በሚያዝያ ወር በተደረገ ጥናት በሶማሌ ክልል በሸበሌ ዞን 165 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎች በጎርፍ መጠቃታቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ 98 ሺሕ ያህል ሰዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በዚህ ሳምንት በወጣው ሳምንታዊ ሪፖርት፣ በክልሉ በተከሰተው ጎርፍ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ አምስት ሺሕ ቤቶች መውደማቸውን፣ በሸበሌ ዞን የሚገኙ 72 ትምህርት ቤቶችና 63 የጤና ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡
በደረሰው አደጋም የተለያዩ መጠን ያላቸው የሕክምና መድኃኒቶችና መገልገያዎች አብረው መውደማቸውን ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ቀላፎና ሙስቲሂል በተባሉ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ 14 ሺሕ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከሌሎች የዞኑ አካባቢዎች ጋር የሚያገናኛቸው የየብስ ትራንስፖርት በጎርፍ ምክንያት ተቋርጧል፡፡
በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል በዶሎ ኦዶ ከተማና በሊበን ዞን የሚገኙ 26 ሺሕ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት መፈናቀላቸው በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ የጎርፍ አደጋ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በባሌ፣ በቦረና፣ በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ፣ እንዲሁም በጉጂ ዞኖች መከሰቱን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ከአደጋው ጋር በተያያዘ በተሠራው ጥናት መሠረት በሸበሌ ዞን ብቻ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመደገፍ አምስት ሚሊዮን ዶላር በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ፣ ይህም በተለይ ንፁህ ውኃ ለማቅረብ፣ እንዲሁም በጎርፉ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል እንደሚውል ተገልጿል፡፡
በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ የሚመራ የልዑካን ቡድን፣ በጎርፉ የተጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተዟዙሮ መጎብኘቱ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