በፓርኮች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል “በህዝቡ ላይ የእኔነት ስሜት ሊዳብር ይገባል” የዘርፉ ባለሙያዎች

በፓርኮች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል “በህዝቡ ላይ የእኔነት ስሜት ሊዳብር ይገባል” የዘርፉ ባለሙያዎች

በኢትዮጵያ ፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል “በህዝቡ ላይ የእኔነት ስሜት ሊሰፍን ይገባል” ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።

በተፈጥሮ ሃብቱ ላይ የሚደርሰው ማንኛውም አደጋ በማህበረሰቡ ህይወት ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እንዳለው በመገንዘብም ሁሉም አካል ለብርቅዬ እንስሳቶቹና ለእጽዋቱም አስፈላጊውን ከለላና ጥበቃ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ በአገሪቷ በሚገኙ የተለያዩ ፓርኮች ላይ አደጋ እየደረሰ ይገኛል።

ለአብነትም በባሌ ብሔራዊ ፓርክ እና በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ በብዝሃ ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

የእሳት አደጋ ምንም እንኳን በብዙ ፓርኮች ላይ ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ90 በመቶ በላይ የጥብቅ ደኖች ቃጠሎ የሚደርሰው በሰው ሰራሽ ምክንያት ነው።

ኢትዮጲያ በበርካታ እንስሳትና እጽዋት ሀብቷ የብዝሃ ህይወት ባለቤትነት በአፍሪካ ከታንዛንያና ከዩጋንዳ ቀጥላ ስሟ ይጠቀሳል።

በዚህም በፓርኮች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች በፓርኩና በእንስሳቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማህበረሰብም የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የዴንና ግጦሽ መሬት የዘረመል ባለሙያ አቶ ሃይሉ አጥናፉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢኒስቲትዩት የለማዳ እንስሳት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አበበ ሃይሉ በበኩላቸው በፓርኮች ውሰጥ የሚኖሩ የአብዛኞቹ እንስሳት ህልውና በእጽዋት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ይገልጻሉ።

በዚህም በተለይ በቅርቡ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የተጎዳው አካባቢ እስኪቋቋም ድረስ ለእንስሳቱ አስፈላጊው ጥበቃ መደረግ እንዳለበትም ነው የሚገልጹት።

በመሆኑም በፓርኮች ህልውና ላይ አደጋ እንዳይጋረጥ በተለይ ህብረተሰቡ የእኔነት ስሜት እንዲሰማውና በአግባቡ እንዲጠብቀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት መሰራት አለባቸውም ብለዋል።

በደንና ግጦሽ መሬት ብዝሃ ህይወት ዳይሬክቶሬት የዘረመል ባለሙያ አቶ ሃይሉ አጥናፉ እንደሚሉትም ህዝቡ ፓርኮችን ባለቤት ሆኖ እነዲጠብቃቸው ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው።

በኢትዮያ ብዝሃ ህይወት ኢኒስቲትዩት የለማዳ እንስሳት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አበበ ሃይሉ እንደሚሉት ሳሮች እንዲያገግሙ መሰራት እንደሚገባ ጠቅሰው በተለይ የአካባቢው ህዝብ ህይወቱ የተመረሰተው በፓርኩ ላይ በመሆኑ ግንዛቤ መስጠት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 23 የሚሆኑ ብሄራዊ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም የአዋሽ፣ የሰሜን ተራሮች፣ የባሌተራሮች፣ ኦሞ እና የነጭሳር ፓርኮች ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ዋልያ አይቤክስን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ብርቅዬ የዱር አራዊቶችና አእዋፋትም በተለያዩ ፓርኮች ተጠልለው ይገኛሉ።

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts