ግሪን ሆሪዞን የምግብ ፕሮጀክት በጀበል ላዱ የህብረተሰቡን ህይወት ሲያሻሽል የደቡብ ሱዳንን የርሀብ ቀውስንም ለመቀነስ ሰብሎችን እያመረተ ነው

ግሪን ሆሪዞን የምግብ ፕሮጀክት በጀበል ላዱ የህብረተሰቡን ህይወት ሲያሻሽል የደቡብ ሱዳንን የርሀብ ቀውስንም ለመቀነስ ሰብሎችን እያመረተ ነው

በደቡብ ሱዳን ከ2006 ጀምሮ ከ2.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ መሬት በውጭ ኢንቨስተሮች ተይዟል

በዴቪድ ሞኖ ዳንጋ

ይህ ዘገባ የተጠናከረው በፑልቲዘር ድጋፍ በኢንፎ ናይል እና ኮድ ፎር አፍሪካ ትብብር ነው

የአለማችን ወጣቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ርሀብና ድህነትን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን በመታገል ላይ ናት፡፡ ሀገሪቷ ራሷ ለረጅም ጊዜ ትመኝ የነበረውን ሰላም እንዳታጣጥም ስጋት ለሆነው እና መቋጫ ላላገኘው ግጭት የራሷን ድርሻ አላት፡፡ 

ከ2013 ጀምሮ ሀገሪቱ በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በጁላይ ወር 2017 እንደገና ባገረሸው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተፈናቀሉበት በማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ድርቅ መከሰቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ህዝቦቿን ለመመገብ በመታገል ላይ ናት፡፡

በሀገሪቱ የምግብ እጥረትን ለመቀነስ በኖቬምበር 2015 መንግስት የምግብ ምርት ያለውን ክፍተት ለማስተካከል ግሪን ሆሪዞን የተባለውን የእስራኤሉን ኩባንያ ጋር ውል ፈጸመ፡፡

ግሪን ሆሪዞን በእስራኤሎች ድጋፍ የሚተገበር የመንግስት ፕሮጀክት ሲሆን፤ የአካባቢው ገበሬዎችን በማሰልጠን እና ለሀገር ውስጥና አለምአቀፍ ገበያዎች ምግብ በማምረት ድህነትን ለመቀነስ እና ኑሮን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው፡፡

‹‹የስምምነቱ ዋነኛ ክፍል ኩባንያው በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኬር ለደቡብ ሱዳን የገጠር ገበሬዎች በስጦታ ባበረከቱት 1.000 ትራክተሮች መስራት ነበር›› የሚሉት የግብርና ሚኒስቴር አስተባባሪና የግሪን ሆሪዞን ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ ዶክተር ኤርኒዮ ባላሲዮ ፒተር ናቸው፡፡

ሀላፊው እንደሚሉት ለፕሮጀክቱ ከጁባ ከተማ ዳርቻ 37 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በጀበል ላዱ 500 ሔክታር መሬት ተመድቦለታል፡፡ 

ግሪን ሆሪዞን በማዕከላዊ ኢኳቶሪያ በጁባና ጀበል ላዱ፣ በምስራቃዊ ኢኳቶሪያ ግዛት በቦር ጆንግሌ ግዛት፣ በሬንክ አፐር ናይል እና በቶሪት ዘመናዊ እርሻዎች አሉት፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የማህብረሰብ የንግድ ግብርና ፕሮጀክቶች በዋኡ፣ ጎክ እና ሩምቤክ ከተሞች አሉት፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ማረጋገጫ ያላቸው ዘሮችን፣ ቁሶችን፣ ምርጥ ዘሮችንና የቴክኒክ ድጋፍን በመስጠት የሰብል ምርቶችን ለመጨመር ገበሬዎችን የሚያበቁ ሲሆኑ፤ ገበሬዎቹም ምርቱን ከሸጡ በኋላ ለግሪን ሆሪዞን በፐርሰንት መልሰው መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡

‹‹እኛ ድጋፍ የምናደርገው ገበሬው አንዴ ምርቱን ካመረተ በኋላ እንዲሰበስበው፣ ወደ ገበያ እንዲወስደው፣ እንዲሸጠው ከዚያም ደግሞ ትርፉን እንዲያካፍል ነው›› የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዮአሽ ዞሀ ናቸው፡፡

እንደ ዮአሽ ከሆነ ከ2016 ጀምሮ ፕሮጀክቱ 1.000 ቶን በቆሎ፣ 200 ቶን ማሽላ፣ 100 ቶን ለውዝ፣ 200 ቶን ሩዝ፣ 250 ቶን ሙዝ እና 300 ቶን ትኩስ አትክልቶችን አምርቷል፡፡ በዚህ ወር የሚሰበሰብ 2.500 ቶን የደረሰ ሽንኩርት ይገኛል፡፡

matooke

በኩባንያው የሚመረቱ ፍራፍሬና አትክልቶች ሀብሀብ፣ ዱባ፣ ጎመን፣ ሱኩማ ዊኪ፣ ቲማቲም፣ ፓፓያ፣ ቃሪያና ሽንኩርት ጭምር ይገኙበታል፡፡ 

የግብርና ሚንስትሩ እንደገለጹት ከሆነ ኩባንያው ከደቡብ ሱዳን አጠቃላይ የምግብ ምርት አንድ አስረኛውን ያህል ያመርታል፡፡ 

ኩባንያው እስከ አሁን ወደ ውጭ ሀገር ምርት ባይልክም በቀጣዩ ማርች ወር መጨረሻ ላይ ግን የተወሰኑ የሽንኩርት ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ማሰባቸውን ዮአሽ ተናግረዋል፡፡

‹‹ፕሮጀክቱ እስከአሁን ትርፋማ አይደለም፡፡ በ2019 ወደ ገበያው ሰብረን ለመግባትና በ2020 ትርፋማ እንሆናለን ብለን ተስፋ እናርጋለን›› ብለዋል፡፡

ላንድ ማትሪክስ ከተባለው ገለልተኛ ተቋም በተገኘ አሀዝ መሰረት ከ2006 ጀምሮ ወደ 2.5 ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ በደቡብ ሱዳን 15 ስምምነት የተፈጸመ ሲሆን፤ በዋናነትም በውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ሌሎች 9 ስምምነቶች በድርድር ላይ ሲሆኑ፤ ከተሳካ ተጨማሪ 1.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንደሚያዝ ዳታው አመልክቷል፡፡

በዩናይትድ ስቴስት በሚገኘው በኦክላንድ ኢንስቲትዩት መረጃ መሰረት የመሬት ይዞታ የተጀመረው በ2011 ሀገሪቷ ነጻነቷን ከማግኘቷ አስቀድሞ ነው፡፡ በጃንዋሪ 2011 እስክትገነጠል ድረስ ባሉት አራት አመታት ውስጥ ለባዮፊውል፣ ለኢኮቱሪዝም፣ ለግብርና እና ደን ልማት ኢንቨስትመንት ከአምስት ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ተፈርሞ መወሰዱን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የአካባቢው ሰራተኞች ቅነሳ

ከጁባ አቅራቢያ የሚገኘው የጀበል ላዱ መሬት ለዘመናት ለግብርና ስራ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በ1978 የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ጋፋር ኒምሪ ያኔ ሱዳን ግዛት የነበረውን መሬት ከመንግስት የግብርና እርሻዎች ለማሽላ አንደኛው አድርገው ማዘጋጀታቸውን በጀበል ላዱ ግዛት ሀላፊ የሆኑት ሱልጣን አንጀሎ ላዱ ይናገራሉ፡፡

መሬቱ ለአካባቢው ህብረተሰብ ማህበረሰቡ ከመተላለፉ በፊት በ1990ዎቹ የኢኳቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ባለቤትነት የተያዘ ነበር፡፡

ሱልጣን አንጀሎ እንደሚሉት የአሁኖቹ ኢንቨስተሮች ወደ አካባቢው ከመምጣታቸው በፊት መሬቱ ጥቅም አልባ ነበር፡፡ ምክንያቱም መንግስት የግብርና እንቅስቃሴዎችን አቆመ፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ደግሞ መሰል ግዙፍ የሆኑ የእርሻ ስራዎችን የመስራት አቅም አልነበረውም፡፡

አሁን የእስራኤሉ እርሻ በካናዳው ድርጅት በጋራ የሚመራ የካናዳ የኢኮኖሚ ልማት ድጋፍ ለደቡብ ሱዳን (CEDASS) በሚባለው የካናዳ ድርጅት በጥምረት የሚመራ ሲሆን፤ በሱዳን መንግስት ፈቃድ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ለዘላቂ የእርሻ ፕሮጀክት መሬቱን መንጥሮና ያረሰው በ2006 ነበር፡፡ ከ2006 ጀምሮ ድርጅቱ – CEDASS ለማህበረሰቡ የስራ እድል የፈጠሩ የኢኮኖሚና የግብርና ስልጠናዎችን መምራት ችሏል፡፡ 

በላዱ ግዛት የግዌሬኬክ መንደር ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ሱልጣን ጄናቢዮ ኬንይ ሎኩ እንደተናገሩት ካናዳውያኑ በአካባቢው ለ8 አመታት በቆዩበት ጊዜያት ከማህበረሰቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው፡፡

ድርጅቱ እንደ ትምህርት ቤት፣ የህክምና አገልግሎቶች፣ የህጻናት ደህንነት እና የእናቶች ጤና በመሳሰሉ የሰብአዊ ተኮር እንቅስቃሴዎች ላይ ይበልጥ ለማተኮር ፕሮጀክቱን ትቶታል፡፡ ነገር ግን እርሻውን ለማስተዳደር ከእስራኤሉ የግብርና ግሪን ሆሪዞን ፕሮጀክት ጋር ጥምረት ፈጥሯል፡፡

እንደ ሴዳስ ከሆነ ግሪን ሆሪዞን ተልዕኮው በአለም ላይ በማህበረሰብ ዘመናዊነት፣ መረጋጋት እና ደህንነት ላይ መስራት በመሆኑ ለመሪ የእርሻ አጋርነት የተመቸ ነው፡፡

ግሪን ሆሪዞን ለእያንዳንዱ አባወራ የምርቱን የተወሰነ ድርሻ በመስጠት እና በግሪን ሆሪዞን ክሊኒክ በሳምንት ሶስት ጊዜ የህክምና አገልግሎትን በማቅረብ የአካባቢው ማህበረሰብ ህይወት እንዲሻሻል አድርጓል ሲሉ ሀላፊው ኬኒይ ተናግረዋል፡፡

Onions 1

 ‹‹በመጀመሪያ እና በሁለተኛ አመት ላይ ከእኛ ጋር በጥሩ ሁኔታ ሰርተዋል፡፡ የህክምና አገልግሎት አቅርበውልናል፡፡ ባለፈው አመት ለማህረሰቡ 100 ጆንያ የበቆሎ ዱቄት በየቤቱ የሚከፋፈል ሰጥተውናል›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያው በርካታ የአካባቢው ሰዎች በእርሻው ውስጥ እንዲሰሩ አድርጓል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶክተር ኢርኒዮ ግሪን ሆሪዞን ፕሮጀክት በአመት ውስጥ ከ362 ሰዎች በላይ በቋሚነት ቀጥሮ አሰርቷል፤ ከ350 እስከ 1.234 ሰዎችን ደግሞ በጊዜያዊነት አሰርቷል፡፡ 

አስተዳዳሪው እንደሚሉት ኩባንያው አረም በማረም የተሰማሩ ሴቶችን ጨምሮ በርካታ የአካባቢውን ነዋሪ ሰራተኞች ቀንሶ በእነሱ ቦታም ከጁባ ሰዎችን በማምጣት እንዲሰሩ አድርጓል፡፡ 

ሱልጣል ኬኒይ እንደሚሉት ህብረተሰቡ በኩባንያው አስተዳደር ደስተኛ አይደለም፡፡ መሬቱ የህብረተሰቡ እንደመሆኑ መጠን በእርሻ ፕሮጀክቱ ላይ ከሌላ አካባቢ ሰዎችን ከማምጣት ይልቅ ለአካባቢው ህብረተሰብ ቅድሚያ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡ 

‹‹መሬቱ የእኛ ነው፡፡ ለዚህም ነው እዚህ ከሚካሔድ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ መሆን ያለብን፡፡ ለምንድነው እኛ ስራ እንዳንሰራ የምንደረገው?›› ሲሉም ኬኒይ ይጠይቃሉ፡፡

የግሪን ሆሪዞን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዮአሽ ዞሀር ግን ‹‹ያለአግባብ ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ የለም›› ይላሉ፡፡ 

‹‹ግሪን ሆሪዞን የደቡብ ሱዳንን የሰራተኛ ህግና ደንቦችን ተከትሎ ነው የሚሰራው፡፡ የተወሰኑ ሰራተኞች ሀላፊነታቸውን ቸል በማለታቸው ወይም በስነ ምግባራቸው የተነሳ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል፡፡ በአብዛኛውም በስራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው ነው›› ብለዋል ዮአሽ፡፡ 

‹‹ያልተገባ ነገር ደርሶብኛል የሚል ሰራተኛ ካለ በማንኛውም ጊዜ እኔጋ መጥቶ ሊያናግረኝ ይችላል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ እያንዳንዱን ጉዳይ እመለከታለሁ›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በእርጥም ለኩባንያው ሰራተኞችን ከሌላ አካባቢ ከማምጣት ይልቅ ከህብረተሰቡ ውስጥ መቅጠር የተሻለ እንደሆነም ዮአሽ ይስማማሉ፡፡

‹‹ማንኛውም የስራ ቅጥር ወይም ስንብት የሚካሔደው በብቃት፣ በስራ ተነሳሺነት እና ባህሪይ ነው›› ሲሉም ለጁባ ሞኒተር በኢሜይል በላኩት ምላሽ ገልጸዋል፡፡

የላዱ ግዛት ህብረተሰብ ሰብሳቢ ሲሊሊያ ላኩ ዋኒ በበኩላቸው ግሪን ሆሪዞን ፕሮጀክት ከጁቤክ ግዛት ጋር በመማከር ሰራተኞችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ቢቀጥር የተሻለ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡ 

‹‹በእርሻው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እነማን እንደሆኑ እንድንከታተልና እንድንመለከት መንግስት ደብዳቤ የሚጽፍልን ለእኛ ነው›› ይላሉ ሰብሳቢዋ፡፡

መንግስት የእርሻ ፕሮጀክት ለአካባቢው ማህበረሰብ ማምጣቱን የሚያደንቁት ዋኒ፤ ማህበረሰቡ ግን ተጠቃሚ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ 

‹‹ማህበረሰቡ በአስተዳደር ቦታዎች ጭምር በእርሻ ፕሮጀክቱ ውስጥ ተቀጣሪ መሆን አለባቸው፡፡ ምክንቱያም እርሻው የሆነ ሰማይ ላይ ተንጠልጥሎ የሚገኝ አይደለም፡፡ በሰዎች መሬት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚያ ባለቤቶች ደግሞ በህይወት ይገኛሉ፡፡ የመንግስት ፕሮጀክቶች እንኳ ቢሆኑ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ መሆን አለበት›› ብለዋል፡፡

በኩባንያ ውስጥ ስራቸውን ካጡ ሰራተኞች መካከከል ስሙ እንይጠቀስ የፈለገ አንደኛው እንዳስታወቀው የእስራኤሉ ፕሮጀክት ከካናዳዎቹ ድርጅት የበለጠ የግብርናው ፕሮጀክት ላይ ከፍተኛ አብዮት ፈጥሯል፡፡ 

በተለይም የእርሻው አመራሮች ከሰራተኞች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠራቸው እርሻዎቹ አሁን በጥሩ ሁኔታ እየተመራ ነው ብሏል፡፡ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዮአሽ ዞሀር ሁሌም አንዳች ስህተት ከተፈጠረ ፈጣን ምላሽ ነው የሚሰጡት ብሏል፡፡ 

ይሁንና አመራሩ በፍጥነት ስለሚቀያየር ችግሮች እንደሚፈጠሩ ነው የገለጸው፡፡ ይህም አዲስ አመራር በመጣ ቁጥር የሚሰጠውን የስራ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ለሰራተኛው አስቸጋሪ እንደሆነ ነው ያስረዳው፡፡ 

‹‹ሰራተኞቹ በአግባቡ እንደማይስተናገዱ ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ እኔም በራሴ ላይ የደረሰውን እመሰክራለሁ›› የሚለው የቀድሞው ተቀጣሪ፤ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰራተኞች ከሀላፊነታቸው መልቀቃቸውን ያስረዳል፡፡

ግሪን ሆሪዞን ለሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ እድገትና ልማት ሲል ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠሩ ይጠቅመዋል ብሏል፡፡ 

‹‹እኔ የማቀርበው ምክር የግሪን ሆሪዞን አመራሮች ፖሊሲያቸውን በማሻሻል ከማህበረሰቡ ጋር ጥሩ ግንኙነትን እንዲኖራቸው ነው›› ብሏል፡፡ ‹‹ግሪን ሆሪዞን የማህበረሰቡን ክብር የማይጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ እድገት አይኖረውም፡፡ ማህበረሰቡም የግሪን ሆሪዞንን ፖሊሲዎች ካላከበረ፤ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡

‹‹ከማህበረሰቡ ጋር ጥሩ የሥራ ግንኙነት ከፈጠሩ ማህበረሰቡ ግሪን ሆሪዞን እርሻውን ለማስፋፋት የሚያስችለውን በቂ መሬት ይሰጣቸዋል›› ሲልም የቀድሞው ተቀጣሪ አክሎ ተናግሯል፡፡

የአካባቢው የመንግስት አስተዳደር ግን በግውሬኬክ መንደር ህብረተሰቡ ከስራ ላይ እንዲቀነስ ተደርጓል የሚለውን ቅሬታ አስተባብሏል፡፡

የላዱ ግዛት ኮሚሽነር የተከበሩ ካንዲዶ ስዋካ ላዱ ግሪን ሆሪዞን በጀበል ላዱ እያካሔደ ያለውን የግብርና ልማት እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡

‹‹በማህረሰብህ ውስጥ እንደ ጀበል ላዱ እርሻ አይነት ዘመናዊ እርሻ ካለ ፈቃደኛ መሆን አለብህ፡፡ ምክንያቱም የአካባቢው ነዋሪዎች መጎዳት የለባቸውምና›› ይላሉ ኮሚሽነር ላዱ፡፡

እንደዚያ ያለ ኢንቨስትመንት በአካባቢው ገበያዎች የሸቀጦች ዋጋን የሚያሻሽሉ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት ስለሚችሉ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ብሔራዊ የመንግስት ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠንም ‹‹አሁን ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መሆን አለብን፡፡ ምግብ ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች የድጋፍ አይነቶች ለህብረተሰቡ ሊቀርብ ይገባል፡፡ ነገር ግን እርሻው በህብረተሰቡ ውስጥ እያለ የአካባቢው ህብረተሰብ ካልሰራ አሉታዊ ተጽዕኖ ነው የሚያመጣው፡፡ ለዚህም ነው ኢንቨስትመንት ካለ የመጀመሪያው ተጠቃሚ ሊሆን የሚገባው የአካባቢው ማህበረሰብ መሆን አለበት የምንለው›› በማለት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የመሬት ህግ 2019 የመሬት ባለቤትነትን ሲያብራራው የህዝብ፣ የማህረሰብ ወይም የግል መሬት ብሎ ነው፡፡ የህዝብ መሬት በደቡብ ሱዳን በሚገኙ ህዝብ በጋራ የተያዘ እና በእምነት በሚመለከተው የመንግስት አካል ስር የሚገኝ ነው፡፡ የማህበረሰብ መሬት ደግሞ በማህበረሰቡ የተያዘ መሬት በጎሳ፣ በነዋሪነት ወይም ፍላጎት መሰረት የሚገለጽ ነው ሲል ህጉ ያብራራል፡፡

የግል መሬት በማንኛውም ግለሰብ በይዞታነት ወይ በሊዝ ባለቤትነት የተመዘገበ ማንኛውም መሬት/ ወይም ማንኛውም መሬት በህግ የግል መሆኑ የተገለጸ ነው፡፡ የጀበል ላዱ መሬት በማህበረሰብ መሬት ዘርፍ የሚወድቅ ነው፡፡ 

የምግብ እጥረት

በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት ባለፈው አመት ሴፕቴምር ወር ላይ የተካሔደው የምግብ ደህንነት ጥናት እንደሚያመለክተው ደቡብ ሱዳን ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ለመመገብ ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ያስፈልጋታል፡፡

እያዳንዱን ደቡብ ሱዳናዊ በቀን ሶስት ጊዜ ለመመገብ ደግሞ ወደ 1.2 ሚሊዮን ቶን ምግብ እንደሚያስፈልግ የግብርና ምርት ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ሎሮ ጆርጅ ሌጁ ይናገራሉ፡፡

በዚህ አመት በሰብል ምርት አለመኖር የተነሳ በሀገሪቱ እየጨመረ የመጣውን አስፈሪ ርሀብ ለመቀነስ ሀገሪቱ በአብዛኛው የጥራጥሬ ሰብሎች ምርት ያስፈልጋታል ሲሉ ሌጁ ለጁባ ሞኒተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ግብርና ሚኒስቴር ከሆነ ደቡብ ሱዳን በ2018 ያመረተችው 404.109 ቶን ምግብ ብቻ ነው፡፡ ይህም አሁን ያለው የህዝብ ብዛት አንጻር ከሚያስፈልገው አነስተኛ ደረጃ በታች ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት በዚህ አመት ይፋ ባደረገው አሀዝ መሰረት የደቡብ ሱዳን ህዝብ ብዛት 13.2 ሚሊዮን እንደሚሆን ይገመታል፡፡ 

ድርቅ እና የእርስ በእርስ ግጭቱ በሀገሪቱ የተከሰተውን የርሀብ ቀውስ አባብሰውታል፡፡ አሁንም ቀጥሎ በሚገኘው የእርስ በእርስ ግጭት የተነሳ ብዙ ህዝብ ምግብ አምራች ከሆኑ ከተሞች ከሴንትራል ኢኳቶሪያ ዬኢ፣ ከምዕራባዊ ኢኳቶሪያ እና ቶሪት ያምቢዮ፣ እና ከምስራቃዊ ኢኳቶሪያ ማግዊ ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመሰደድ ላይ ናቸው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የጃንዋሪ ወር ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ በግጭቱ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ተሰደዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ክትትል በሚያደርግባቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኙትን 193.219 ጨምሮ እዚያው ደቡብ ሱዳን ውስጥ 1.97 ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅሏል፡፡

Water melon 2

የአለም ምግብ ፕሮግራም የተቀናጀ የምግብ ደህንነት ምዕራፍ ደረጃ ሪፖርት የ2018 መጨረሻ እና የ2019 የመጀመሪያ ሩብ አመትን የምግብ ደህንነት አለመኖርን ደረጃ የተነበየ ሲሆን፤ 5.3 ሚሊዮን ሰዎች በመላ ሀገሪቱ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልጉ ይፋ አድርጓል፡፡

ዶክተር ሌጁ እንደተናገሩት ርሀብ በምስራቃዊ እና ማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ግዛቶች ክፉኛ ተንሰራፍቷል፡፡ የግሪን ሆሪዞን ፕሮጀክት ደግሞ በጁባ የምግብ ምርቶች በአካባቢው ገበያዎች የሚሸጡ በመሆናቸው ይህንን ቀውስ የሚቀንስ ነው፡፡

ይሁንና ፕሮጀክቱ አሁንም ድረስ በጨቅላ እድሜ ላይ ነው ብለዋል ሌጁ፡፡ በሁለተኛ ምዕራፍ እርሻው ሀገሪቱ ከነዳጅ ውጪ ያላትን ገቢ ለማሻሻል የከብት እንስሳቶችና የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን አምርቶ ወደ ውጭ ሀገሮች ይልካል ሲሉ ኤርኒዮ ገልጸዋል፡፡

የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ጉዳዮች ሚኒስትር ሚዛናዊ ያልሆነው ንግድ ደቡብ ሱዳን በሀገር ውስጥ የምታመርታቸውን ብዙ የግብርና ምርቶቿን ወደ ውጭ ሀገሮች እንዳትልክ እንቅፋት ሆኖባታል፡፡

የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የእቅድ ጄኔራል ዳይሬክተር የሆኑት ስቴፈን ዶክተር ማታቲያስ ‹‹ሚዛናዊ ንግድ ለመፍጠር ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባቸውን ምርቶች ማለዋወጥ አለብን›› ይላሉ፡፡

‹‹የደቡብ ሱዳን ንግድ የአንድ ወገን ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ሀገሪቱ ለፍጆታ ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባ እና ትንሽ ደግሞ ወደ ውጭ የምትልክበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው ከሰላም ጋር የበለጠ ብዙ እናመርታለን፡፡ እንደ ግሪን ሆሪዞን እውነተኛ ኢንቨስተሮችም ወደ ሀገራችን ይመጣሉ›› ሲሉ ማታቲያስ ተናግረዋል፡፡

የእርስ በእርስ ጦርቱ የሀገሪቱን ወደ ውጭ የመላክ አቅሟ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ ማታቲያስ፡፡ ነገር ግን ደቡብ ሱዳን በቆሎ፣ ሩዝ፣ ባቄላ፣ ሎዝ፣ የአረብ እጣን፣ እንጨት፣ ቡና፣ ጥጥ፣ አሳ፣ ቆንጥር፣ የከብት እንስሳት እና የከብቶች ቆዳን ጨምሮ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ ከፍተኛ አቅም እንዳላት ይገልጻሉ፡፡

እንደ ግሪን ሆሪዞን ያሉ የውጭ ኩባንያዎች በሀገሪቱ የምግብ ምርት እና ወደ ውጭ የመላክ አቅም እንዲሻሻል ማድረጋቸውን ዶክተር ሌጁ አስታውቀዋል፡፡  

‹‹ግሪን ሆሪዞን በቆሎ፣ ሩዝ፣ ማሽላ እና አትክልቶችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሰብል ምርቶች እንዴት እንደምናሳድግ ጥሩ ልምድ ሰጥቶናል›› ብለዋል፡፡

ኢርኒዮም ይህንኑ አስተያየት ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹ይህ ፕሮጀክት በውስጡ ለሚገኙት ገበሬዎችና ሰራተኞች የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ እድል ሰጥቷል ብለዋል፡፡

በጀበል ላዱ ማህበረሰብ ላይ ተጽዕኖ

ህብረተሰቡ ግሪን ሆሪዞን በአካባቢው የፈጠረውን ተጽዕኖ በተመለከተ የተለያየ ሀሳብ ነው ያለው፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ነዋሪና ገበሬ የሆነው ቪታ ሳሙኤል እንደተናገረው ኩባንያው የእርሻ ቁሶች፣ ዘሮችን እና የመጠጥ ውሀን በጣም ለተቸገሩት በማቅረብ ጭምር በተለያዩ መንገዶች ማህበረሰቡን ሲጠቅም ቆይቷል፡፡

‹‹የግሪን ሆሪዞን ትልቁ ጠቀሜታ የጀበል ላዱ ወጣቶች የስራ እድል መስጠቱ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ነዋሪዎች የሚመቹ ስራዎችን አምጥተዋል›› ሲል ቪታ ተናግሯል፡፡

‹‹በሀዘንም ሆነ በደስታ ጊዜ ግሪን ሆሪዞን የመጠጥ ውሀ፣ ሽንኩርት እና አንዳንድ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለምሳሌ ወደ ከተማ መጓጓዣ ያቀርብልናል፡፡ ከመንደራችን ወደ ከተማ የሚወስደን መጓጓዣ ማግኘት ቀላል አይደለም›› ብለዋል፡፡

ካትሪና ፖኒ የስድስት ልጆች እናት ሲሆኑ፤ ግሪን ሆሪዞን በአካባቢው ብቸኛ ትምህርት ቤት ለሆነውና የልጅ ልጆቻቸው ለሚማሩበት ለግዌሬኬክ አንደኛ ደረጃ ትምርህት ቤት የመማሪያ ቁሶችን እንደሰጠ ይናገራሉ፡፡ የ58 አመቷ ወይዘሮ አክለውም ኩባንያው ምርት በሚሰበስብበት ጊዜም ከምርቱ የተወሰነውን ያህል ለአካባቢው ማህበረሰብ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ይህ አይነቱን ተግባር ብዙ ኩባንያዎች ሲፈጽሙት ያልተሰማ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

ኩባንያው በመንደራቸው ብቸኛ ለሆነው ክሊኒክ መድሀኒቶችን በማቅረብ የህክምና አገልግሎት እንዲሻሻል ቢያደርግና የመጠጥ ውሀ ለማውጣት የሚያስችል የጉድጓድ መቆፈሪያን ቢያቀርብ መልካም እንደሆነ ነው ፖኒ የሚያስገነዝቡት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከናይል ወንዝ የተበከለ ውሀን በቀጥታ እንደሚጠጡና ለበሽታ እንደሚዳረጉም ነው ያስታወቁት፡፡

ዶክተር ሌጁ እንዳስታወቁት እንደ ግሪን ሆሪዞን አይነቶቹ የመንግስትን የምግብ ደህንነት ፕሮጀክት ላይ የሚሰሩ የውጭ ሀገር ኩባንያዎች መንግስት የምግብ ደህንነት ነጻነት ፕሮጀክትን በ2014 ከጀመረ በኋላ በሀገሪቱ የምግብ ምርት እንዲሻሻል አድርገዋል፡፡

‹‹ግሪን ሆሪዞን በቆሎ፣ ሩዝ፣ ማሽላ እና አትክልቶችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰብሎችንም ምርቶች እንዴት እንደምናሳድግ ጥሩ ልምድ ሰጥቶናል›› ብለዋል፡፡

      አዲስ የመስኖ ቴክኖሎጂ

የእስራኤሉ ኩባንያ የሚመራው ፕሮጀክት በቢሊዮኖች የሚቆጠር የደቡብ ሱዳን ፓውንድ የሚያወጣ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለደቡብ ሱዳን ህዝብ በማስተዋወቁ አድናቆትን አትርፏል፡፡

‹‹እነርሱ የሚሰሯቸው በመስኖ የማጠጣት ቴክኖሎጂ ሲስተሞች በጣም ጥሩ ናቸው›› ይላሉ የግብርና ምርት ጄኔራል ዳይሬክተር የሆኑት ሌጁ፡፡

ኩባንያው ለሰብል እህሎች እየተሽከረከረ ውሀ የሚያጠጣ መሳሪያን በኒው ላንድ ፋርም ተክሏል፡፡ መሬት የማጽዳቱንና ዝግጅቱን ጨምሮ አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱ ወደ 1.000.000.000 (1ቢሊዮን) የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ይሆናል ብለዋል ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዮአሽ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያው የጠብታ ውሀን የማጠጣት ዘዴን ለሙዝ ተክሎችና በአትክልቶች ላይ የሙከራ እርሻ በሆነውና በጁባ በሰሜናዊ ባሪ ፓያም አካባቢ በሉሪ ሱሬ በሚገኘው ኒው ላንድ እርሻ ላይ ይጠቀማል፡፡ በጀበል ላዱ እና በኒው ላንድ እርሻዎች በመስኖ አጠቃቀሙ የሚፈጀው ውሀ መጠን ወደ 200.000 እና 50.000 ኩቢክ ሜትር ነው፡፡

በናይል ወንዝ በየእያንዳንዱ ሰአት ወደ 6 ሚሊዮን ሜትር ኩቢክ ሜትር ውሀ እንደሚያልፍ ዮአሽ ይገልጻሉ፡፡

‹‹የእኛ እርሻ በአመት ውስጥ የሚጠቀመው ውሀ በናይል ወንዝ በግማሽ ሰአት የሚያልፈውን ያህል ነው›› ይላሉ፡፡

‹‹ለማለት የፈለኩት ነገር በናይል በጣም ብዙ መጠን ያለው ውሀ ስላለ እንደዚህ አይነት እርሻዎችን መስራትና ከናይል ወንዝ ውሀ መጠቀም ይቻላል ነው፡፡ እስከአሁን ድረስም ደቡብ ሱዳን ከናይል ከምታገኘው ድርሻ ምንም ነገር አልተነካም›› ሲሉም ዮአሽ ይመሰክራሉ፡፡

ሀገሪቱ ራሷን ለመቻል 50.000 ሄክታር መሬት የሚለማ እና ጥሩ ግብርና እንደምትፈልግ ያስረዳሉ፡፡

በውሀ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር በሀይድሮሎጂ እና ጥናት ዳይሮክቶሬት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ኢንጂነር ሮበርት ፒተር ዛካዮ በበኩላቸው ግሪን ሆሪዞን የሚጠቀምበት በመስኖ የማጠጣት ዘዴ ውሀን ቆጥቦ ለመጠቀም ብቁ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹የጠብታ እና የተሸከርካሪ ማሽን ውሀ የማጠጣት ዘዴ በግልጽ በቱቦ በመጠቀም ከማጠጣት ዘዴ ጋር ሲነጻጸር በጣም ብቁ ነው፡፡ ምክንያቱም ውሀ የሚወጣው አስፈላጊ ለሆነ ነገር ብቻ ነውና›› ብለዋል፡፡
ተጨማሪ ዘገባ እና አርትኦት አኒካ ማክጊኒስ

Print Friendly, PDF & Email

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts