እምቦጭ የውሃ አካላት ስጋት

እምቦጭ የውሃ አካላት ስጋት

 

እምቦጭ አረምን በንቃትና በጋራ መከላከል ካልተቻለ በአገሪቷ ባሉ የውሃ አካላት በመዛመት በህልውናቸው ላይ ስጋት ሊሆን እንደሚችል የአማራ ክልል አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን አስታወቀ።

አረሙ በጣና ኃይቅ ከተከሰተ በኋላ በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቷ ክልሎች እየተዛመተ መሆኑም ነው የተጠቀሰው።

የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ለኢዜአ እንደተናገሩት የእንቦጭ አረም በዘሩ አማካኝነት በስፋትና በፍጥነት የመራባት ጠባይ ስላለው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች አረሙ ወዳልታየባቸው አካባቢዎች የመዛመት እድሉ ከፍተኛ ነው።

አረሙ በአሳ ማጥመጃ መረቦች አማካኝነት ይዛመታል የሚለው ትልቁ የስጋት ግምት ሲሆን፣ በሰዎች አማካኝነትም ከቦታ ቦታ ሊዛወር እንደሚችል ጠቁመዋል።

የዛሬ ሰባት አመት በጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተው ይህ አረም አሁን ላይ ከጣና አልፎ በደቡብ ክልል አባያ ኃይቅና በጋምቤላ ባሮ ወንዝ ላይ መታየቱ አረሙ በሌሎችም ሊዛመት እንደሚችል ማሳያ ነው ብለዋል።

የውሃ አካላትን ከመሰል ችግሮች በርብርብ ማዳን ካልተቻለም ችግሩ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይም ስጋት ሊሆን እንደሚችል አበክረው አሳውቀዋል።

በመሆኑም የውሃ አካላትን ከዚህና መሰል አደጋዎች ለመታደግ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

አሁን ባለው ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞም መሰል በርካታ መጤ አረሞች ሊከሰቱ ይችላሉም ነው ያሉት።

ይህንን ችግር ቀድሞ ለመከላከልና ተከስቶ ሲገኝም መቆጣጠር የሚችል ተቋም በፌዴራል ደረጃ መቋቋም እንዳለበት ይመክራሉ።

አሁን ላይ ከጣና ኃይቅ አረሙን ለማጥፋት በአገር ውስጥ ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በኩል ያልተቋረጠ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል ዶክተር በላይነህ።

በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ ተከታታይ የሆኑ ምርምሮች በክልሉ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰሩ እንዳሉም ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎቹ ምክረ ሃሳብ በማቅረብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው ብለዋል።

ቀድሞ ያን ያህል የነበረው የፌዴራል መንግስት ድጋፍም አሁን ላይ የተጠናከረ እንደሆነም አሳውቀዋል።

የእምቦጭ አረም በቶሎ ማጥፋት ካልተቻለ የውሃ አካላት ላይ በመንሰራፋት ለድርቀት እንደሚዳርግና በውሃ ውስጥ ያሉ ህይወት ያላቸው ዝርያዎችን በማጥፋት በኢኮኖሚና በአካባቢ ስነ ምህዳር ላይ ጉዳት እንደሚያደርስም ታውቋል።

 

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts