ጽጌረዳ፦ የአባይ ወንዝን እና ማህበረሰቡን የነጠለው አበባ

ጽጌረዳ፦ የአባይ ወንዝን እና ማህበረሰቡን የነጠለው አበባ

በአየለ አዲሱ አምበሉ

ይህ ዘገባ የተጠናከረው በኢንፎ ናይል እና ኮድ ፎር አፍሪካ ትብብር በፑልቲዘር ሴንተር ድጋፍ ነው፡፡

አቶ አብርሃም በቀለ የ58 አመት ጎልማሳ ሲሆኑ፤ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ አቅራቢያ የምትገኘው የመንሸንቲ መንደር ነዋሪ ናቸው፡፡ አስራ አንድ የቤተሰባቸውን አባላትን ጨምረው የሚያስተዳሩበትን መሬታቸውን በ2008 የጽጌረዳ አበባን ለሚያመርቱ ኢንቨስተር ከተሰጠባቸው በኋላ ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል፡፡

‹‹ያለ ተገቢ ካሳ ነበር ከመሬታችን እንድንፈናቀል የተደረግነው›› ሲሉ በንዴት የሚናገሩት አቶ አብርሃም፤‹‹አሁን ያለምንም መሬት፣ ምግብና ውሀ ለመኖር እየታገልን ነው›› ይላሉ፡፡

አቶ አብርሀም አሁን በባህርዳር ከተማ የቀን ሰራ በመስራት በሳምንት የሚያገኙትን 15 ዶላር ቤተሰባቸውን ለመመገብ ያውሉታል፡፡

የእሳቸው ታሪክ መሬታቸውን ለአበባ ልማትና የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጪ ሀገር ለሚልኩ ባለሀብቶች የተሰጠባቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህይወት መስታወት ነው፡፡

Picture13

ኢትዮጵያ ከኬንያ በመቀጠል በርካታ የአበባ ምርትን ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኔዘርላንድስ በመላክ ሁለተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ናት፡፡ 

ከኢትዮጵያ የእጽዋት አምራች ላኪዎች ማህበር የተገኘ አሀዝ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ በ2017 ከአበባ ምርት እና ሌሎች የእጽዋት ውጤቶች ሽያጭ 300 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ ባለፈው የበጀት አመት ደግሞ የእጽዋት ኢንዱስትሪው በዋናነትም ወደ ውጭ ሀገር ከሚላክ አበባ ምርት 271 ሚሊዮን ዶላር ተገኘቷል፡፡

ብሔራዊ እቅድ ከሚሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ብርሀኔ እንደሚናገሩት ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ላይ ከአበቦች ኢንዱስትሪው ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዳለች፡፡ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስርሜሽን እቅድ (ከ2015/16 – 2019/20) ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማድረስ እጅግ ጠቃሚ መሰረት እንደሆነ የሚታመንበት ነው፡፡ 

ነገር ግን ሁሉም ነገር መልካም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የአበቦች ኢንዱስትሪ ሲያድግ በየአመቱ መሬታቸው ለአበባ አምራች ኢንቨስተሮች የሚወሰድባቸው 3000 ሰዎች ከመሬታቸው እንደሚፈናቀሉ ከአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ደህንነት ፕሮግራም አስተባባሪ ቢሮ የተገኘ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የመሬት ንጥቂያን በተመለከተ በመንግስት፣ በኩባንያዎች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በሚዲያ እና በዜጎች ትብብር መረጃ የሚያሰባስበው ላንድ ማትሪክስ ዳታቤዝ በኢትዮጵያ በቅርብ አስርት አመታት ውስጥ 1.4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መወሰዱን መዝግቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ በመላ ሀገሪቱ 120 ስምምነቶች ተፈጽመዋል፡፡ 15 ስምምነቶች በድርድር ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሲጠናቀቅም ተጨማሪ 0.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን እንዲወሰድ ሊያደርግ ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ ከተነጠቁ መሬቶች መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ለውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች የተሰጡ ናቸው፡፡ የህንድ ኩባንያዎች አብዛኛውን መሬት የያዙ ሲሆን፤ በተለይም በባዮፊውል እና የአበባ ምርትን ጨምሮ በሰፋፊ የእርሻ ስራ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እንደ ሳኡዲ አረቢያ፣ አሜሪካን፣ ጣሊያን፣ ማሌዥያ፣ ቻይና፣ ኦስትሪያ፣ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ካናዳ እና ሲንጋፖር ያሉ ሀገሮችም ትልልቅ ኢንቨስተሮች ይገኙበታል፡፡

ልክ እንደ አብርሀም ሁሉ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ዘንዘልማ መንደር ነዋሪ የሆነችው የ27 አመቷ ህይወቴ ያዜ የአካባቢው ማህረሰብ በየጊዜው እየቀነሱ ‹‹በአንድ ወቅት የአያቶቻችን በሆነው መሬት ላይ ስደተኛ እየሆንን ነው›› ስትል ትናገራለች፡፡ 

ማህበረሰቡ የተወሰደበት መሬቱን ብቻ ሳይሆን የውሀ አካላትንም እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹የተፈጥሮ ውሀ አለን፡፡ ነገር ግን ጠጥተን አናውቅም፡፡ ኢንቨስተሮች ወስደውታል›› 

‹‹የተፈጥሮ ውሀ አለን፡፡ ነገር ግን ጠጥተን አናውቅም፡፡ ኢንቨስተሮች ወስደውታል›› 

ህይወቴ የምትኖርበት የዘንዘልማ መንደር ከአባይ ወንዝ ሶስት ኪሎ ሜትር፤ ከአባይ ምንጭ ከጣና ሀይቅ 4.7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

እንደ አማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ኢትዮጵያ በቅርቡ ለእጽዋት ተክሎች ጥቅም የሚውል 6.000 ሄክታር መሬትን ባህር ዳርን ጨምሮ በጣና ሀይቅ እና በአባይ ወንዝ በኩል ያሉ ቦታዎችን አዘጋጅታለች፡፡

በኢትዮጵያ ግዙፍ የሆኑ 10 የእጽዋት ተክሎች ኢንቨስትመንት ስራዎች በጣና ሀይቅ እና በአባይ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኙ ሲሆን፤ በጣና ሀይቅ በኩል 1.200 ሄክታር፤ በአባይ ወንዝ በኩል ደግሞ ሌላ 2.000 ሄክታር መሬት ይሸፍናሉ፡፡ ይህ መረጃ ከኢትዮጵያ የዕጽዋት አምራቾች ላኪዎች ማህበር መረጃ ላይ የሰፈረ ሲሆን፤ እንደ ጆቫኒ አልፋኖ ፋርም፣ ኮንዶር ፋርምስ፣ ፎንታና ሆርቲካቸር፣ ፒና ፍላወርስ፣ አሪኒ ፍላወርስ፣ ሶሎ አርጎ ቴክ፣ ታል ፍላወርስ እና ጆይ ቴክፍሬሽ የመሳሰሉ ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች በአካባቢው ትኩረት ያደረጉት የሚለማ መሬትን ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ውሀን እና ሁለቱንም የውሀ አካላትንም ጭምር እንጂ!

የአባይ ወንዝ ተፋሰስ ባለስልጣን ሀላፊ የሆኑት አስራት ጸሐይ፤ ከነዋሪዎቹ ጋር በማነጻጸር በአካባቢው የሚካሔዱ የአበቦች ኢንቨስትመንቶች የበለጠ ውሀን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡

‹‹በደረቃማ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ ሰዎች በሳምንት በሚያገኙት አምስት ሌትር ውሀ ለመኖር ሲታገሉ፤ እንስሳት ደግሞ በብዛት ይሞታሉ›› የሚሉት ሀላፊው፤ ‹‹የጽጌረዳ አበባ ደግሞ አንዱ ግንድ በሳምንት በአማካይ ሰባት ሌትር ውሀ ይፈልጋል›› ይላሉ፡፡  

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የውሀ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ አደም ወርቁ፤ ‹‹ይህ ሁኔታ በክልሉ የውሀ አካላትን ቀስ በቀስ እንደሚያደርቅ›› ያስባሉ፡፡

በክልሉ የአበባ ምርቶች ‹‹በየአመቱ ሙሉ ውሀን የያዙ 20.000 የኦሊምፒክ መዋኛ ገንዳዎች›› ያህል ውሀን በየአመቱ ይፈልጋሉ›› የሚሉት በአማራ ክልል በውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የውሀ ተመራማሪ የሆኑት መሰለች ዘላለም ናቸው፡፡ ይህ ውሀ ደግሞ የሚወሰደው ከጣና ሀይቅ እና ከአባይ ወንዝ ነው፡፡

ዶክተር መሳይ አበበ በኢትዮጵያ የአበባው ዘርፍ ተንታኝ ሲሆኑ፤ ያልተገባ የውሀ ሀብት የሚጠቀመውን የአበባ ምርት ኢንዱስትሪውን ይተቻሉ፡፡

‹‹ይህ ሁኔታ ያልተመጣጠነ የማዳበሪያ አጠቃቀም፣ በተባይ ማጥፊያ መርዞች እና በዘፈቀደ የፍሳሽ አወጋገድ የተነሳ የሚመጣውን የአፈር፣ ውሀ እና አየር መበከልን የሚያስከትል ነው›› ይላሉ፡፡

ከመጠን በላይ በንጥረ ነገሮች የበለጸገ ከመሆኑ የተነሳም የተበከለው ውሀ በቀላሉ በውሀ አካላት ውስጥ እጽዋቶች ጥቅጥቅ ብለው እንዲያድጉ ያደርጋል፡፡ በርካታ ጥናቶችና የዜና ዘገባዎች እንደሚያመለክቱትም የጣና ሀይቅ በእምቦጭ አረም በመሸፈን ሊጠፋ ተቃርቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በቀላሉ ወደ ጎረቤት አባይ ወንዝ እና ጣና ሀይቅ የሚያመሩ የማዳበሪያና የተባይ ማጥፊያ መርዞችን ስለሚጠቀሙ በርካታ የአበባ እርሻዎች ላይ ቅሬታዎች ቀርበዋል፡፡ ታደለ የሺዋስ ትዛዙ የእርሻ እና አካባቢ ጥበቃ ሳይንስ ተመራማሪ ሲሆኑ፤ ‹‹ኬሚካሎቹ በቀላሉ ከምድር በታች ወዳለ ውሀ ሰርጸው ይገባሉ›› ይላሉ፡፡

የተቆረጡ አበባዎች ለገበያ ሲቀርቡ፤ የሚረግፉ ቅጠሎችን የመሳሰሉ ተረፈ ምርቶች ያሉ የሚወገዱ ዝቃጭ ኬሚካሎችን የያዙ ተረፈ ምርቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዝቃጭ ኬሚካሎች በአግባቡ ካልተወገዱ በሰው ልጆች እና እንስሳትም ጤና ላይ ጉዳትን ያስከትላሉ፡፡ 

Picture18
Local pond near a flower project in Amhara region.

ለአብነት ያህልም፤ በአካባቢው ገበሬዎች መካከል አንዱ የሆነው ሸጋ በላይ እንደሚናገረው ማህረሰቡ የገጠመው ችግር ‹‹የእርሻ መሬቱ መቀነሱ ብቻ አይደለም፡፡ የተባይ ማጥፊያ መርዞች ከተረጩ በኋላ ከብቶችም መሞታቸው ነው››

‹‹ለክልሉ ባስልጣናት ቅሬታችንን አቅርበን ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም መፍትሔ አላገኘንም፡፡ እኛ እየተቸገርን መንግስት ግን ታክስ በመሰብሰብ ተጠቃሚ ሆኗል›› በማለት ሸጋ አምርሮ ይናገራል፡፡ የኢትዮጵያ የዕጽዋት ልማት ኤጀንሲ የመንግስት ተቋም ሲሆን፤ አበባዎችን፣ ፍራፍሬ እና አትክልቶችን እንዲሁም የእጽዋትና ከብት እርባታ ዘርፉን አዋህዶ የያዘውን የእጽዋት ሴክተሩን ለመደገፍ በዋናነት የተቋቋመ ነው፡፡

የኤጀንሲው ጄኔራል ዳይሬክተር አለም ወልደገሪማ እንደሚናገሩት በኢትዮጵያ የእጽዋት ሴክተሩ ያደገው ‹‹ኢትዮጵያ ለአበባ አልሚ ኢንቨስተሮች የሰጠችው አፈርን፣ ውሀን፣ ስነ ምህድራዊ እና ለገበያ የቀረቡ እድሎችን መጠቀምን›› ትኩረት ባደረገው አነስተኛው የግሉ ዘርፍ ነበር ነበር፡፡ 

የአባይ ውሀ ለአባይ ህዝቦች የተሰኘ ኢኒሼቲቭ አቀንቃኝ የሆነው ሰለሞን ወርቁ እንደሚናገረው የአባይ ወንዝ ምንጭ በሆነው አካባቢ ለግብርና ስራ መሬትን የወሰዱ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ከአካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ አይደግፏቸውም፡፡ 

‹‹በልማት ስም ሰፋፊ መሬቶችንና ሀብቶችን ወስደዋል፤ ግን ምንም ልማት አላየንም›› በማለት ሰለሞን ይሞግታል፡፡ 

ከእነዚህ የእርሻ መሬቶች መካከል የተወሰኑት የታቀደላቸውን አላማ ሙሉ በሙሉ ባለመዋላቸው ቅሬታ ቀርቦባቸዋል፡፡

አቶ አለም ወልደገሪማ የተወሰኑ ኢንቨስተሮች የተሰጣቸውን መሬት በአግባቡ እንዳልተጠቀሙበት አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኤጀንሲያቸው ለ25 አልሚዎች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቀዋል፡፡

መሬት የተነጠቁ ተጎጂዎች ይናገራሉ

በባህር ዳር ከተማ የቤዛዊት መንደር ነዋሪ የሆነችው የ28 አመቷ አመለወርቅ ያዚ መንግስት የአካባቢውን ማህበረሰብ ቸል በማለት ለውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ማድላቱን ትወቅሳለች፡፡

‹‹ተስፋ ላላቸው የአካባቢው ወጣቶች በሮች ሁሉ ዝግ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለውጭ ሀገር ዜጎች ክፍት ናቸው›› ትላለች አመለወርቅ፡፡ የአካባቢው ገበሬዎች ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት አስቴር ተሰማ በበኩላቸው ምንም እንኳ በአካባቢው ያሉ የአበባ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሰሩ አብዛኞቹ ሰራተኞች ተግተው ቢሰሩም፤ ‹‹የሚያገኙት ገቢ ግን የማይረባ በመሆኑ ህይወታቸውን ከባድ አድርጎባቸዋል፡፡ ኢንቨስተሮቹ ግን በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያተርፋሉ›› ትላለች፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የእጽዋት አልሚ ኩባንያዎች ላይ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች በተደጋጋሚ የሚነገረው ኩባንያዎቹ አትራፊ እየሆኑ ቢገኙም፤ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ግን ምንም አይነት እድገት አያሳዩም፡፡

በእነዚህ የውጭ ሀገር የእጽዋት ኩባንያዎች ውስጥ ከሚሰሩት መካከል የዘጌ መንደር ነዋሪ የሆነው የ33 አመቱ ዮርዳኖስ ማንደፍሮ ይገኝበታል፡፡ ዮርዳኖስ አለቆቹ ከስራ ያሰናብቱኛል በሚል ስጋት የሚሰራበትን ድርጅት ይፋ እንዳናደርግ አሳስቦናል፡፡ እርሱ በሚሰራበት ድርጅት ብዙ ሰራተኞች በወር የሚከፈላቸው 30 ዩሮ እንደሆነ ገልጾልና፡፡ 

የኢንቨስተሮችና የአካባቢው መንግስት ለቅሬታዎች ምላሽ አላቸው

የጆቫኒ አልፋኖ እርሻ ተወካይ የሆኑት ሳሚ ባንቹ ‹‹ትምህርት ቤቶችን እና የጤና ተቋማት የመሳሰሉ የልማት ስራዎችን በመስራት ከአካባቢው ማህረሰብ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን›› ይናገራሉ፡፡ 

በተመሳሳይ ሁኔታ በጽሑፍ በተዘጋጀ ምላሽ የሰጡን የየመኒ እርሻ ተወካይ መሐመድ ‹‹ማንኛውንም ነገር በተቀመጠው መስፈርት መሰረትነው›› ብለዋል፡፡

Picture8

‹‹የተባይ ማጥፊያ አጠቃቀምን በተመለከተ በአውሮፓ በተፈቀደው መሰረት ነው የምንጠቀመው፡፡ የፍትሀዊ ንግድ ማረጋገጫ ሰርፍኬት አለን›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል መንግስት የኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ይኼነው በላይ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ በእጽዋት ኢንቨስትመንት የተነሳ በርካታ የአካባቢው ገበሬዎች መፈናቀላቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በአካባቢው ህብረተሰብ መስዋዕትነት የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ትኩረት ያደረገውን ‹‹የመንግስትን ፖሊሲ›› ይተቻሉ፡፡ 

ወደ መፍትሔው ማምራት

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራ መግስታዊ ያልሆነው ፎረም ፎር ኢቫይሮመንት የተባለው ተቋም በ2008 ይፋ ያደረው ሪፖርት እና በኢትዮጵያዊው ተመራማሪ አስናቀ ደመና በ2016 የቀረበው ሪፖርት ጨምሮ በርካታ ጥናቶች በኢትዮጵያ የመሬት መቀማት ችግር በዋና ባለይዞታዎቹ ማህረሰብ ዘንድ የፈጠረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳያሉ፡፡ የሚለሙ መሬቶች፣ ያልተነኩ ደኖች፣ እና የዛፍ መሬቶች ለባዮፊውል ፕሮጀክቶች ተከፋፍለዋል፡፡ ይህም ተፈጥሯዊ ስነ ምህዳርን የሚያጠፋ መሆኑን ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ የዕጽዋት ዘርፉ ባለሞያ እና ተንታኝ የሆኖት ዶክተር መሳይ ከበደ የኢትዮጵያ መንግስት የሠዎችን ከመሬታቸው መፈናቀልና መባረር መመርመር እና ገበሬዎችም መልሰው መስፈራቸውንና በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የነዋሪዎች መብትን ያከበረ ተገቢውን ካሳ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ ከውሀ አካላት ለአበባ እርሻ የሚወጣ ውሀ በዘላቂነት ለማውጣት የሚያስችል ግልጽ መመሪያዎችን ለማዘጋጀት ከእጽዋት አምራቾቾ እና ላኪዎች ማህበር ጋር በመሆን መስራት እንደሚገባውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

‹‹በክልሉ ሁሉም የአበባ እርሻዎች የውሀ ሀብትን ለመጠበቅ የሚረዳውን የጠብታ ውሀ መስኖ አጠቃቀም ዘዴን እንዲተገብሩ መገደድ አለባቸው›› በማለትም ዶክተር መሳይ የመፍትሔ ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ፡፡

ለተጨማሪ መረጃ እና አርትኦት በፍሬድሪክ ሙጊራ

Originally published in Zehabesha

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts