኩም፤ በቡናምቡትዬ ካምፕ ያሉ ነዋሪዎች ግን አቅማቸው እንደማይፈቅድ ይናገራሉ፡፡

የቡላምቡሊ ወረዳ ነዋሪዎች ኮሚሽነር የሆኑት ፒተር ፔክስ ፓክ በሰጡት ቃለ-ምልልስ የውሀ እጥረት በሰፈራው አካባቢ በተለይም በምዕራፍ 2 መኖሪያ መንደር ከፍተኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

“በእውነቱ እኔም እንደ አንድ ግለሰብ በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች በተለይም ይበልጥ ተጎጂ ለሆኑት ህጻናትና ሴቶች በጣም ነው የማዝነው” ይላሉ ኮሚሽነር ፓክ፡፡

They are now making and using local waragi for washing hands though children end up drinking and getting intoxicated

ኮሚሽነሩ አክለውም ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመታደግ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ቢሯቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጽህፈት ቤት፣ ለሚመለከታቸው አካላት እና ኤጀንሲዎች እንደሚያሳውቅም አስረድተዋል፡፡

ለጊዜው ግን ኮሚሽነር ፓክ የምዕራፍ 2 ነዋሪዎችን የሚያበረታቱት በምዕራፍ 1 መንደር ከሚገኙ ጎረቤቶቻቸው በልማዳዊ የውሀ መገኛ ምንጮች ውሀን እንዲወስዱ ነው፡፡  

ምንም እንኳ በጥንት ጊዜ የቀደሙ ቤተሰቦቻቸው ከልማዳዊ የውሀ ምንጮች ውሀን ማውጣት ቢችሉም፤ በኤልጎን ክፍለ ግዛት በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበው የህዝብ ብዛት ቁጥር የተነሳ የሰው ልጆች እንቅስቃሴ እነዚህን የተፈጥሮ ውሀ ሀብቶችን አቅምን ሊያዳክምና አደጋ ላይ ሊጥል ችሏል፡፡

ምንጮች እና ወንዞች ለአካባቢው ማህበረሰብ የቅርብ አማራጮች ቢሆኑም በከፍኛ ሁኔታ የተበከለ ውሀን ነው የሚይዙት፡፡ 

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በታጃር፣ በቡኬዲ ወረዳ በኮሊር ክፍለ ከተማን በመሳሰሉ አጎራባች አካባቢዎች የሚገኘው ማህበረሰብም ንጹህና ደህንነቱ የተረጋገጠ ውሀ እጥረት እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡

የማህበረሰቡ አባላት በተለይም ሴቶችና ህጻናት ለመጠቀም ጥሩ ያልሆነ ውሀን ከምንጮች ሲቀዱ የዚህ ዘገባ አቅራቢ ተመልክቷል፡፡ “ምግብ ማብሰል፣ መታጠብ እና ከሁሉም በላይ የፕሬዝዳንቱን የእጅ መታጠብ ትዕዛዝ መተግበር እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለን ብቸኛ አማራጭ ደግሞ ይህ ብቻ ነው” ስትል የአካባቢው ነዋሪ የሆነችው ጁሊያ አሴኬንያ ትናገራለች፡፡ 

በአካባቢዋ እንደሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች ሁሉ አሴንያ ውሀ የምትቀዳው በቡላምቡሊ እና ቡኬዲ ወረዳዎች መካከል ከሚገኘው ከሲሮኖ ወንዝ ነው፡፡

ፒየስ ኦኬሎ በታጃር ነዋሪ ሲሆን፤ ከ600 በላይ የሚሆነው የአካባቢው ነዋሪዎች ጥገኛ የሆኑት አንዳንድ ጊዜ ከትሎች ጋር ጭቃማ ውሀን ከሚያወጣው አንድ የውሀ ጉድጓድ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ 

“በዚህ በተበከለ ውሀ ሁልጊዜም ተጎጂዎቹ ህጻናት ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከመጠጣታቸው በፊት ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ አይተገብሩምና” ሲል ኦኬሎ ይገልጻል፡፡

ይህ ማህበረሰብ ከሶስት አስርት አመታት በላይ በአንድ የውሀ ጉድጓድ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን እየጨመረ የመጣው ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ጫና እና የአየር ንብረት ፈተናዎች መጨመር አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል፡፡ 

እነዚህ መንደሮች በዩጋንዳ የገጠሩ ማህበረሰብ ንጹህ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ ውሀ ላለማግኘቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ በ2ኛው የሀገር አቀፉ የልማት እቅድ ውስጥ የዩጋንዳ መንግስት በገጠር አካባቢዎች በ2012/13 አመት ላይ 65 በመቶ የነበረውን የውሀ አቅርቦትን በ2019/20 ወደ 79 በመቶ ለማሳደግ እንደሚሰራ ቁርጠኝነቱን ገልጾ ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የአደጋ ዝግጁነት እና ቁጥጥር ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሮዝ ናካቡንጎ እንደሚገልጹት የግል ንጽህና አጠባበቅና ጽዳት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሰፈራ መንደሩ መከሰታቸው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን በፍጥነት መቆጣጠር የሚቻል ነው ብለዋል፡፡

“ለዚህም ነው ሚዲያ እጅጉን አስፈላጊ የሆነው፡፡ እኛ ሁሉም ቦታ መድረስ አንችልም፡፡ ሚዲያ ግን ይችላል፡፡ እናም እንዲህ እንደ አሁኑ እኛ እንድናውቀው ያደርጋል፡፡ በምዕራፍ 2 የመኖሪያ አካባቢ ከውሀ ጋር በተያያዘ ያውን ችግር ለመፍታት በአፋጣኝ መስራት ይኖርብናል” ሲሉም ለኒው ቪዥን ተናግረዋል፡፡

This is a borehole in Tajar Kolir in Bukedea district which sometimes pumps brown like creatures and colored water according to residents

የታሪኩ ዳራ

በናሜትሲ መንደር በቡዳዳ አውራጃ በማርች ወር 2010 ላይ የደረሰው የመሬት መንሸራተት በዩጋንዳ ከተመዘገቡ አስከፊ ጉዳቶች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በአደጋውም በኔምሲ መንደር 100 ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ፣ ከ300 በላይ ሰዎችም እንደጠፉ እና 85 ቤቶች እንደወደሙ ይታመናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በ2018 በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ቢያንስ 60 ሰዎች ሲሞቱ፤ 400 ሰዎች ደግሞ ጠፍተዋል፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ሽልንግ የሚያወጣ ንብረትም ወድሟል፡፡ የዩጋንዳ ቀይ መስቀል ማህበር ያወጣው መረጃ ደግሞ ቡዳዳ ውስጥ በቡካላሲ እና ቡዋሊ ክፍለ ግዛቶች በ2018 አደጋ የተጎዱ ሰዎች ብዛት ቁጥር 12,000 መሆኑን ነው፡፡ 

የዩጋንዳ የአየር ንብረት ባለስልጣን እንዳስታወቀው የአብዛኞቹ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች መንስኤ ያልተስተካከለ የዝናብ ሁኔታ መልክ የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡

አብዛኞቹ የመሬት መንሸራተቶች የሚከሰቱት ቀጥ ባሉ እና ውሀን በሚይዙ ጎድጓዳማ አካባቢዎች ነው፡፡ በሰሜን ምስራቅ በኩል የሚገኙ ቦታዎች በዝናብ መምጫ በኩል አቅጣጫ ስለሚገናኙ  ለመሬት መንሸራተት በይበልጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡

የማህረሰቡ ተሳትፎ

በቡናምቡትዬ ሰፈራ በምዕራፍ 2 አካባቢ ለጉዳት የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የመንግስትንና የልማት አጋሮቹ መላ እስኪሰጧቸው ድረስ አርፈው አልተቀመጡም፡፡ ይልቁንም ተጎጂዎች መደራጀትን መርጠዋል፡፡ በሰፈራው መንደር የሚገኙ አዋቂዎችና ህጻናት ለገጠማቸው ችግር መፍትሔ የአጭርና ረጅም ጊዜ የመፍትሔ እርምጃዎችን ፈጥረዋል፡፡ 

