የህጎች አለመረጋገጥ በደቡብ ሱዳን የመሬት ነጠቃን አቀጣጥሎታል

የህጎች አለመረጋገጥ በደቡብ ሱዳን የመሬት ነጠቃን አቀጣጥሎታል

ከ2006 ጀምሮ 2.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ይዘዋል

በፖል ጂምቦ

የአለማችን ወጣቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን በመልካም ምክንያቶች ሳይሆን የእርስ በእርስ ጦርነቶችን ጨምሮ በጎሳ ግጭቶችና በመሬት ነጠቃዎች የአለምአቀፍ የዜና ርዕሰ ጉዳይ ሆና ትኩረትን ስባለች፡፡ 

ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እያነሰ በመጣው መሬት እና በውሀ ሀብቶች የተነሳ ብዙ የጎሳ ግጭቶች ከአስር አመት ያነሰ እድሜ ባለቤት በሆነችው ሀገር መንጭተዋል፡፡ 

ድህነት በከፍተኛ ሁኔታ በተንሰራፋባቸው ቦታዎች ደግሞ በስፋት የተካሔደው የህዝብ መሬት ነጠቃ የማህበረሰቡ መሬት በከፍተኛ ሁኔታ ተነጥቆ ከብቶችን በትንሽዬ የግጦሽ መሬት ላይ ያስቀረ እና ባህላዊ የውሀ መጠጫ ቦታዎቻቸው ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ አጸያፊው የመሬት ንጥቂያ ህመሙ የአባይ ወንዝን ዋንኛ የውሀ ማግኛ ምንጩ ለሆነው ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ አይደለም፡፡

ለነጋዴ ኢንቨስተሮች መንገዶችን ለማመቻቸት ሲባል ደን የማራቆት ተግባር መቀጠሉም እንዲሁ የወንዙን ውሀ ለመስኖ በመዋሉ የተነሳ የአባይ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡ 

Sheng DA firm a Chinese firm in Gumbo Rajaf Payam along the River Nile. 1

በአባይ ወንዝ ዙሪያ መሬት ለመውሰድ በውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች የሚደረገው ሽሚያ ለም የሆነውን የህበረተሰቡን ሄክታር መሬት ያለአካባቢው ማህረሰብ ተሳትፎ እንዲከፋፈሉ ተደርገዋል፡፡ 

በመንግስት ኩባንያዎች፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ በሚዲያ እና በዜጎች ተሳትፎ ትብብር የመሬት ነጠቃን በተመለከተ መረጃ የሚሰራው ላንድ ዳታ ማትሪክስ መሰረት በደቡብ ሱዳን ከ2006 ጀምሮ 2.5 ሚሊዮን ሄክታር ያህል መሬት መወሰዱን መዝግቧል፡፡ የመሬት ነጠቃ በመሬቱ ላይ መብት ካላቸው ባለይዞታዎች ፍላጎት ውጪ መሬቱን መውሰድ ማለት ነው፡፡ 

የዚህ አብዛኛው መሬት ከዩናይትድ አረብ ኢምሬት፣ ከሱዳን፣ ከኖርዌይ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከሳኡዲ አረቢያ እና ከግብጽ ኩባንያዎች ጋር ለተፈጸሙ 11 ስምምነቶች የተከፋፈለ ነው፡፡ 

የመሬት ባለቤትነት በስፋት ያለው በትልቁ ኢኳቶሪያ ክልል እና በተወሰኑ የባሄር ጋዜል ክፍሎች ነው፡፡ በእነዚህ ክልሎች የተካሔደው ሰፊ የሆነ የመሬት ነጠቃ የተፈጥሮ ሀብት ማውጣት፣ በነዳጅ ቁፋሮ እና በግብርና ምርት ስራዎች ላይ በማተኮር ነበር ሲል አርቲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በ2008 የዩናይትድ አረብ ኢምሬትሱ አልኤን ብሔራዊ የዱር እንስሳት ድርጅት የአደን ካምፖችን ለመገንባት ለ30 አመት ባለቤትነት 1.7 ሚሊየን ሄክታር መሬትን ወስዷል፡፡

በ2009 ደግሞ የግብጹ ካላ ሆልዲንግ የተባለው ኩባንያ ወደ ግብጽ የሚላኩ እህሎችን ለማምረት በናይል ወንዝ በመስኖ የሚለማ 105.000 ሄክታር መሬትን ወስዷል፡፡ 

በ2007 የኖርዌዩ ግሪን ሪሶርስ ኩባንያ በማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ግዛት የወይራ ዛፍ ደኖችን ለማልማት 180.000 ሄክታር መሬት ወስዷል፡፡ በአለምአቀፍ ስምምነት መሰረት የአየር ንብረት ተጽኖን ለመከላከል የካርቦን የሚለቁ ኩባንያዎች ከእጽዋት አምራች ኩባንያዎች ካርበን ልቀት የሚከላከሉበትን ካርበን መግዛት ይችላሉ፡፡ 

ነገር ግን ይህ አይነቱ የእጽዋት ልማት በረጅም ጊዜ ሒደት ተከላ በስነ ምህዳር ላይ እና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው፡፡ ካሊፎርኒያ መቀመጫውን ያደረገው ኦክላንድ ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ በኡጋንዳ አረንጓዴ ሀብቶች የአካባቢውን ነዋሪዎች ያባረረ፣ የውሀ እና የግጦሽ መሬት የማግኘት መብታቸውን የገደበ፣ የተፈጥሮን ስነ ምህዳር የሚያጠፋ ኬሚካሎችን እንዲጠቀሙ ያደረጋቸው መሆኑ ተገልጻል፡፡

በሌላ የመሬት ስምምነቶች በ2010 የቀድሞው የንጉስ አብደላህ ልዩ ሀይል እና የሳኡዲ ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ልዑል ባንዳር ቢን ሱልታን አል ሳውድ በግዊት ዩኒቲ ግዛት 100.000 ሄክታር መሬት ይዞታ አላቸው፡፡ አሁን ግን ይህ መሬት ያለ ጥቅም እንዲሁ ይገኛል፡፡ 

የናይል መሬቶች መቆራረስ

በጁባ ደቡብ ከተማ 10ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከጉምቦ ወደ ራጃ መንገድ ሲኬድ 10ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ዝርግ መሬት በአብዛኛው ተቆራርሶ በአባይ ወንዝ በኩል ያሉ በርካታ መሬቶች ለውጭ ሀገር ኢቨስተሮች መሰጠታቸው በግልጽ ይታወቃል፡፡

አንዳንድ ሳይቶች ከፍ አድርገው ባቆሙት ምልክት ላይ የግል ንብረታቸው መሆኑን ለመጠቆም በትልቁ ባቆሙት የምልክት ሰሌዳ ላይ ‹‹የእከሌ ንብረት›› … ‹‹ለሽያጭ ያልቀረበ›› የሚሉ መልዕክቶችን አኑረውበታል፡፡ ሌሎች ደግሞ በኮንክሪት ግድግዳ የተከፋፈሉ ሲሆን፤ በመሬቶቹ ላይ የእርሻ ስራ እየተሰራባቸው ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ 

አንዳንዶቹ የምልክት ማስታወቂያዎቹ በቻይንኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፡፡ የናይል ወንዝ መሬቶች ከሩቅ የአለማችን ቦታዎች ሳይቀር ምን ያህል አማላይ እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአትክልት ምርት እና የኮንስትራክሽን ስራ በሚከናወንበት አንደኛው በኩል “Sheng DA, Chinese Street No 9, Gumbo, Rajaf Payam”  የሚል ጽሑፍ ይነበባል፡፡

በታጠረው ቅጥር ውስጥ ብዙ ወንድ እና ሴት የቻይና ዜጎች ከግዙፍ ጥቁርና ጤናማ ውሾቻቸው ጋር ይገኛሉ፡፡ እንግሊዘኛ የማይናገሩና በአካላዊ እንቅስቃሴ ምልክቶች የእርሻ ስራቸውን የሚሰሩ ናቸው፡፡ ጥልቅ የመሬት ቁፋሮ የሚያደርግ መሳሪያ፣ የማረሻና የመዝሪያ ትራክተሮችን ጨምሮ ግዙፍ የእርሻ ማሽኖች ነበሯቸው፡፡ ከ2016 ጦርነት የተረፉ ናቸው፡፡ 

