በህንድ ኒውዴልሂ በሳይንስና አካባቢ ማዕከል አማካኝነት የተካሔደ ጥናት እንዳመለከተው አፍሪካውያን ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቧቸው 90 ከመቶ ያህሉ ተሽከርካሪዎች አሮጌና ያገለገሉ በመሆናቸው ለአካባቢያዊ ብክለት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
ማዕከሉ እንዳስታወቀው ተሸከርካሪዎቹ መርዛማ በካዮችን ስለሚለቁ የአየር ንብረት ለውጥን የሚያባብሱ ናቸው፡፡ የጤና እና የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ለመቀነስ ቁጥጥር የለሹን የአሮጌ መኪኖች አወጋገድን ለማስቆም አለምአቀፋዊ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ማዕከሉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ማዕከሉ የጥናቱን ዝርዝር ጉዳዮች ባስታወቀበት መግለጫው ላይ ‹‹ወደ አፍሪካ ከሚገቡ ተሸከርካሪዎች ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት አሮጌ እና ያገለገሉ ናቸው፡፡ ከመኪኖቹ የሚለቀቁት መርዛማ ብካዮች፣ ሙቀት አማቂ የግሪን ሀውስ ጋዞች እና ጥቁር ካርቦን በሰዎች ጤና ላይ እና በአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን የከፋ ያደርጉታል›› ብሏል፡፡