ከመሬት መውሰዱ ባሻገር: ግድቦችና ሀይቆች የውሀ እጥረትን ያባብሳሉ

ከመሬት መውሰዱ ባሻገር: ግድቦችና ሀይቆች የውሀ እጥረትን ያባብሳሉ

ካስዋ በሙዚዚ ወንዝ በኩል በካጋዲ እና ክዬንጆጆ ዲስትሪክት ድንበር መካከል በምዕራብ ካምፓላ የምትገኝ አነስተኛ መንደር ናት፡፡ እስከ 17 ሄክታር የሚሆነው የዚህች መንደር አካባቢ በቀጣዮቹ ሶስት አመታት የሀይል ማመንጫ ግድብ ይሆናል፡፡
በመንደሩ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎችም የዩጋንዳ መንግስት ፕሮጀክት በሆነው በሙዚዚ የሀይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት አማካኝነት ከሚፈናቀሉ 829 ሰዎች መካከል ናቸው፡፡
‹‹በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 473 ሄክታር መሬት ይፈልጋል›› የሚሉት በዩጋንዳ የኤሌትሪክሲቲ ጄኔሬሽን ኩባንያ የክትትልና ምዘና ባለሞያ የሆኑት ቪንሴንት ኪሴምቦ ናቸው፡፡ ከአካባቢው የሚፈናቀሉ ሰዎችም ‹‹ተገቢውን የካሳ ክፍያ›› ያገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የካጋዲ ዲስትሪክት የፓርላማ አባል የሆኑት ጄኒፈር ምባባዚ ግን ከአካባቢው የሚነሱ ሰዎች የካሳ ክፍያቸው የተተመነው በቀደሙት አመታት በመሆኑ በቀጣይ ህይወታቸው ‹‹ለከፋ ጉዳት ይጋለጣሉ›› ብለዋል፡፡
‹‹የአካባቢው ነዋሪዎች የካሳ ክፍያ ተመኑን በግዳጅ እንዲፈርሙ ነው የተደረጉት፡፡ ንብረታቸው ከሚገባው መጠን በታች የተተመነ በመሆኑ በድጋሚ በሚሰፍሩበት አካባቢ አዲስ መሬት ለማግኘት አይችሉም›› ይላሉ የፓርላማ ተመራጭዋ ምባባዚ፡፡
ከግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው የመሬት ባለቤትነት ውዝግብ ለሙዚዚ የሀይል ማመንጫ ግድብ አዲስ አይደለም፡፡ በአለም ላይም አንደኛው ጸብ ፈጣሪ ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከ20.000 በላይ ነዋሪዎችን ያፈናቀለ ሲሆን፤ በላይኛው አትባራ ወንዝ ላይ የተገነባውና በ2017 በሱዳን መንግስት የተመረቀው የአትባራ እና እና ሰቲት ግድብ ፕሮጀክት እስከ 30.000 ሰዎችን አፈናቅሏል፡፡ በዩጋንዳ ደግሞ በናይል ወንዝ ለሚገነባው ለካሩማ የሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ በአኩሩዲያ፣ ካሩም፣ ኣዎ እና ኖራ መንደሮች የሚኖሩ 300 ያህል ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
የውሃ አጠቃቀም እና አቅርቦት በአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ዘንድ ከመሬት ጋር የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ ግዙፍ የሆኑ ግድቦች እና ሰው ሰራሽ የውሀ ሀይቆች የነዋሪዎችን የመሬት ይዞታ ከማጥፋት ባሻገር፤ በግጭት የሚሰደዱ ሰዎችን ቁጥር በፍጥነት እንዲጨምር እና ተፈናቃዮች በሚሰፍሩበት ማህበረሰብ ዘንድም የመሬት ጫና እንዲፈጠር ምክንያት ናቸው፡፡
ምንም እንኳን የውሃ ግድቦች እና ሰው ሰራሽ የውሀ ሀይቆች ከፍተኛ የሆነ ታዳሽ ሀይልን የሚያመነጩ፣ ለእርሻም ሆነ ለኢንዱስትሪ የሚጠቅሙ ውሃን የሚሰጡ፣ የወንዝን ፍሳሽና ጎርፍን የሚቆጣጠሩ ቢሆኑም፤ በተመራማሪዎች ይፋ የሆነ አዲስ ጥናት እንደሚያመለክተው ለድርቅና የውሃ እጥረት መከሰትም አሉታዊ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ በኔቸር ሰስቴኔብቲ ይፋ የሆነው ይኽ ጥናት በስዊድን አፕሳላ ዩኒቨርስ በአርዝ ሳይንስ ዲፓርትመንት በፕሮፌሰር ጂዩሊያኖ ዲ ባልዳሳሬ አስተባባሪነት ከስምንት ሀገሮች የተውጣጡ አስር ባለሞያዎች በመተባበር የሰሩት የሶስት አመት የምርምር ውጤት ነው፡፡
በዚህ ቃለ መጠይቅ በ2017 ከእንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ቤኔዲክት ሞራን ጋር በመሆን በኦሞ ወንዝ የተሰራው ግልገል ግቤ 3 ሀይል ማመንጫ ግድብ በኢትዮጵያ ሀይቁን እና በኬንያ ከ2000 በታች የህዝብ ብዛት ያላቸውና በጣና ሀይቅ ላይ ኑሯቸውን የመሰረቱትን የኤል ሞሎ ህዝቦችን ምን ያህል እንደጎዳ በኒው ቪዥን ኦንይን ላይ በስፋት የሰራው ፍሬድሪክ ሙጌራ አዲሱን ጥናት በተመለከተ ፕሮፌሰር ጂሊያኖን አናግሯቸዋል፡፡
ፍሬድሪክ፡ የውሃ እጥረትንና ድርቅን ይከላከላሉ የሚባሉት ግድቦችና ሀይቆች እንዴት ነው አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉት?