አሁን ላይ ግን ማሽኖቹ በጥቃቅን የአትክልት እርሻ እና በኮንስትራክሽን ግንባታ ስራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ 

በርካታ ተመሳሳይ ክፍልፋይ መሬቶች በተርታ ሆነው ይታያሉ፡፡ ሁሉም ወደ ናይል ወንዝ ዳርቻ የተዘረጉ ናቸው፡፡

በአቅራቢያው በኩል ደግሞ የተወሰኑ የተከለሉ ቅጥሮች በከፍተኛ ደረጃ በታጠቁ ጠባቀዎች ዙሪያቸውን ይጠበቃሉ፡፡ ስፋታቸው 20 ጫማ እና 40 ጫማ የሆነ ኮንቴይነሮች ተደራርበው ይታያሉ፡፡ የኮንቴይነር አቅርቦቶቹ  የኮንቴይነር ጭነት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለቤትነት የተመዘገቡ ናቸው፡፡

የባሪ ጎሳ አባል የሆኑት የ48 አመቷ ፖሊና ዋኒ በቤተሰቧ መሬት ላይ በተፈጸመው የመሬት ነጠቃ ታዝናለች፡፡ 

በጉምቦ እና ራጃፍ መካከል የሚገኘው ሰፊ መሬት የባሪ ማህበረሰብ እንደሆነ የሰባት ልጀች እናት የሆነ ትናገራለች፡፡ ነገር ግን በ1980ዎቹ ግጭቱ ከተነሳ ጀምሮ ግለሰቦች መሬታቸውን ጥለው እንዲወጡ ግፊት አድርገውባቸዋል፡፡

‹‹በ1983 አንያና 1 በተባለው ግዛት በተፈጠረ ጦርነት ወቅት የሆኑ ሰዎች እዚህ መጥተው ታጣቂዎች በአካባበያችን እንደሚያሰፍሩ ነገሩን፡፡ ወዲያውኑም መንደሩን ማስተዳደር ጀመሩ፡… ስለዚህም ይህንን መንደር ለቀው ወጡ፡፡ የተወሰንነው ደግሞ ከላይ ከወንዙ በመጣ ከፍተኛ ጎርፍ የተነሳ ተፈናቀልን›› በማለት ፖሊና ያስታውሳሉ፡፡

በዚህን ጊዜ ነበር የተወሱ ደላሎች በአባይ ወንዝ በኩል ያለውን ለም መሬት ላይ ያተኮሩት፡፡

አሁን አሁን አንዳንድ ፖለቲከኞችና ደላሎች ለግዙፍ ኩባንያዎች የህዝብ የሆነውን ለም መሬት ለእርሻ ስራ በሚል በሊዝ ለመስጠት ስምምነቶችን እንደሚፈረሙ ይናገራሉ፡፡

‹‹በወንዙ አካባቢ ያሉ ትናንሽ ከፍታ ቦታዎችን ሳይቀር እንደወሰዱብን ታምናላችሁ?›› እነዚያ 10 በ10 ጫማ ስፋት ያላቸው ቦታዎች ባለቤት አላቸው›› ይላሉ ፖሊና በእጃቸው ወደ ትንሽዬዋ ድንጋያማ ቦታ እየጠቆሙ፡፡

የወንድ አያታቸው የሰፊ መሬት ባለቤት እንደነበሩ የሚናገሩት ፖሊና፤ አሁን ላይ ግን በጣም በትንሽዬ ቁራጭ መሬት ላይ ቤተሰባቸውን ለማኖርና አነስተኛ የግብርና ስራ ለመስራት መገደዳቸውን ይገልጻሉ፡፡

ለስላሳ መጠጦችን የሚያመርቱና የሚያሰሩ አንዳንድ ኢንቨስተሮች በቀጥታ ጥሰው የሚገቡት ወደ ናይል ወንዝ ዳርቻዎች ነው፡፡ ወዲያውም ወደ ውሀው የሚያመሩ የኮንክሪት ግድግዳዎችን ይገነባሉ፡፡

The sign post of Sgeng DA firm on Chinese Street No 9 on the Gumbo Rajaf Paym road. 1

ብዙ ባይሆንም በሆቴል ኢንዱስትሪ የተሰማሩት ኢንቨስተሮችም ጭምር በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ አትራፊ በሆነው የሆቴል ቢዝነስ ልቀው ለመውጣት የራሳቸው የሆነ የሐይቅ ዳርቻን ከልለዋል፡፡

ማለቂያ በሌለው የመሬትና ጫናዎች የተነሳ የናይል ወንዝ የሚኝበትን አቅጣጫ እንደገና መልሶ ለመግለጽ ተገዷል፡፡

ግብርና ንግድ የምግብ እጥረትን የማስቀረት እቅዶች

መንግስት የውጭ ሀገር ኩባንያዎች በብዛት ምግብ አምርተው በሀገሪቱ የተከሰተውን የምግብ እጥረት እንደሚጠፋ ተስፋን በመሰነቅ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ያበረታታል የሚሉት ዶክተር ሎሮ ጆርጅ ለጁ ሉጎር የግብርና ምርት እና ኤክስቴንሽን ሰርቪስ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡

ከ7.1 ሚሎዮን በላይ ሰዎች ማለትም ከደቡብ ሱዳን ህዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ የሆነው የእርስ በእርስ ጦርነቱ ባስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ የተነሳ እንዲሁም በቅርብ አመታት በተከሰተ ድርቅ አማካኝነት ለመቀንጨር አደጋ የተጋለጠ ነው፡፡

እንደ የኖርዌይ ህዘብ ለደቡብ ሱዳን ተራድኦ ድርጅት መረጃ እስከ 2016 ጦርነት ድረስ የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግም እና የአረብ ሀገሮችን ኩባንያዎችን ጨምሮ የውጭ ኢንቨስተሮች የተፈጥሮ ሀብት ለማውጣት፣ ለነዳጅ ቁፋሮ እና ለግብርና ስራ የሀገሪቱን 10 በመቶ መሬት ይዘዋል፡፡

ነገር ግን በ2016 በደቡብ ሱዳን ግጭት ሲያንሰራራ ብዙ የውጭ ሀገር ግዙፍ የግብርና ኩባንያዎች ሀገሪቷን ለቀው ሔደዋል፡፡ እነዚህ እርሻዎች አሁንም ድረስ ያለ ጥቅም ተቀምጠዋል፡፡

‹‹አሁን በአነስተኛ የምግብ ምርት የተነሳ የሀገሪቱ ሶስት አራተኛ ክፍል በርሀብ ይመታል፡፡ በመስኖ የሚለማ እርሻ የለንም፡፡ የንግድ እርሻዎች የሉንም፡፡ ከ2016 ጦርነት በፊት ግን ነበሩን›› ይላሉ ሌጁ፡፡

ይሁንና አሁን መንግስት የገጠመውን ከፍተኛ የምግብ እጥረት ለመቋቋም የሚያስችል አዳዲስ ነጋዴ ኢንቨስተሮችን በሰፋፊ የምግብ ምርት ስራዎች ላይ ለማሳተፍ ስትራቴጂ አዘጋጅቷል፡፡ የ2014 የድርቅ እና ጎርፍ ራዕይ አካታች የእርሻ ማስተር ፕላን የምግብ ንግድ ስራዎች በሀገር በቀልና የውጭ ኢንቨስተሮች በኩል እንዲከናወን ያለመ መሆኑን ሌጁ ተናግረዋል፡፡ ይህም ጥራት ያለው የምግብ ምርት የበለጠ በጥናት የተደገፈ እንዲሆን ያካተተ ነውም ብለዋል፡፡

Pauline Wani a resident of Gumbo Rajaf.

‹‹የምግብ ደህንነትን ለማረጋጥ ሀገሪቱን በስድስት ስነ ምህድራዊ ዞኖች ከፍለናል፡፡ የናይል ኮሪደር አለን፤ ምስራቃዊ እና ምዕራባዊ ለጥ ያሉ ቦታዎች፣ ከፍታዎችና ተራራዎች፣ ከፊል ደረቃማ አካባቢዎች እና የግብርና ጥናት የሚካሔድባው ዞኖች ናቸው›› ብለዋል፡፡ 

መንግስት መሬትን ወደ የግብርና መሬቶች፤ የግጦሽ መሬቶችን ለከብት እርባታ የማዛወር፤ እንዲሁም በመላው ደቡብ ሱዳን ደኖችን የመጠበቅ ስራ እንደሚሰራ ሀላፊው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የተበላሹ የግብርና ማሽኖች መልሰው እንዲያገለግሉ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን የህዝብ መሬት ለግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና ህብረተሰብ እድሎችን የሚሰጥ የህዝብ ሀብት ቢሆንም በሀገሪቱ የመሬት ማጭበርበር በቀላሉ የሚተኮርበት እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡  

የመንግስት እቅድ ‹‹በኢንቨስተሮች በኩል ብዛት ያለው የምግብ ምርቶች እንዲመረቱ ማድረግ እስከሆነ ድረስ ኢንቨስተሮች መሬቱን እንዴት እንደያዙት ማረጋገጥ የኛ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም ከመሬት ጋር በተያያዙ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሌሎች ሀላፊዎች አሉና›› በማለትም ሀላፊው ለጁ ይናገራሉ፡፡

ግልጽ የሆነ የመሬት ህግ አለመኖር

ከመሬት ጋር በተያያዘ ብዙዎቹ ፈተናዎች የተፈጠሩት ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን በ2011 ካገኘች በኋላ ግልጽ የሆነ የመሬት ህግና ሒደቶች አለመኖራቸው እንደሆነ የደቡብ ሱዳን የመሬት ሚኒስትር መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ሞሰስ ማል ይገልጻሉ፡፡

በብዙ የመሬት ስምምነቶች መንግስት ዋና የመሬት ባለቤት የሆኑት ሰዎች በመንግስት የተረጋገጠ ህጋዊ የሆነ የመሬት ይዞታ ማስረጃ ስለሌላቸው መብታቸውን በአግባቡ ማስጠበቅ ሳይችል ቀርቷል፡፡

‹‹ከደቡብ ሱዳን ነጻነት በፊት በነበረው ህገ መንግስት መሰረት ከሆነ የመሬት ባለቤት ህዝቡ-ህብረተሰቡ ነው፡፡ የተለያዩ ስምምነቶችን ለማድረግ ሲያመሩ ያላቸውን የመሬት ድርሻ በንብረትነት ይጠቀማሉ›› ይላሉ ሞሰስ ማል፡፡ 

Dr Loro George Leju Lugor Director General Agricultural Production and Extension Servvices Transitional Government of South Sudan. 1

ከነጻነት በኋላ የደቡብ ሱዳን የመሬት ፖሊሲ ለውይይት ወደ ፓርላማ ያመራ ቢሆንም፤ እስከአሁን መደበኛ የሆነ አዲስ ህግ አልጸደቀም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቷ የምትጠቀመው ከነጻነቷ በፊት በ2009 በወጣው የመሬት ህግ ሲሆን፤ ሌሎች የሀገሪቱ ግዛቶች ደግሞ የራሳቸው የሆነ የመሬት ፖሊሲዎች፣ ህግና መመሪያዎች አሏቸው፡፡

በደቡብ ሱዳን በጥቅሉ ሶስት ቡድኖች መሬት ባለቤት ናቸው እነርሱም፤ የጎሳ ህብረተሰቦች፣ መንግስት እና በሊዝ ባለቤት የሆኑ የግል ባለሀብቶች ናቸው፡፡

የህረተሰብ የመሬት ባለቤትነት ከሁሉም የጎላ ሲሆን፤ ህረተሰቡመሬትን በባህላዊ ህጎች እንዲጠቀሙበት የሚፈቅድ ነው፡፡ በመንግስት ባለቤትነት የያዘው መሬት ደግሞ በብሔራዊ ፓርኮች፣ የተከለሉ የመጫወቻ ቦታዎች እና በደኖች ስር ህግ ነው፡፡ 

ምንም እንኳን የግል የመሬት ባለቤትነት ወይም በሊዝ የመሬት ባለቤትነት በገጠራማ ቦታዎች በብዛት ቢታይም፤ እንደ እስራኤሉ ግሪን ሆሪዞን ያሉት የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ዋና ፍላጎት የሚያሳዩት በከተሞች አካባቢ የሚገኙ መሬቶችን መያዝ ነው፡፡ እነዚህ መሬቶች በማህበረሰቡ እና በመንግስት ተቋማት የሚከራዩ ናቸው፡፡

አግባብ የሆነ የመሬት ህግ ባለመኖሩ ኢንቨስተሮች ከማይጠረጠሩ ግለሰቦችና ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ስምምነት በመፈጸም ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ይላሉ ሞሰስ ማል፡፡

የደቡብ ሱዳን የመሬት አሊያንስ ዋና ጸሐፊ ዎድካን ሴቪየር ላዛሩስ በበኩላቸው በደቡብ ሱዳን ብዙዎች ከመሬታቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ያስገደዳቸው ግጭት በ2013 እና 2016 ከተከሰተ በኋላ የመሬት ጉዳይ እጅግ ትኩረት መሳቡን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ብዙ የህግ ባለሞያዎችም ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይዘው ለመሟገት ይፈራሉ፡፡ ምክንያቱም የመሬት ውዝግቦች ውስጥ የሚገኙት በማህበረሰቡ ውስጥ በጣም ሀይል ያላቸው ሰዎች በመሆናቸው የተነሳ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የ2009 የመሬት ህግን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ተግዳሮቶች የገጠሙት ሲሆን፤ በተለይም የሰው ሀብት ማነስ እና በገንዘብ የፈረጠመ ጡንቻ አለመኖሩ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳልተቻለም ገልጸዋል፡፡

ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ ፓያም ላንድ ካውንስል፣ ዘ ካውንቲ ላንድ አውቶሪቲ፣ የመንግስት መሬት ኮሚሽን እና ብሔራዊ የመሬት ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ አካላት ሀላፊነት ወስደው ነበር፡፡ ይሁንና በተወሰኑ ግዛቶች በፓያም ላንድ ካውንስል የመሬት ባለስልጣናት የሉም፡፡ ሀላፊዎቹ ሲኖሩም ውጤታማ አይደሉም፡፡ 

‹‹ደቡብ ሱዳን አዳዲስ 32 ግዛቶች እንዲፈጠሩ ያስገደደው ቀውስ በ2016 እስኪፈጠር ድረስ 10 ግዛቶች ብቻ ነበራት፡፡ ይህም አዲስ ብዥታን አምጥቷል፡፡ ምክንያቱም ዩኒቶች ሀላፊነታቸውን ለመወጣት የሚችሉበት የሰው እና የገንዘብ ሀይል የላቸውም፡፡ ብዥታው አንዳንድ ግዛቶች ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ አስገድዷቸዋል›› በማለት ዎድካን ያስረዳሉ፡፡

የ2009 የመሬት ህግ ኩባያዎች በሊዝ የያዙትን መሬት እስከ 99 አመት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅድ ነው፡፡ ይሁንና በተመሳሳይ በ2009 የወጣው የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ህጉ የሚፈቅደው ጊዜ ደግሞ ከ30 እስከ 60 አመት ድረስ ብቻ ነው፡፡

ተጨማሪ ውዝግቦችን ለማስቀረት በአሁኑ ወቅት ሚኒስተርመስሪያ ቤታቸው አዲስ የሀገሪቱን የመሬት ህግ በማርቀቅ ላይመሆኑን ሞሰስ ማል ገልጸዋል፡፡

ይህ ሒደት ግን ለረጅም ጊዜን የሚፈጅ ነው፡፡ የሀገሪቱን የመሬት ፖሊሲ ለመቅረጽ የተዘጋጀው ሰነድ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው በ2014 በደቡብ ሱዳን የመሬት ኮሚሽን ሰብሳቢ ሮበርት ላዶ ሲሆን በቀድሞው የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻር በተመራው በሚኒስትሮች ካውንስል ስብሰባ ላይ ነበር፡፡

‹‹ፖሊሲው  የመሬት መብቶች ደህንነትን፣ እኩል ተጠቃሚነትን ጨምሮ በርካታ የመመሪያ መርሆችን ያካተተ ነበር፡፡ ፖሊሰው መሬትን የህዝብ፣ የግል እና በማህበረሰብ ባለቤትነት የተያዙ በሚል በሶስት ዘርፎች ለይቶ ያስቀመጠ ነው›› ብለዋል ሞሰስ ማል፡፡

እንደ ሞሰስ ማል አስተያየት የሀገሪቱ መንግስት ለህዝቡ መሬት ሀላፊነት አለበት፡፡ ማንኛውም መሬትን የሚፈልግ ኢንቨስተር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስምምነት ከመፈጸሙ በፊት መሬቱን የመለየትና መንግስት እንዲያውቅ የማድረግ ሒደትንመከተል ይገባዋል ብለዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የምንመለከታቸው ኢንቨስተሮች የአካባቢውን (የሀገሬውን) ህዝብ እየበዘበዙ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የመሬት ህግ ሳይኖረን በፊት የፈጸሙትን ስምምነት ነው የሚያቀርቡት›› ይላሉ፡፡ 

በብሔራዊ የመሬት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የመሬት ኤክስፐርት የሆኑት ዊሊያም ኢቤሬ እንደሚሉት አዲሱ ፖሊሲ የግለሰቦችን የመሬት ባለቤትነት አስፈላጊነትን እውቅና የሚሰጥ እና የባለቤትነት ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መሰረታዊ ነው ብለዋል፡፡

የመሬት ፖሊሲ ሰነዱ የፓርላማውን ማረጋገጫ ለማግኘት ለአምስት አመታት እንደተቀመጠ ነው፡፡ 

ይሁንና በደቡብ ሱዳን የመሬት አሊያንስ ፕሮግራም ኦፊሰር የሆኑት ሙሴምቤ ግላመርሰን እንደተናገሩት ብዙ ሰው ፖሊሲው መኖሩን አያውቅም፡፡ ስለዚህም ፖሊሲው ጸድቆ ተግባራዊ ሲሆን፤ ተገቢውን የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ረቂቁ በአሁኑ ወቅት አራተኛ ንባብ ላይ ሲሆን፤ በዚህ አመት ሊጸድቅ ይችላል ሲሉ ግላመርሰን ተናግረዋል፡፡ 

በሀገሪቱ ከመሬት ይዞታ ባለቤትነትና አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረውና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን ፖሊሲ በ2013 የደቡብ ሱዳን ካቢኔ አጽድቆታል፡፡

አዲሱ ፖሊሲ ከጦርነቱ በኋላ ከመሬት መብቶችና በከተሞች መደበኛ ባልሆኑ አሰፋፈሮች እና ከመሬት አጠቃቀም የሚፈጠሩ ግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች ላይ ማተኮርን የመረጠ ነው፡፡

የመሬት ነጠቃ እና በግዛቶችና አካባቢዎች መካከል ወሰኖች ላይ ያሉ አለመግባባቶችም በዚሁ ፖሊሲ ትኩረት አግኝተዋል፡፡

የህብረተሰብ ተቃውሞ ስምምነቶችን ሲያፈርስ

ግልጽ የሆኑ ህጎች እንዳሉ ሆኖ፤ የአካባቢ ህብረተሰብ በሀገሪቱ የመሬት ነጠቃን በመታገል ስኬታማ የሆኑባቸው የተወሰኑ ክስተቶች አሉ፡፡

በህብረተሰብ ተቃውሞ ከተሰረዙ ስምምነቶች መካከል በጣም አወዛጋቢ የመሬት ስምምነት ተብሎ በዋናነት የሚጠቀሰው በ2008 በዳላስ ቴክሳስ ድርጅት፣ በናይል ትሬዲንግ እና ልማት እንዲሁም በሙካያ ፓያም ኮፐሬቲቭ መካከል ተፈጽሞ የነበረው ነው፡፡

ይህ የ25.000 ዶላር ስምምነት 600.000 ሄክታር መሬትን ለአሜሪካው ኩባንያ ለ49 አመታት በሊዝ ባለቤት የሚያደርግ ሲሆን፣ ኩባንያው መሬቱን ለነዳጅ ቁፋሮ፣ ለእንጨትና ለግዙፍ የግብርና ስራዎች መጠቀም የሚችልበትን ሙሉ መብት የሚያጎናጽፍ ነው፡፡

ከ2008 በኋላ የሙካያ አካባቢ የህብረተሰብ አባላት ፊርማቸውን በማሰባሰብ ካምፓኒው የአካባቢውን ማህበረሰብ ሳያማክር በፕሮጀክቱ የተነሳ 600 አባወራዎች ከመኖሪያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ጠቀሱ፡፡ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኬርም ስምምነቱ እንዲሰረዝ አደረጉ፡፡

Mr Moses Maal Acting Director General Lands Ministry.

የ30 አመቷ ጀማ ኪደን የሙካያ አካባቢ የሊዝ ስምምነት ሲፈረም የ20 አመት ወጣት ነበረች፡፡ በወቅቱምየወንድ አያቷ ከአካባቢው ማህረሰብ ጋር በመሆን የመሬት ነጠቃውን በመቃወም ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ታስታውሳለች፡፡ 

‹‹ያን ግዜ የምንመለከተው ሁሉ እንግዳ የሆኑ ሰዎች በትልልቅ መኪኖች በመሬታችን ላይ ሲመላለሱ ነበር፡፡ የተወሰኑት ነጮች ሲሆኑ፤ ሌሎች ደግሞ የማናውቃቸው የደቡብ ሱዳን ዜጎች ነበሩ›› ትላለች፡፡

ስምምነቱ ሊሰረዝ የቻለው የህብረተሰቡ የተሻለ ጥቅም ሲባል ነበር፡፡

‹‹የአካባቢውን ማህረሰብ ጥቅም ከግምት ውስጥ ሳታስገባ በራስወዳድነት ለራስህ ጥቅም ስትል እንዴት የማህበረሰቡን መሬት እንዴት ነጥለህ ለሌላ ትሰጣለህ? ከመጠን ያለፈ ስግብግብነት ህዝብ ከመኖሪያው እንዲፈናቀል ምክንያት መሆኑን ማየት በጣም አሳምሞኛል›› በማለትም ኪደን ትናገራለች፡፡

ቻርለስ ዋኒ በምዕራብ ጁባ ከተማ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው ላንያ መንደር ገበሬ ናቸው፡፡ በሙካያ የመሬት ስምምነት በኋላ የመሬቱ የተወሰነ ክፍል ለሙካያ ፓያም የመሬት ስምምነት ከተወሰደ በኋላ በላንያ አዋሳኝ ክልል ለመስፈር መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ከእኛ ጋር ፈጽሞ ምክክር ተደርጎ አያውቅም፡፡ በወቅቱ እየሆነ ስለነበረው ነገር ነገር ሊያስረዳን የሚፈልግ ማንም አልነበረም፡፡ እንሰማ የነበረው ነገር ከቤተሰቦቻችን የወረስነው መሬት ተላልፎ ሊሰጥ መሆኑን ብቻ ነበር፡፡ ይበልጥ የሚያሳምመው ነገር ደግሞ መሬታችን የሚሰጠው ለውጭ ሀገር ኢንቨስተር በማይረባ ክፍያ መሆኑ ነው›› ይላሉ ዋኒ፡፡

በደቡብ ሱዳን መሬት በጣም ስሜት የሚሰጥ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ጣልቃ መግታባቸው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ አለበለዚያ ይህ ውዝግብ ወደ ከፍተኛ ግጭት እንዲቀጣጠል ያደርግ ነበር›› በማለትም ዋኒ ይናገራሉ፡፡

ተጨማሪ ዘገባ እና አርትኦት በአኒካ ማክጊኒስ

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts