የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ታገደ

የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ታገደ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ከዛሬ ጀምሮ መታገዱን የኢፌዴሪ የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን ሚድሮክ ጎልድ በለገደምቢ በሚያካሂደው የወርቅ ማዕድን ልማት ስራ ላይ የአካባቢው ነዋሪ፥ የኩባንያው የምርት ሂደት የአካባቢ ብክለት እያስከተለ ነው የሚል ቅሬታ ማንሳቱን ተከትሎ ነው ፍቃዱን ያገደው።

በገለልተኛ አካል ጥልቀት ያለው ጥናት እስከሚጠና ድረስ የኩባንያው ወርቅ የማምረት ስራው መታገዱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ጥናቱ በገለልተኛ አካል ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮችን እና ባለ ድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እንደሚካሄድ፥ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ባጫ ፋጂ ተናግረዋል።

የኩባንያው ወርቅ የማምረት ሂደት መቀጠል ያለመቀጠል ሂደትም በጥናቱ ውጤት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አዲስ ጥናት ሲሰራም የጥናቱ ወሰን ከዚህ በፊት ከተደረገው እንዲሰፋ እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ የሚወሰዱ ናሙናዎች ቁጥርም ከፍ ይደረጋል ብለዋል።

የነበረው አዋጅ የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ እድሳት እንዲደረግ እንደሚፈቅድ ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ የኩባንያው የወርቅ አመራረት ሂደት በአካባቢው ችግር እየፈጠረ መሆኑን ሚኒስቴሩ እንዳመነበት አንስተዋል።

ይህን ተከትሎም የኩባንያው የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ከዛሬ ጀምሮ መታገዱን አስረድተዋል።

አሁን የተወሰደው እርምጃም ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

ከሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ጋር በተያያዘ በገለልተኛ አካል የሚደረገው የጥናት ሂደትም ዛሬ ተጀምሯል።

የጥናቱ አጠቃላይ ውጤት ምን ያክል ጊዜ እንደሚወስድና መቸ እንደሚጠናቀቅ ግን የተባለ ነገር የለም።

Like this article?

Share on Facebook
Share on Twitter
Share on Linkedin
Share on Pinterest
Share on Telegram
Share on WhatsApp

Leave a comment

Related Posts