ለአብነት ያህልም በቡናምቡትዬ ካምፕ ተፈናቃይ የሆኑ 110 ህጻናት ስብስብ “ዛሬ ዛፍ በመትከል ያለፈውን መርሳት” የሚል ዘመቻ ፈጥረዋል፡፡ 

በታዳጊ ህጻናት የተመሰረተውና የሚመራው ዘመቻ በኤልገን ተራራ የመሬት ናዳ የተጎዳውን ወጣቱን ትውልድ በአካባቢ ጥበቃ መንፈስ የተሞላ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቡናምቡትዬ ካምፕ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ አስተባባሪ የሆነው ታዳጊው ጄምስ ዋክሆሊ በለጋ እድሜያቸው ዛፍ ለምን እንደሚተክሉ ተጠይቆ ሲመልስ፤ የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት የነጠቀባቸውን አደጋ ለማስቀረት የሚረዳ አስፈላጊ ስለሆነ ነው ብሏል፡፡

“አብዛኞቻችን ወላጆቻችንን፣ ጓደኞቻችንን፣ መምህሮቻችንን እና ዘመዶቻችንን አጥተናል፡፡ ለእኛ ወደፊት ለመቀጠል ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር አደጋው ተመልሶ እንዳይመጣ በመከላከል ነው” ሲል የተናገረው ዋክሆሊ፤ እስከ አሁን የተከሏቸውን ዛፎች ለዘጋቢዎች አሳይቷል፡፡

ታዳጊዎቹ ልጆች ዛፎችን የሚተክሉት በካምፑ ውስጥ መንግስት ለእያንዳንዱ ቤት በሰጠው ካሬ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ከወላጆቻቸው ቤቶች ግቢ ውስና ውጪ ባሉ አካባቢዎችም የዛፍ ችግኞችን ይተክላሉ፡፡

“አሁን የእኛ ችግር ቦታ አለማግኘት ነው፡፡ እዚህ በቂ መሬት ብናገኝ አሁን ከተከልነው ዛፍ የበለጠ ብዙ ዛፎችን መትከል እንችል ነበር” ሲል የ13 አመቱ ኤቨር ናማታካ ይናገራል፡፡ 

የቡናምቡትዬ አደጋ ካምፕ ህጻናት ልጆች ያለፈውን አሳዛኝ ትዝታ ጉዳት ለማስቀረት በአካባቢያቸው እስከ አሁን ድረስ የተለያየ ዝርያ ያላቸው 200 ችግኞችን ተክለዋል፡፡

እነዚህን በአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሰጡት ልጆችን የገጠማቸው ሌላ ፈተና ችግኝ ለመትከል አስፈላጊ የሆነውን ውሀ በምዕራፍ 2 አካባቢ አለማግኘታቸው ነው፡፡ 

ይህንን ትኩረት ሰጥቶ የሚናገረው ናማታካ “ዛፎቹ እየጠወለጉና ለመሞት እየተቃረቡ ነው፡፡ ምክንያቱም በምዕራፍ 2 አካባቢ የምንኖር ህጻናት ሁላችንም በቂ የሆነ ውሀ ስለሌለን ነው” ብሏል፡፡

የባለስልጣናቱ መልሶች

ለህጻናቱ ችግኞችን የለገሰው የወረዳው የደን ዲፓርትመንት የህጻናቱ ዘመቻ በቀጣይ 10 አመታት የአካባቢውን የደን ሽፋን መጠን አሁን ካለበት 40.6 በመቶ ወደ 55.9 በመቶ እንደሚያሳድግ ይገምታል፡፡ 

የተሻሻለ የውሀ አገልግሎት አቅርቦትና ምቹ አካባቢን ለመፍጠር ብሔራዊ መነሳሳትን ለመፍጠር መሪ የሆነው የመንግስት ተቋም የውሀ እና አካበቢ ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በህጻናቱ ተግባር ተደንቋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ቢያትሪስ ኤኒዋር የቡናምቡትዬ መልሶ ሰፈራ ካምፕ ህጻናትን አድንቀዋል፡፡ 

“ህጻናቱ ከዚህም የበለጠ መስራት የሚችሉ ነበሩ፡፡ እንደ ሚንስቴርም ሆነ እንደ አካባቢ ጥበቃ አክቲቪስት በግሌ እነዚህ ህጻናት ትልቅ ስራ ሲሰሩ በመመልከቴ በጣም ተደንቄያለሁ፡ ምክንያቱም እነዚህ ልጆች ቡዳዳ ውስጥ ሀላፊነት በጎደለው የሰው ልጆች አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎች በፈጠሩት ውጤት ተጎጂ ስለነበሩ ነው” ሲሉም ኤኒዋር ተናግረዋል፡፡

እንደ ኤኒዋር ገለጻ በዩጋንዳ ገጠራማ አካባቢዎችም ሆነ በመላ አፍሪካ ታደጊ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ታዳጊዎችን ማግኘት እውነተኛ ውይይትን የሚረዳ ነው፡፡ 

ልክ እንደ ሚኒስቴር ኤኒዋር ሁሉ የቡላምቡሊ አካባቢ ወረዳ ኮሚሽነር ፓክም በታዳጊ ወጣቶቹ  የአካባቢ ጥበቃ ስራ ተደንቀዋል፡፡ ሌሎች አጎራባች ማህበረሰቦች “ከእነዚህ ህጻናት ቅጠል መበደር” መጀመር አለባቸው ብለዋል፡፡ 

የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሯ እንደተናሩት በቂ የሆነ የደን ሽፋን ባላቸው አካባቢዎች አብዛኛውን ጊዜ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ንጹህ የውሀ ሀብት ይኖራል፡፡ በምዕራፍ 2 በካምፑ ውስጥ ለሚኖሩ ማህበረሰብ ክፍሎች ከውሀ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት የበኩላቸውን እንደሚያደርጉም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም በካምፑ የሚገኙ ወላጆች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊ የሆነውን የእጅ መታጠቢያ ሳሙና መግዛት ስለማይችሉ ለእጅ ንጽህና መጠበቂያነት የሚያገለግለውን ባህላዊውን ዋራጊን (አረቄ መሳይ መጠጥ) ማዘጋጀት ጀምረዋል፡፡

 “አንዳንዶቻችን ባህላዊውን ዋራጊን ማዘጋጀት ጀምረናል” ያሉት በቡዳዳ ወረዳ በ2018 የመሬት መንሸራተት አደጋ አምስት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በሞት ያጡት ዘከሪያ ማቱቦንዶ ናቸው፡፡ 

“ከዚህ ዋራጊ ጋር በተያያዘ ችግር የሆነብን ህጻናቱ መጠጣታቸውን መቀጠላቸው ነው” በማለትም ማቱቦንዶ ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡ 

የቡላምቡሊ ወረዳ ፖሊስ ኮሚሽነር ፔሸንስ ባጋንዚ በበኩላቸው ዋራጊን እንደ ሳኒታይዘር ለእጅ ማጽጃነት መጠቀም የቤት ውስጥ ጥቃት እና የህጻናት መብት ጥሰት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም በማንኛውም ሰአት ቤት ውስጥ አግኝተው ሊጠጡና ሊሰክሩ ስለሚችሉ ነው ብለዋል፡፡ 

የቡላምቡሊ ወረዳ በሚያዝያ ወር ብቻ በቤት ውስጥ ጥቃትና ህጻናት መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ 20 ጉዳዮች ተመዝግበውበታል፡፡ ይህም ከተለመዱ ምክንያቶች 80 በመቶ ጨምሯል፡፡ለዚህም ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል ተብሎ የሚዘጋጀውን ዋራጊን መጠቀም አይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ፖሊስ መገንዘቡን አስታውቋል፡፡

ይህ የኢንፎናይል ዘገባ የተጠናከረው ለኮድ ፎር አፍሪካ እና ፑልቲዘር ሴንተር እና ናሽናል ጂኦግራፊ ሶሳይቲ ባደረጉት ድጋፍ ነው፡፡

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts