ህይወት ከኮቪድ 19 ጋር በኬንያ ትልቁ የድሆች መኖሪያ

ህይወት ከኮቪድ 19 ጋር በኬንያ ትልቁ የድሆች መኖሪያ

በሔንሪ ኦዊኖ

ኮቪድ 19 በመጋቢት 2020 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም ጤና ድርጅት አማካኝነት ወረርሽኝ መሆኑ ይፋ ሲደረግ አፍሪካውያን እጅጉን ተሸብረው ነበር፡፡

የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰባቸው የእስያ እና አውሮፓ ሀገሮች ከተከሰተው የሞት መጠን አንጻር ብዙዎች የከፋ ነገር እንደሚደርስ ነበር የጠበቁት፡፡ የአፍሪካ ሀገሮች ካላቸው ደካማ የጤና አሰራርና ዝግጅት ማነስ የተነሳም ኮቪድን ለመቋቋም ዝቅተኛ ግምት ነበር የተሰጣቸው፡፡

በአፍሪካ የዘፈቀደ የሰዎች አሰፋፈሮች ደግሞ ቫይረሱ ከፍተኛ ጥቃት ከሚያደርስባቸውና የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ ከሚችልባቸው ቦታዎች መካከል በዋንኛነት ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ ይሰነዘሩ የነበሩ ቅድመ ትንበያዎች በአፍሪካውያን ዘንድ ድንጋጤና ጭንቀትን ፈጠሩ፡፡ አብዛኞችም የከፋ ነገር ከመጣ ብለው ለፈጣሪያቸው ሐጢያታቸውን መናዘዝ ጀመሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከቫይረሱ ለማምለጥ ሞከሩ፡፡

“ሞትን እንዲሁ እያየን ልንጠብቀው አንችልም፡፡ የኮቪድ 19 በሽታ መንስኤ የሆነው ቫይረስ የሚሰራጨው በንጽህና አጠባበቅ ጉድለት እና መተፋፈግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለምንም ልፋት ኪቤራ ጥሩ ምሳሌ ናት” የምትለው የኪቤራ ነዋሪ የሆነችው ቢያትሪስ አንያንጎ ናት፡፡

ይህችን የ250,000 ህዝብ መኖሪያ የሆነችውን የድሆች ከተማ ኪቤራን በመልቀቅ በርካታ ነዋሪዎች ቫይረሱን ፍራቻ ወደ ገጠር አካባቢዎች ሔደዋል፡፡

ይሁንና እንደ ድንበር መዝጋት እና የአካላቂ ርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች በመወሰዳቸው እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች የቫይረሱን ስርጭት ለማዘግየት ተችሏል፡፡

በኬንያም ሆነ በአፍሪካ በትልቅነት የሚጠቀስ የሰዎች የዘፈቀደ አሰፋፈር ያለባት ኪቤራ በማህበረሰብ ተነሳሺነት የተካሔዱ የውሀ እና የንጽህና መጠበቂያዎች አቅርቦት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ነዋሪዎችን ለመታደግ አስችሏል፡፡ ይህ የተደረገው ታዲያ ያልተመጣጠነ መሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያዎች ፍላጎት ባለበትና በጣም በተጨናነቀችው ከተማ አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ባልተቻለበት ሁኔታ ነው፡፡

Free water to Kibra residents by Shofco

ጥንቃቄ በራስ መንገድ

ኪቤራ በኬንያ ዋና ከተማ የሚገኘው የናይሮቢ ግዛት ስድስት ሚሊዮን ህዝብ አካል ስትሆን፤ ከመሀል ከተማው በደቡብ ምዕራብ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ መጋቢት 13 ቀን በኬንያታ ናሽናል ሆስፒታል መገኘቱ ይፋ ሲሆን የኪቤራ ነዋሪዎች እጅጉን ደንግጠው ነበር፡፡

ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ነዋሪነቱ ከኪቤራ ብዙም ከማትርቀው ከካጂያዶ ግዛት ከኦንጋታ- ሮንጋይ መንደር ነበር፡፡ በወቅቱም አብዛኛዎቹ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ነበሩ፡፡ በመሆኑም የኪቤራ ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ አካባቢዎች እየሔዱ የእለት ተእለት የጉልበት ስራ መስራታቸውን እንዲያቆሙ ማሰሰቢያ ተሰጣቸው፡፡ መጀመሪያ ላይም ነዋሪዎቹ ብቸኛ የገቢ ምንጫቸውን ለማቆም መወሰን ተቸግረው ተሟግተው ነበር፡፡ 

እንደ ሌላው አለም መደበኛ ባልሆነ አሰፋፈር እንደሚኖሩ ህዝቦች ሁሉ የኪቤራ ነዋሪዎችም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ስራዎችን ወይም እንደ የሰው ቤት ሰራተኝነት እና ግንበኝነት ያሉ የተለመዱ ስራዎችን በመስራት የሚያገኙትን ገቢ በማብቃቃት ነው የሚኖሩት፡፡ ብዙ ሴቶችም በሴትኛ አዳሪነት ለመሰማራት ተገደዋል፡፡

በ2019 የኬንያ የህዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ መሰረት የስራ አጥ ቁጥር 50 በመቶ ሲሆን፤ እንደ ኪቤራ ባሉ አካባቢዎች አብዛኞቹ በድህነት የሚኖሩ ህዝቦች የቀን ገቢ 200 የኬንያ ሽልንግ (2 ዶላር) ነው፡፡

ቫይረሱን ለመቆጣጠር ሲባል መንግስት በአየር መንገድ በኩል የተጓዙ መንገደኞችና ከእነሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ወዳጆቻቸው 14 ቀን ለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ የሚያስገድድ ውሳኔ ማስተላለፉ ሁኔታውን እንዲቀየር አድርጓል፡፡ የበሽታው አስከፊነት በኪቤራ ነዋሪዎች ላይ ይበልጥ የከፋ መሆኑን በመረዳት ነዋሪዎቹ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማዳን የመንግስትና የጤና ሚኒስቴር ምክርን ተግባራዊ ለማድረግ ሀላፊነቱን ወሰዱ፡፡

እንቅስቃሴዎቹም በግል ድርጅቶች አማካኝበር ሐብቶችን በሚያንቀሳቅሱ በተለያዩ የማህበረሰብ መሪዎች አማካኝነት የሚመራ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም የሰው ልጆች ፍላጎቶች ላይ በሚሰጠው አገልግሎት የሚታወቀው ኪቤራ ታውን ሴንተር (Kibera Town Center) ነጻ የመጠጥ ውሀ የማቅረብ፣ የጽዳት አገልግሎት፣ የእጅ መታጠቢያ ጣቢያዎች እና ስለ ኮቪድ 19 ህዝብን የማንቃት ስራን የእለቱ በአካባቢው ይሰራል፡፡

KTC Daniel Futawax using public address system to reach to community

የጋራ ፈተናዎች

መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ህዝብ ተጨናንቆ ስለሚኖርባት ኪቤራ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የየተነሳ ሞት ቀጠና እንደምትሆን ተገምቶ ነበር፡፡ በደቡብ ምዕራብ ናይሮቢበ2.5 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ 250,000 ሰዎች የሚኖሩባት ኪቤራ በጣሙን በተጠጋጉ አካባቢዎች የተከበበች ናት፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በዚህ መኖሪያ 12 መንደሮች ይገኛሉ፡፡ እነርሱም ጋትዌኬራ፣ ሶዌቶ፣ ማኪና፣ ኪሲሙ ንዶጎ፣ ኪቺንጂኦ፣ ላይኒ ሳባ፣ ሲላንጋ፣ ሊን፣ ካይንዳ፣ ማሺሞኒ፣ ራይላ እና ሙሩ ናቸው፡፡

የአንድ መኖሪያ ቤት ስፋት 12 በ12 ጫማ ሲሆን፤ 8 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች እንደ ቤተሰብ ይኖሩበታል፡፡ እንዲህ ያለ ቤት የኪራይ ዋጋ በወር በአማካይ 2,000 የኬንያ ሽልንግ (19 ዶላር) ያህል ነው፡፡ ይህም ቋሚ የውሀ አቅርቦት በሌለበት ሁኔታ ነው፡፡ የኤሌትሪክ አቅርቦት ደግሞ በህገ-ወጥ መንገድ መስመር በማገናኘት፣ ያለአግባብ በተገኘ ቆጣሪ እና በጸሀይ ሐይል (ሶላር ፓወር) አማካኝነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

የአምረፍ ሄልዝ አፍሪካ የተሰኘው የጤና ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ጊቲንጂ ጋታሂ እንዳስታወቁት በኪቤራ አንድ ሰው በህይወት የሚቆይበት አማካይ እድሜ 30 ነው፡፡ የጨቅላ ህጻናት ሞት በከፍተኛ የሞት መጠን የሚመዘገብበት ሲሆን፤ 19 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት አምስት አመት ሳይሆናቸው ይሞታሉ ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ታዲያ በኪቤራ ለኮሮኖ ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ በእድሜ የገፉ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ 

“በሚያሳዝን ሁኔታ በኪቤራ የህጻናትና ወጣቶች በህይወት የመቆየት እድሜ አነስተኛ መሆኑን ቁጥሮች ያሳያሉ፡፡ የኮቪድ 19 ደግሞ ይበልጥ አነስተኛ ያደርገዋል” ይላሉ ጊታሂ፡፡

ምንም እንኳ የወጣት ህዝብ ቁጥር ቢልቅም በርካታ ነዋሪዎች ለኮቪድ 19 ይበልጥ ተጠቂ የሚያደርጋቸው ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት ያህል በኪቤራ ለሚኖሩ ወላጅ አልባ ህጻናት ምክንያት የሆነው እንደ እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያለ በሽታ ተጠቃሽ ነው፡፡ 

በኬንያ የሜዲሲን ሳንስ ፍሮንታየር ሜዲካል አስተባባሪ ዶክተር መሐመድ ሙኬ በብዛት ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል የተወሰኑትን ጠቅሰዋል፡፡ ከሌሎች የአባላዘር በሽታዎች በተጨማሪ እንደ ወባ፣ ማጅራት ገትር፣ የሳምባ ምች፣ የአንጀት በሽታ፣ ኮሌራ፣ ታይፎይድ የመሳሰሉት በሽታዎች ይገኙበታ፡፡ ኪቤራ የሚገኘው የአምረፍ ሄልዝ አፍሪካ የኬንያ ክሊኒክ እንዳስታወቀው የሳምባ ምች ህክምና ከሚያደርጉ ህመምተኞች መካከል 50 በመቶ ያህሉ ኤችአይቪ አለባቸው፡፡

አብዛኛዎቹ የኤችአይቪ ታማሚዎችም የእድሜ ማራዘሚያ መድሀኒት ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆናቸውንም ነው ዶክተር ሙኬ የገለጹት፡፡ ለዚህም ደግሞ ምክንያታቸው አብዛኞቹ መድሀኒቱን ስለማያገኙ ወይም ወጥ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ስለማይችሉ አሊያም ደግሞ መድሀኒቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ ምግቦችን ለማግኘት ስለማይችሉ ነው፡፡

ከመጠን በላይ በሰው የተጨናነቀና የንጽህና ጉድለት ከመኖሩ ባሻገር የንጹህ ውሀ አቅርቦት አለመኖር ኪቤራ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፊያ ምቹ ሜዳ ሆኗል፡፡

Kibera slums

በኪቤራ ንጹህ የመጠጥ ውሀ ማግኘት ብዙ ጊዜ አስቸጋሪና በቱቦ በሚገባ ፍሳሽም የተበከለ ነው፡፡ ሜዳ ላይ እዳሪን መጣልና መጸዳዳት የተለመደ ነው፡፡ ከመሸ በኋላ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶችን መጠቀም አስጊ በመሆኑ ሰዎች በፌስታል ተጸዳድተው ይጥላሉ፡፡ ሜዳ ላይ መጸዳዳትና በቀላሉ የእጅ መታጠቢያ አቅርቦት አለመኖሩ ችግሩን አባብሶታል፡፡

እነዚህ ጉዳዮችም በናይሮቢ ግዛት በውሀ ወለድ በሽታዎች የሚከሰት ሞት 40 በመቶ እንዲደርስ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በ2019 የኬንያ ህዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ መሰረት ኪቤራንና በአቅራቢያ የሚገኙ ጥሩ የኑሮ ሀኔታ ያላቸው መንደሮች ጭምር ባካተተው ኪብራ ክልል 84 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች የተሻሻለ ውሀ ያገኛሉ፡፡ ይሁንና 45 በመቶ የሚሆኑት ቤተሰቦች ውሀ የሚያገኙት ከህዝብ ቧንቧዎች ወይም ከቧንቧ ሲሆን፤ 16 በመቶ ያህሉ ከነጋዴዎች ይገዛሉ፡፡ 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከኪቤራ ውጭ ያሉ ባለጸጋ ቤተሰቦች ደግሞ መኖሪያ ቤታቸው በተዘረጋ የቧንቧ መስመር ውሀ ያገኛሉ፡፡

የንጹህ የመጠጥ ውሀ ዋጋ ውድነትና በቀላሉ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ህገ-ወጥ የውሀ ቱቦዎች ውሀ መውሰድ ተስፋፍቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ሰዎች ውሀ እንዲያገኙ እድል ቢሰጥም፤ ወደ ቱቦዎቹ ፍሳሽ በማስገባት የውሀ ማጠራቀሚያዎችን ይበክላል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የውሀ አቅርቦት ለብዙ አስርት አመት የቆየ መሻሻል ቢያሳይም፤ ባለፉት ሰባት አመታት ግን ቀንሶ ታይቷል፡፡ በ2015 የተሻሻለ የውሀ አቅርቦት መጠን 75 ከመቶ ይገመት የነበረ ሲሆን፤ በ2019 ደግሞ 65 በመቶ መሆኑ በብሔራዊ ጥናት ላይ ተመልክቷል፡፡

ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት በከተሞች አካባቢዎች በተለይም ደግም እንደ ኪቤራ ባሉ አካባቢዎች የዘፈቀደ ሰፈራ አማካኝነት የሰዎች ቁጥር መጨመር ነው፡፡ በከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሀን የሚጠቀሙ ቤተሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ከ2000 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ቀንሷል፡፡ 

በኪቤራ ውስጥ ብቻ በርካታ ተላላፊ በሽታዎች ሲኖሩ፤ አብዛኛዎቹም ገዳይ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም በ2019 ግንቦት ወር ላይ ኮሌራ ተከስቶ የነበረ ሲሆን፤ ሰዎች ተቀራርበው ስለሚኖሩ በቀላሉ ሊስፋፋ ችሏል፡፡ አሁን ደግሞ ኮሮና ቫይረስ በከፋ ሁኔታ ሊስፋፋ ይችላል፡፡

እነዚህ ችግሮች በቂ ፈተናዎች ባይሆኑ እንኳ ተገቢ የጤና አገልግሎት ለማግኘት ሲሞከር ይከሰታሉ፡፡ በኪቤራ ምንም አይነት አምቡላስ ዘልቆ መግባት አይችልም፡፡ ነዋሪዎቹ ሞተር ብስክሌት ወይም የፈረስ ጋሪዎችን ነው የሚጠቀሙት፡፡ 

ደሳሳዋ መንደር ኪቤራ በኬንያውያን ዘንድ በተለያዩ ጉዳዮች ትታወቃለች፡፡ ጥቂቶቹ ብቻ በአህጉርና አለምአቀፍ ደረጃ ተገልጸዋል፡፡ በእርግጥ የቱሪስት መስህብም አይደለችም፡፡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸው ናት፡፡

የመፍትሔ እርምጃዎች

በኪቤራ ጠባብ መንገዶች በሁሉም ግድግዳዎች ላይ ማለት ይቻላል ኮቪድ 19 አጠገባችን ነው የሚል ነዋሪውን የሚያሳስቡ መልዕክቶችን የያዙ ፖስተሮች ተለጥፈው ይታያሉ፡፡ 

ይህ ተግባር በኪቤራ ትልቁ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሆነው የሆፕ ፎር ኮሙኒቲስ መልካም ስራ ነው፡፡ ድርጅቱ በኪቤራ ሁሉም የመግቢያ ቦታዎች እና ህዝባዊ ቦታዎች ቢያንስ የእጅ መታጠቢያ ጣቢያ እንዲኖር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ 250 የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች በአውቶብስ መናኸሪያዎች፣ በገበያዎች፣ በዋና ዋና መደብሮች፣ በህዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ እና በሌሎችም አካባቢዎች በማዘጋጀት ያለ ክፍያ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡

የእጅ መታጠቢያ ጣቢያዎቹ በየአራት ሰአቱ መልሶ የሚሞሉ ሲሆን፤ በሌሎች ቦታዎች እንደ ህዝብ ብዛታቻው ከዚህም ባነሰ ሰአት መልሰው ይሞላሉ፡፡

“ቫይረሱን ከመከላከል አንጻር በአካባቢያችን ግንዛቤ ለመፍጠር በሞተር ብስክሌት እየዞርን በድምጽ ማጉያ እናስተምራለን” ሲሉ የሾፎኮ (Shofco) ስራ አስኪያጅ ኬኔዲ ኦዴድ ይናገራሉ፡፡ “ሞተር ብስክሌቶቹ ተስማሚ የሆኑ ድምጽ ማጉያዎች ያሏቸው ሲሆን፤ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ በድምጽ የተቀረጹ ትምህርት ሰጪ መልዕክቶች ይተላለፋሉ፡፡ ስለዚህ የሞተር አሽከርካሪው ስራ መልዕክቶች ለነዋሪዎች እንዲደርስ በዝግታ በዝግታ ማሽከርከር ብቻ ነው፡፡”

“ሾፎኮ ኮቪድ ቢኖርም ባይኖርም ማህበረሰባችን እጣ ፈንታቸውን ለመወሰን አቅም እንዳላቸው ያምናል፡፡ ስለዚህም በኪቤራ የድሆች ከተማ በሁሉም የመግቢያ አካባቢዎች የእጅ መታጠቢያ ጣቢያዎች እንዲኖሩ አድርገናል” ይላሉ ኦዴዴ፡፡ “ስለ ኮቪድ 19 የሚሰነዘሩ የተሳሳቱ መረጃዎችንም እየታገልን ግንዛቤ ለመፍጠር ቤት ለቤት እየሔድን እናስተምራለን፤ የእጅ ማጽጃዎችን እና ቤት ውስጥ የተሰራ ሳሙናዎችን እናከፋፍላለን” ሲሉም ኦዴድ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ኪቤራ በኬንያ ለኮሮና ቫይረስ ከተጋለጡ ማህበረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ ነዋሪዎቿ የእጅ መታጠብ አስፈላጊነትን በአግባቡ ለመተግበር የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተቀብለውታል፡፡ ምንም እንኳ ምቾት ባይኖረውም አዲስ ልማድ ሆኗል፡፡

በካቢኔ ጸሐፊው በሙታሂ ካግዌ የሚመራው የኬንያ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው መሰል ወረርሽኞች ሲከሰቱ በከተማ ንጽህና በጎደላቸው አካባቢዎች የሚከሰቱ ሞቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮቪድ 19 የሚያደርሰው አሳዛኝ ጉዳት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡

“ከመንግስት፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር በመተባበር ወረርሽኙ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዳያጠፋ እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ካግዌ ተናግረዋል፡፡

“ቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ የምንጋፈጥ ከሆነ ወይም በምንጋፈጥ ጊዜ ህይወታችን አንዳችን ከሌላችን፣ ከከተማችን፣ ከሀገራችንም ጋር የተያያዘ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ይህ ፈጽሞ ልንረሳው የማይገባ እውነታ ነው” በማለትም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የቀጠናው ረዳት ሀላፊ የሆኑት ዜፋኒያህ ኦምዎቻ በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የኪቤራ ነዋሪዎች ወደ አካባቢያቸው የሚመጡ አዳዲስ ሰዎችን በትኩረት ከማጤን ባሻገር የቤተሰቦቻቸውን፣ የዘመዶቻቸውንና ጓደኞቻቸውን እንቅስቃሴዎች በቅርበት እየተቆጣጠሩ ነው ብለዋል፡፡ ይህም አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን ለመግታትና የግድ ካልሆነ በስተቀር ቤት ውስጥ መቆየትን ለማበረታታት ነው፡፡

Hand sanitizer at bus station

የኪቤራ ነዋሪዎች አሁን የእጅ ንኪኪን ከማስወገድ አንጻር ክንዶቻቸውን በማነካካት አዲስ የሰላምታ አሰጣጥን እየተገበሩ ነው፡፡ ይህ የሰላምታ መንገድ በኬንያ በስፋት የተለመደ የሰላምታ አሰጣጥ እየሆነ የሚገኝ ሲሆን፤ ከተለመደው በእጅ የመጨባበጥ ሰላምታ አይነት የማያሰጋ ነው፡፡ የክንድ ሰላምታው ከህጻን እስከ አዋቂ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የክንድ ሰላምታው አሁን በሁሉም ቦታ ቤት ውስጥ ሳይቀር የተለመደ የሰላምታ መንገድ ሆኗል፡፡

የኪቤራ ነዋሪ ህዝብ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው፣ ታታሪ እና ፍላጎት ያላቸው ናቸው፡፡ በየቤታቸው ብዙ ውስንነቶች ቢኖሩም፣ የኪቤራ ህዝብ የኮቪ 19 ወረርሽኝን ለመታገል ሁሉንም ነዋሪ ያማከለ ማህበረሰባዊ አገልግሎት መፍጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡

ክህሎት ያላቸው ወጣቶች በህንጻ ግድግዳዎች ላይ ይጽፋሉ፤ ይስላሉ፡፡ የስዕል ክህሎታቸውን በገለጹባቸው ቦታዎችም ጥበባዊ በሆነ አገላለጽ የሰሯቸው ስራዎች የሚገኙ ሲሆን፤ የአፍና ፊት መሸፈኛ ጭምብል መልበስን፣ የእጅ መታጠብ እና አካላዊ ርቀትን አስፈላጊነትን የሚገልጹ ምስሎች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ስዕሎች ኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች እንኳ ግንዛቤ የሚሰጡ ናቸው፡፡

“ክህሎታችንን በመጠቀም የአካባቢያችን ነዋሪዎች ስለ ኮቪድ 19 መረጃ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ እነዚህ ስዕሎች የተማረውንም ያልተማረውንም ህብረተሰብ ክፍል በቫይረሱ ዙሪያ መረጃ የሚሰጡ ናቸው” በማለት በኪቤራ የህንጻ ላይ ስዕል ሰአሊው ስቴፈን ንዜላ ተናግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የኪቤራ ነዋሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል ሰፍተው አቅምን ባገናዘበ ዋጋ በ5 የኬንያ ሽልንግ (0.47 ዶላር) ይሸጣሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በነጻ ያከፋፍላሉ፡፡ እንደ ኬንያ ቀይ መስቀል ያሉ ድርጅቶች ደግሞ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር ሲሰጡ፤ አምረፍ ደግሞ በየሳምንቱ አካባቢውን በኬሚካል ያጸዳል፡፡ አድቬንቲስት ዴቨለፕመንት ኤንድ ሪሊፍ ኤጀንሲ የተባለው ሰብአዊ ድርጅት ደግሞ ተንቀሳቃሽ የእጅ መታጠቢያ ባልዲዎችን በተመረጡ ቦታዎች ያቀርባል፡፡

ካሮሊና ፎር ኪቤራ የተባለው ድርጅት በብሔራዊ መንግስት አማካኝነት ምግብና የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትን ‹አዶፕት ኤ ፋሚሊ› በተሰኘው ፕሮግራም ተጋላጭ ለሆኑ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ያከፋፍላል፡፡ የድርጅቱ ስትራቴጂክ ፓርትነርሺፕስ ዳይሬክተር የሆኑት ቤት-አን ከችማ እንዳስታወቁት እስከአሁን በፕሮግራሙ አማካኝነት ወደ 100 የሚጠጉ ቤተሰቦች እና 300 ተማሪዎች ከርሀብና ከድህነት ለመታደግ ተችሏል፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ወሮችም ተጨማሪ ሰዎችን ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል፡፡ 

ፕላን ኢንተርናሽናል ኬንያም በአካባቢው የኮቪድ 19 ወረርሽን ለመቀነስ የሚሰሩ ድርጅቶችን በመቀላቀል እየሰራ ይገኛል፡፡

የቀጠናው የፓርላማ አባል የሆኑት ቤናርድ ኦኮዝ እንዳስታወቁት በኪቤራ ሁለት ትልልቅ የገበያ ቦታዎችን፣ ሁሉንም መንደሮችና መኖሪያ አካባቢዎችን እንዲሁም የፍሳሽ ማወገጃዎችን ለማጽዳት ብቻ መንግስት 1,800 ወጣቶችን ከኪቤራ ቀጥሯል፡፡ እያንዳንዳቸውም በቀን 600 የኬንያ ሽልንግ (5.60 ዶላር) ያገኛሉ፡፡ እነሱንም አልባሌ ቦታና ተግባር ላይም ከመዋል ታድጓቸዋል፡፡

እነዚህ አነስተኛ እንቅስቃሴዎች በኪቤራ ቆሻሻ አካባቢ የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አንጻር ፍሬ መስጠት ችለዋል፡፡ ኬንያውያን የቫይረሱን አስከፊነት በሌላው አለም ላይ መመልከት ችለው ነበር፡፡ በኪቤራ እና በሌሎች በሀገሪቱ በሚገኙ ሌሎች የቆሸሹ አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች በዚህ አስፈሪ በሆነ ጊዜ እንኳ ህብረት ፈጥሯል፤ በእርግጥም ተስፋ አለ!

ምስጋና፤ ይህ ዘገባ የተጠናከረው ከኢንፎናይል InfoNile ጋር በመተባበር ከኮድ ፎር አፍሪካ ድጋፍና ከፑልቲዘር ሴንተር እና ናሽናል ጂኦግራፊክ ሶሳይቲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts