በቆንጂት ተሾመ (አዲስ አበባ)
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ቁልፍ ሰው ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞተው ተገኝተዋል፡፡ ላለፉት ሰባት አመታት ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን ያገለገሉት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል፡፡ ኢንጂነሩ የግድቡ ግንባን በተመለከተ ወቅታዊ መግለጫ ለጋዜጠኞች ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል በሰጠው መግለጫ ኢንጂነሩ በጥይት መሞታቸውን በማስታወቅ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሔደ ነው ብሏል፡፡ ድርጊቱ ያስቆጣቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡ መንግስት የምርመራውን ውጤት እንዲያሳውቅም ጠይቀዋል፡፡
በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በኢንጂነሩ ሞት ሀዘናቸውን በመግለጽ ከግድያው ጀርባ ያለውን አካል መንግስት አጣርቶ እንዲያሳውቅና ፍትህ እንዲሰጥ አጥብቀው አሳስበዋል፡፡
በአፍሪካ ግዙፍ የኤሌትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በስራ አስኪያጅነት የመምራት ሀላፊነትን ከተሸከሙት ከኢንጂነር ስመኘው በቀለ ግድያ ጀርባ ያለው ምክንያት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ግድቡን ግንባታ አጠቃላይ እውነታ በተመለከተ እንደ እርሳቸው ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሞያ ባለመኖሩ የእርሳቸው ህልፈተ ህይወት በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚችልም ስጋት ፈጥሯል፡፡