በጃቪየር ሲላስ ኦማጎር
ከአምስት አመታት በፊት ሙሳ ማንዳ በማናፍዋ ወረዳ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል የመንግስት ስራውን ሊለቅ እንደሆነ ለባለቤቱና ለዘመዶቹ በነገራቸው ጊዜ ከሚገባው በላይ ተበሳጭተውበት ነበር፡፡
‹‹እነርሱ ምን ማለት እንደሆነ ፈጽሞ አልገባቸውም ነበር፡፡ በገንዘብ ደረጃ እኔንም ሆነ ቤተሰቤን ለማቆየት ስለመቻሉ አላሰቡም ነበር›› ይላል ማንዱ፡፡ ‹‹ሰዎች ያስቡት እንደነበረውና አሁንም እንደሚያስቡት የእለት ዳቦ እንኳ የሚገዛ እንዳልሆነ ነው፡፡ ማንም ቢሆን በተለይም በእኛ ባልነቃ ማህረሰብ ዘንድ የአካባቢ ጥበቃ የሚሰጠውን ጥቅምን የተረዳ አልነበረም››
ነገር ግን የቀድሞው ሜካኒክ የባለቤቱንና ዘመዶቹን ጭንቀት ቸል በማለት የቡቡሎ አካባቢያዊ ጥበቃ ማህበር ፕሮጀክት (ቢኮማፕ) Bubulo Environmental Conservation Management Association Project (BECOMAP) የተሰኘ የመንደር ውስጥ የቁጠባና የብድር ትብብር ተቋምን መሰረተ፡፡ ፕሮጀክቱ የተመሰረተው በማናፍዋ ወረዳና በአጎራባቾቹ የአካባቢ ጥበቃ ስራን መስራት ነው፡፡ የቡድኑ አባላት ራሳቸው ቡድኑን የሚያስተዳድሩ ሲሆን፤ በዝቅተኛ ወለድ እርስ በእርስ መበዳደር እንዲችሉ በቋሚነት ይቆጥባሉ፡፡
‹‹በእኛ አካባቢ (በናሙቴምቢ መንደር) ሰዎች እንዲገነዘቡት የምፈልገው ነገር እኛ እንደ አካባቢ ነዋሪ የምንሰራው ማንኛውም ነገር እስከ ፖሊሲ አውጪዎች ድረስ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይን ቅድሚያ መስጠት ተፈጥሮን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ቋሚ ገቢ በማግኘትም የተሻለ ህይወት መምራት እንደምችል ለማረጋገጥም ነው›› ሲል ማንዱ ተናግሯል፡፡
ህብረተሰባዊ መፍትሔ ለመሬት መንሸራተት
የጎርፍ አደጋን፣ የአፈር መሸርሸርን፣ የውሀ ሙላትና እና የመሬት መንሸራተትን ለመቋቋም ለዛፍ ተከላ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን ለመጠበቅ እና ለህብረተሰብ ማነቃቂያ መርሀግብሮች የሚውል ገንዘብን ለመቆጠብ ያለመው ፕሮጀክት የተመሰረተው በ2013 ነበር፡፡ ማንዱና አብዛኛዎቹ የቡድኑ አባላት በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የመሬት መንሸራተት እና ባለፉት በርካታ አመታት በኤልጎን ክፍለ ግዛት በተለይም በቡዱዳ፣ በማናፍዋ፣ በሲሮንክሆ እና በቡላምቡሊ ወረዳዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የተረፉ ናቸው፡፡
ክልሉ ከመሬት መንሸራተት ጋር በተያያዘ የረጅም ጊዜ ታሪክ አለው፡፡ በ1950ዎቹ እና በ60ዎቹ መጀመሪያ 11 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር ፍርስራሽ የማውንት ኢልጎንን በማፈራረስ ወደ ወንዞችና ተፋሰሶች እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ከነዚህ ሰላሳ የመሬት ፍርስራሽ ግድቦች ሲሰበሩ ወንዞችን አግደዋል፤ ድልድዮችንና መንገዶችን አጥፍተዋል፡፡
በቅርብ አመታት ግን የመሬት መንሸራተት አደጋ በቁጥርም ሆነ በአይነት ጨምሯል፡፡ በ1997 እና በ2004 ባሉት አመታት ውስጥ በታላቁ ማናፍዋ አካባቢ የጣለው ከባድ ዝናብ 48 ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ያፈናቀለና መሬት አልባ ያደረገ ነበር፡፡ በ2010 ማርች ወር ላይ በቡዱዳ ወረዳ በሚትሲ መንደር የተከሰተው የመሬት መንሸራተት በዩጋንዳ ታሪክ በአስከፊነቱ የተመዘገበ ነው፡፡ በአደጋው 100 ሰዎች መሞታቸው የታመነ ሲሆን፤ ከ300 በላይ የሚሆኑት ያሉበት አልታወቀም፡፡ በናሜትሲ 85 ቤቶችን አውድሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመሬት መንሸራተት አደጋ በ2018 የተከሰተ ሲሆን፤ ቢያንስ 60 ሰዎችን ገድሏል፤ 400 ያህሉ ደግሞ አልተገኙም፡፡ በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በቢሊዮን የሚቆጠር ሺልንግ የሚያወጡ ንብረቶችም ድራሻቸው ጠፍቷል፡፡ የዩጋንዳ ቀይ መስቀል ማህበር በ2018 በቡዱዳ አዋሳኝ ግዛቶች በሆኑት በቡካላሲ እና በቡዋሊ የተጎዱት ሰዎች ቁጥር 12.000 እንደሆነ ነው ያስታወቀው፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ የሚከሰተው ያልተለመደ ዝናብ ለመሬት መንሸራተቶቹ ዋንኛ መንስኤ መሆኑን የዩጋንዳ ብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ የመሬት መንሸራተቶች የሚከሰቱት ውሀ በሚጠራቀምባቸው ቀጥ ባሉ ገደሎችና በጎድጓዳማ ቁልቁለቶች ነው፡፡ በሰሜንምስራቅ ፊት የሚገኙት ቁልቁለቶች ለከፍተኛ ለመሬት መንሸራተት የተጋለጡ ሲሆኑ፤ ከዝናብ መምጫ አቅጣጫ ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡
የወንዝ ጅረቶችና ተፋሰሶች መጥፋትን ጨምሮ ደካማ የግብርና አሰራሮች አደጋዎቹን አባብሰውታል፡፡
በ1960ዎቹ፣ በ1970ዎቹ በማፍዋ ወረዳ የሚገኙት እንደ ፓሳ፣ ናሜትሲ እ ማናፍዋ ወንዝ ያሉ ወንዞች ማህበረሰቡ የሚጠቀምበትን ንጹህና ደህንነቱ የተጠበቀ ውሀ ነበራቸው፡፡ ኮረብቶች ቁልቁለቶች ሁሌም በዝሆን ሳርና ዛፎች የተሸፈነ አረንጓዴ እጽዋቶች የተሸፈኑ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ሀላፊነት የጎደለው የሰው ልጅ እንቅስቃሴዎች ቁልቁለቶቹ ላይ ጫና በመፍጠር የወንዝ ጅረቶችና ተፋሰሶችን አጥፍቷል፤ የአፈሩን ሻካራነት አለስልሶታል፡፡ ይህም ለመሬት መንሸራተት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡
በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የመሬት መንሸራተት አደጋ ያስጨነቃቸው ማንዱ እና ሌሎች በማናፍዋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ 10 ሰዎች በ2013 አካባቢያቸውንና በክልሉ የሚገኙ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ በ2013 ቢኮማፕን (BECOMAP) መሰረቱ፡፡
እያንዳንዱ አባል 20.000 ወይም 50.000 የዩጋንዳ ሽልንግ (በግምት ከ5-13 ዶላር) መዋጮን ከፍሏል፡፡ እያንዳንዱ 10 መስራች አባል 100 ዛፎች የሚተክሉበትን አንድ ሄክታር መሬት ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ስድስት አመታት የተመዘገቡ የአባላት ቁጥሩን ወደ 72 ማሳደግ የቻለ ሲሆን፤ ከእነርሱም መካከል 20 በመቶ ወጣቶች፤ 30 በመቶ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ቡድኑ ከ30.000 በላይ ዛፎችን ተክሏል፡፡ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በ50 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በመግባቢያ ሰነድ ስምምነታቸው መሰረት የቡድኑ የጋራ ንብረት ነው፡፡
የቡድኑ አባላት በአብዛኛው የሚተክሉት ዛፎች ከጥድና ከባህርዛፍ በተጓዳኝ በአፍሪካ ባላዊ ማህበረሰብ ወቅት ይበቅሉ የነበሩትን እንደ ምቩሌ ዛፎች አይነቶቹን ሀገር በቀል ዛፎች ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አይነቶቹ ዛፎች የተሻለ አፈርን የመጠቀምና ውሀን የመያዝ አቅማቸው በጣም ጥሩ መሆኑ በመረጋገጡ ነው፡፡
ሰው ሰራሽ ደኖች ለማህበረሰቡ አባላት ገቢ የሚያስገኙ የስራ ምንጭ እየሆኑ ነው፡፡ ዛፎችን ከመትከል ጎን ለጎን የቡድኑ አባላት በደኖቻቸው ውስጥ የጥራጥሬ እህሎችን ሰብሎችን፣ እንደ ጎመን፣ ቲማቲምና አቮካዶ ያሉ አትክልቶችን፣ እና እንደ ፓሽን ፍራፍሬ እና ማንጎ ያሉ ፍራፍሬዎችን ለሽያጭና ለቤት ፍጆታ ያበቅላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአጠና የሚሆኑ ዛፎችን ይሸጣሉ፤ በደን ክልላቸው ውስጥ የንብ ቀፎ በመስቀል ማር በመሸጥ ገንዘብ ያገኛሉ በማለት ማንዱ ተናግሯል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ የሚሸጠው ምርታቸው ማር ሲሆን፤ በአማካይ 1ሚሊዮን የዩጋንዳ ሽልንግ (ከ270-450 የሚጠጋ ዶላር) ገቢ በየሳምንቱ ያገኛሉ፡፡
ጆን ዋቡና በ20ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኝ ወጣት ሲሆን፤ እንደ እርሱ ያሉ የአካባቢው ማህበረሰብ ወጣቶች ከማር፣ ከፍራፍሬዎች እና አትክልቶች እንዲሁም ከአጠና እንጨት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ አሁን የትምህርት ክፍያቸውን መሸፈን እንደቻሉ ይናገራል፡፡
በቢኮምብ ድርጅት ውስጥ በይፋ ለአባልነት የተመዘገቡ ከ15 በላይ ወጣቶች የሚገኙ ሲሆን፤ 50 ወጣቶች ደግሞ በዘመቻ ላይ ይሳተፋሉ፡፡
የቡድኑ አባላት እንደገለጹት በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ተግዳሮት ሆነው ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን በደኖቹ አማካኝነት አደጋዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል፡፡ ሞትን የሚያስከትል ከባድ ዝናብ በሚከሰትባቸው ከአጎራባች ወረዳዎች ከቡዱዳ፣ ናሚሲንዳ እና ቡታሌጃ ደግሞ እውነታው ተቃራኒ ነው፡፡
ማንዱ የእነሱን መንገድ ያለምንም ሰበብ በዩጋንዳ ሁሉም ማህበረሰብ የአየርንብረት ለውጥን በስፋት ለመከላከል እንዲጠቀምበት ነው የሚመክረው፡፡
በቀጣይ ቅርብ ጊዜ ውስጥ ቢኮማፕ የቁጠባ ቡድኑን ወደ ተቀናጀ የትብብር ማህበረሰብ በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በማውንት ኢልጎን ክፍለ ክልል እና ከዚያም ባሻገር ለመስራት መነሳሳቱን የቡድኑ የኦፕሬሽን እና ስትራቴጂ ሀላፊ ማይክል ሚሪሲዮ አስታውቀዋል፡፡
የሪሊፍዌብ የአለምአቀፍ ልማት ዲፓርትመንት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በሰው ልጆች ተጽዕኖ የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ አማካይ የሙቀት መጠን በቀጣዮቹ 20 አመታት በዩጋንዳ በ1.5 ፤ በ2080ዎቹ ደግሞ ወደ 4.3 ዲግሪ ሲልሺየስ እንደሚጨምር ነው፡፡ ይህ መጠንም ከዚህ በፊት ተከስቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል፡፡
የዩጋንዳ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው ግብርና ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የዝናብ አቅጣጫ እና አመታዊ አጠቃላይ የዝናብ መጠንም ላይም ለውጦች እንደሚኖሩ ይጠበቃሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሪፖርቱ ዩጋንዳ በከፍተኛ ሁኔታ ለአየርንብረት ለውጥና ተቀያያሪነት ተጋላጭ መሆኗን፤ ኢኮኖሚዋ እና የህዝቦቿ ደህንነት ከአየር ንብረት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በሰው ልጆች አማካኝነት የሚከሰት የአየር ንብረት በቀጣዩ ክፍለዘመን የሀገሪቷን የእድገት አቅጣጫ ለማቆም ወይም ለመለወጥ ከፍተኛ አቅም አለው፡፡
‹‹ፖለቲከኞችና ትልልቅ የቢዝነስ ሰዎች ይህንን ትግል መቀላቀል አለባቸው፤ የአለም ኢኮኖሚን ለመገንባት ተስፋ በማድረግ ፕላኔታችንን እና ህዝቦቿን ልትጨቁናቸው፣ ጉድጓድ ውስጥ ልትቀብራቸው፣ ልትሰረስራቸው እና ልታርሳቸው አትችልም፡፡ ባለጸጋዋ ፕላኔትህ ልትጠፋ፣ ልትመነምን፣ ልትሸረሸር እና ልትጠፋ ትችላለች›› ሲሉ የምባሌ ማዘጋጃ የአካባቢ ጥበቃ ኦፊሰር ሮህ ንያሪቢ ያስጠነቅቃሉ፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በተለየ ሁኔታ በማውንት ኢልጎን ክልል ለብዙ ህይወት እና ንብረቶች መውደም፣ የምግብ ደህንነት አለመረጋገጥን የሚጨምር፣ እንደ ወባ ላሉ በሽታዎችን መስፋፋትን የሚፈጥር፣ የአፈር መሸርሽን እና የመሬት መከላትን፣ የጎርፍ አደጋ በመሰረተልማት እና ሰፈራዎች ላይ የጎርፍ አደጋን የሚያስከትል፣ እና የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ልማትን አቅጣጫ የሚያስቀይር ነው፡፡
ዛፎች የአየር ንብረትን እንዴት ይከላከላሉ?
‹‹የአየር ንብረት ለውጥ እና የአለም ሙቀት መጨመር በአሁኑ ወቅት የአለማችን ትልቁ ስጋት ሊሆን የቻለው ከአካበቢችን ጋር ያለን ግንኙነት ሀላፊነት የጎደለው በመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ ይሁንና እኛ እንደ ሰብአዊ ፍጡር ከተሞክሯችን በመማር በአዎንታዊ መልኩ ልዩነትን መፍጠር እንችላለን›› ይላል ማንዱ፡፡
‹‹የሙቀት መጠን በአስገራሚ ሁኔታ በመጨመሩንና የውሀ መጠን በአስደንጋጭ ሁኔታ በመቀነሱ አሁን ሁሉም ሰው ወቅቶች እንዴት እንደሚቀያየሩ ተመልክቷል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ማለት አሁኑኑ ተግራዊ እርምጃ መውሰድ አለብን ማለት ነው! የመንግስትን ጣልቃገብነት መጠበቅም አይኖርብንም›› ብሏል፡፡
አብዛኞቹ የቢኮማፕ ዛፎች የተተከሉት በተራሮች፣ ቁልቁለቶች፣ ተፋሰሶችና የወንዞ ጅረቶች ላይ ነው፡፡ ስለዚህም በማውንት በኤልጎን ቁልቁለታማ ቦታዎች የተለመዱ አደጋዎች የሆኑትን የጭቃ መንሸራተትን፣ ጎርፍን እና የውሀ ሙላትን መከላከል ይቻላል፡፡ አደጋዎችን ከመቀነስ ጎን ለጎን ዛፎቹ ከስነ ምህዳሩ በተፈጥሮ ካርበን እና ሌላ የግሪንሀውስ ጋዞችን ይወስዳሉ፡፡ ይህም የአየርንብረት ለውጥ ተጽዕኖን እንዲዘገይ ያደርገዋል፡፡
የአየርንብረት ለውጥ ኤክስፐርት እና ጂዮሎጂስት የሆኑት ፍሬድክ ጆርዳን ኦሉካ ዛፎች የአየር ንብረትን ለመከላከል ያላቸውን የጎላ አስተዋጽኦ በመጥቀስ የቢኮምፕን እንቅስቃሴ አድንቀዋል፡፡
‹‹በጥሩ የዛፍ ጥላ የተሸፈኑ በአጎራባች ማህበረሰብ ዛፍ ከሌላቸው ከ6-10 ዲግሪ ሼልሺየስ ድረስ የበለጠ የቀዘቀዙ ናቸው›› የሚሉት ኦሉካ፤ ‹‹ለአየርንብረት ለውጥ ዋና ሚና ያለው ዋና የግሪን ሀውስ ጋዝ የሆነውን የተቃጠለ አየርን (ካርቦንዳይኦክሳይድን) ለመቀነስ ዛፍን መትከል ማንም ሰው ማድረግ የሚችለው ቀላሉ ነገር ነው›› ብለዋል፡፡
የቢኮምፕ አባላት በተለየበ ሁኔታ የዛፍ ተከላ ትኩረታቸው በወንዝ ጅረቶች፣ በቁልቁለታማ ቦታዎች እና ተራሮች ላይ በማድረጋቸው አመስግነዋቸዋል፡፡ ምክንያቱም የተተከሉት አብዛኞቹ ዛፎች አፈርና ድንጋዮችን በጋራ አጥብቆ ለመያዝ የሚጠቅሙ በመሆናቸው እንደ መሬት መንሸራተት ያሉ አደጋዎች እንዳይከሰቱ መመከት ይችላሉ፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ኤክስፐርቱ እንደገለጹት ዛፎቹ በሚቀጥሉት 10 አመታት ወይም ከዚያም በኋላ እያደጉ ሔደው የተተከሉት ዛፎች እና የዝሆኔ ሳሮች አፈሩን በአንድነት ለመያዝ፣ ነፋስን ለመክፈል እና ስነ ምህዳሩን ለመጠበቅ እና ሌሎች ጠቃሚ ሚናዎችንም ይጫወታሉ፡፡
‹‹ይህ ማለት በቅርቡ በማውንት ኤልጎን ክልል የመሬት መንሸራተቶች፣ ጎርፍ እና የአፈር መታጠብ ቀንሶ እናያለን ማለት ነው›› ሲሉ ኦሉካ ተናግረዋል፡፡
የልማትና አካባቢ ጥበቃ አድቮኬት ጥምረት ሰብሳቢ ዶክተር አርተር ቤይኖሙጊሻ የመንደሪቱ ቡድን በማውንት ኤልጎን ቁልቁለቶች የአካባቢ ጥበቃን ማሸነፋቸውን አድንቀዋል፡፡
የዩጋንዳን መጻኢ ጊዜ ለማረጋገጥ በዩጋንዳ እያንዳንዱ ማህበረሰብ የቢኮምፓን ተሞክሮቸእንዲከተሉ ቤትኖሙጊሻ ይፈልጋሉ፡፡
‹‹ከእኛ ከሶስተኛው አለም ሀገሮች በተቃራኒ ዛፍ መትከል በአደጉት አገሮች፤ በከተሞች ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ እየተተገበረ ነው፡፡ ምክያቱም የዛፍ ጥላ ያላቸው ከተሞች አውቶሞቢሎች አቀዝቅዘው ለማቆየት ስለሚችሉ፣ ከነዳጅ ማጠራቀሚያ፣ ከነዳጅ መሙያ ጣቢያዎችና ከሞተሮች የሚወጣውን የጋዝ ልቀት ስለሚቀንሱና በማህበረሰቡ ውስጥ የሙቀት ደሴት ውጤትን ለመቀነስ ስለሚረዱ ነው›› ሲሉ ቤይኖሙጊሻ ተናግረዋል፡፡
በዩጋንዳ እያንዳንዱ ማህበረሰብ የቢኮማፕን ፈለግ እንዲከተል ቤይኖሙጊሻ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ይህ የዩጋንዳን ክብር በአለምአቀፍ ደረጃም የሚያስጠብቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በ2016 በሞሮኮ በተካሔደው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለማስቀረት በቂ ስራ ካልሰሩ ሀገሮች መካከል ዩጋንዳ አንዷ መሆኗ ተጠቅሶ ስለነበር ነው›› ብለዋል፡፡
የቢኮማፕ አንደኛው መስራች አባልና የቀድሞ ሲኒየር የኢኮኖሚ ባለሞያ ሳም ማውሶ ሲራሊ በበኩላቸው ‹‹ማንም ሰው የትም ቢኖር፤ ዛፍን መትከል ይችላል፡፡ ይህን ማድረግም ሀገራችንን እና ፕላኔታችን ጤናማ እንዲሆኑ አንድ ተግባራዊ እና አዎንታዊ እርምጃ ነው›› ብለዋል፡፡
ይሁንና እንደ ማውሶ ከሆነ፤ ተራው ህዝብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ መቆጠብ የለበትም፡፡ በተለይም በጣም ቀላሉ መንገድ የሆነውን ዛፎችን በመትከል መከላከል ይችላል፡፡
የአካባቢ ጥበቃን ለህብረተሰቡ ማቅረብ
በፋይናንስ ሚንስትር መስሪያ ቤት ሲኒየር የኢኮኖሚ ባለሞያ የሆኑት ማውሶ፤ የአለማችን መንግስታት ስለ አየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች በጠጣር ቃላት ማውራታቸውን እንዲያቆመሙ ይፈልጋሉ፡፡ ይልቁንም የአካባቢ ማህበረሰብ አባላት በሚረዱት ሁኔታ ቀላል ቃላትን እንዲጠቀሙ ነው የጠየቁት፡፡
‹‹በተለይም ደግሞ በማህበረሰብ ውይይቶች ላይ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ እና ግሎባል ዋርሚንግ የመሳሰሉ ቃላትን ነው የምንጠቀመው፡፡ ማህበረሰቡ ደግሞ የምንወያየው የልሂቃን ጉዳዮች ላይ ይመስለውና ራሱን ያርቃል›› ሲሉ ማውሶ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የማህበረሰቡን ትኩረት ልናገኝ የምንችለው በሚገባቸው ቀላል ቃላቶች ስንጠቀም እና ዛፎችን መትከል ጥቅሙ ለራሳቸው እንደሆነ ስንነግራቸው ነው››
በቡዱዳ ዲስትሪክት የማንጂያ ግዛት የህዝብ እንደራሴ የሆኑት ጆን ባፕቲስት ናምቤሺ፤ የቢኮማፕ ዛፍ ተከላ ተሞክሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአርአያት የሚጠቀስ መሆኑን አድንቀዋል፡፡
‹‹ከእዚህ ቡድን ስራ በመነሳሳት በመላው ሀገሪቱ በጋራ ዛፍ መትከልን የሚደግፈውን ፖሊሲ ለማውጣት እያሰብኩ ነው፡፡ ነገር ግን የትኞቹን ዝርያዎች መትከል እንደሚገባን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ጥራት ያላው ዛፎች መሆን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ዛፎች በተራራማ አካባቢዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቋሙው ለመብቀል ስለሚያዳግታቸው ነው›› ብለዋል፡፡
ይህ የናምቤሺ እንቅስቃሴ ስኬትን ከተጎናጸፈ ዩጋንዳ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነ እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ቢያንስ የተወሰነ ዛፎችን መትከል እንደሚጠበቅበት የሚያስገነዝበውን ህግን ካጸደቁት ጎረቤቶቿ ርዋንዳ እና ኬንያን ልትቀላቀል ትችላለች፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የፓርላማ ኮሚቴ አባልየሆኑት ናምቤሺ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ከዩጋንዳ መንግስት የተሻለ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትን ይሻሉ፡፡
እንደ ቢኮምፓ ያለ ማህበረሰብ ወለድ እንቅስቃሴዎች ወጥ የሆነ እድገት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከመንግስት እና ከልማት አጋሮች ተገቢውን ማበረታቻ እንዲያገኙ ግፊት ያደርጋሉ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሆኑት እንደ ዶክተር ማሪ ጎሬቲ ኪቱቱ አስተያየት በቡጊሱ ለመሬት መንሽተት እና ሌሎች አደጋዎች ቋሚ መፍትሔው የተራቆተውን አካባቢ መልሶ ማልማት ነው፡፡
‹‹የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊቀጥሉ የሚችሉት ሰዎች ደካማ በሆነ የግብር ተግባሮች አማካኝነት ነው፡፡ የወንዝ ዳቻዎችን መጠበቅ አለብን›› ይላሉ ሀላፊዋ፡፡ እንደ ቢኮማፕ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥን የሚዋጉ ቡድኖች ሴቶችና ወጣቶች በዘመቻቸው ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታት እንዳለባቸውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ናቹራል ሪሶርስ ኢንስቲትዩት (በአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ማዕከል) የተካሔደ የ2017 ጥናት እንዳመለከተው በዩጋንዳ የደን ሽፋን መመናመን በየአመቱ ወደ 200.000 ሄክታር ጨምሯል፡፡ ለዚህ የደን ሽፋን መጥፋትም በአብዛኛው የሰው ልጆች አማካኝነት የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በተፈጥራዊ ምክንያቶች የሚደርሰው ጥፋት በጣም አነስተኛ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በተወሰነ ደረጃ የሚጠቀሰው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ በየአመቱ በ3.6 መቶ የሚያድገው የዩጋንዳ የህዝብ ብዛት ቁጥር ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የቅርብ ጊዜ ሪፖርት በ2019 ኦገስት ወር በየዩጋንዳ የህዝብ ብዛት 45.883.274 የሚገመት ነው፡፡ በአሁኑ የእድገት መጠን መሰረት በ2025 ላይ ዩጋንዳ ወደ 63 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ መኖሪያ እንደምትሆን ይገመታል፡፡
የቀድሞ የማናፍዋ ሴት የፓርላማ አባል ሳራ ኔታሊሲሬ፤ የቢኮማፕ መስራች አባላት አማካሪዎች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ የቡዱኑን ተሞክሮ የከተማ አካባቢዎች ጨምሮ በመላው ዩጋንዳ የሚገኙ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች በፍጥነት ሊተገብሩት ይገባል ብለዋል፡፡
በዩጋንዳ የፓርላማ ኪሚቴ፣ በብሔራዊ አካባቢያዊ አስተዳደር ባለስልጣን የሚመሩት የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲዎች እና የአካባቢ ጥበቃ ፖሊስ ጭምር የሚገኙበት የተባበሩት መንግስታት ኢንተርገቨርመንታል ፓናል የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የቀድሞዋ ህግ አውጪ ይጠይቃሉ፡፡
‹‹ከመኖሪያቤት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ ማውጣት አለባቸው፡፡ ህዝቡ በየአካባቢው፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ በስራ ቦታውና እንደ የገበያ ቦታዎችና የእምነት ቦታዎች ባሉ ህዝባዊ አካባቢዎች ዛፎችን መትከል አለበት›› ሲሉ ኔታሊሲሬ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