ፕሮፌ. ጁሊያኖ፡ ሰው ሰራሽ ሀይቆችን ከማስፋፋት ጋር በተያያዘ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ነው የምንሟገተው፡፡ እነርሱም የአቅርቦት- ፍላጎት ሒደት እና የሀይቆቹ ተጽዕኖ ናቸው፡፡ የውሀ አቅርቦት- ፍላጎት ሒደት የውሀ አቅርቦትን መጨመር ከፍተኛ የፍላጎት መጨመርን የሚፈጥር መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ሰው ሰራሽ ሀይቆች ውጤት ስንል ደግሞ በሀይቆች ላይ ከመጠን ያለፈ ጥገኛ መሆን ተጋላጭነትን ከመጨመር ጋር ያሉ ነገሮችን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በድርቅ ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን ያባብሳል፡፡ የድርቅ ውጤቶችን እና የውሀ እጥረትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሀይቆች ይበልጥ ችግሮቹን አባባሽ ሊሆኑ ይችላሉ የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
ፍድሪክ፡ በአፍሪካ ጥናቱ ለመስራት መነሳሳት የፈጠሩላቹ ግድቦችና ሀይቆች የትኞቹ ናቸው?
ፕሮፌ ጂሊያኖ፡ በጥናት ወረቀታችን ላይ በመገንባት ላይ ካሉ አዳዲስ ግድቦች መካከል አንዱ ምሳሌ ሆኖ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እና በግሎባል ሳውዝ የሚገነቡት ሀይቆች ናቸው፡፡
ፍድሪክ፡ 90 ከመቶ የኤሌትሪክ ሀይል ማመንጫ በሆነው በአባይ ወንዝ ላይ በርካታ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በእቅድና በመገንባት ላይም ናቸው፡፡ ታዲያ እንደ ግድቦችና ሀይቆች ያሉ ትልልቅ የውሃ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥገኛ መሆን እንደማይገባ መናገር ይቻላል?
ፕሮፌ. ጁሊያኖ፤ እያንዳንዱ ጉዳይ የተለያየ በመሆኑ እንደዚያ ብለን ማጠቃለል አንችልም፡፡ ሀይቆች ሁልጊዜ መጥፎ ናቸው? አይ! አይደሉም! ከውሃ እጥረትና ድርቆች ጋር ተያያዘ ምዘና ሲካሔድ የተለያዩ አማራጮች በሚጠቀሱበት ጊዜ ከውሀ እጥረት ጋር በተያያዘ ፈጽሞ ያልተጠበቁ ውጤቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ እንዲታወቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ አማራጭ ለተለያዩ ማህበራዊ ቡድኖች የተወሰነ ማህበራዊ፣ አካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳለው ሁሉ፤ የራሱ የሆነ ማህበራዊ፣ አካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ወጪዎችም አሉት፡፡ በሀሳባዊው አለም እነዚህ ሁሉ ነገሮች በሁለቱም ባለድርሻ አካላት ዘንድ በግልጽ እና በዲሞክራሲያዊ ሒደት በጥንቃቄ መታየት አለባቸው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ያሉ ባለሞያዎችም እንዲሁ በከፍተኛ ሁኔታ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው፡፡
ፍሬድሪክ፡ ጥናችሁ ዩናይትድስቴትስን በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ ታዲያ በአፍሪካ ስላለው ሁኔታ እንዴት ተቀባይነት ይኖረዋል?
ፕሮፌ. ጁሊያኖ፡ በአለምአቀፍም ሆነ በሀገርአቀፍ ደረጃ ያሉት ሁለቱንም የጥናት ማህደሮች ነው የተነተንነው፡፡ ጥቅል የሆኑ መረጃዎችንም አብራርተናል፡፡ በእርግጥ ጥናታችንን ለማድረግ ያነሳሳን ‹‹እያደገ ያለውን የውሀ ፍላጎት ለማሟላት የውሀ አቅርቦትን መጨመር አለብን›› በሚለው ልማዳዊ አስተሳሰብ ላይ በመመስረት በተገነቡት በአፍሪካ ብዙ ግድቦችና ሀይቆች ነው፡፡
ፍሬድሪክ፡ ከጥናት ውጤታችሁ በመነሳት በመደበኛነት ጎርፍ እና የውሀ እጥረት የሚከሰትባቸው የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች መንግስታት በሚገነቧቸው ግድቦች የተነሳ ችግሮች እንዳይባባሱ ምን ማድረግ አለባቸው?
ፕሮፌ. ጁሊያኖ፡ ከውሀ ጋር በተያያዘ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ከሚያደርጉት ተሳትፎ በተጨማሪ በከፍኛ ሁኔታ በመሰረተ ልማት ላይ ጥገኛነትን ማስቀረት እና ቀላል የሆኑ እርምጃዎች ላይ ይበልጥ መስራት ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ የጎርፍ አደጋ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አሰራርን እና አነስተኛ ውሀ የሚጠይቁ የእርሻ ስራዎችን ማካተት ይችላሉ፡፡
ይህ የዘገባ ፕሮጀክት የተሳካው በፑልቲዘር ሴንተር ከፍተኛ ድጋፍ አማካኝነት ነው፡፡

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts