ጆርጅ ኦንያንጎ በኬንያ ምዕራብ ናይሮቢ በኪሱሙ ግዛት በቪክቶሪያ ሀይቅ ዱንጋ ወደብ ላይ በአሳ እርባታ ነው የሚተዳደረው፡፡ በአሳ እርባታ ስራ ከአስራ አምስት አመታት በላይ ሰርቷል፡፡ የ56 አመቱ ኦንያንጎ የሰባት ልጆች አባት ሲሆን፤ እንደ አሁኑ ባይሆንም ጥሩ ገቢ ያገኝ ነበር፡፡

‹‹አሳ በማጥመድ ጥሩ ገቢ አገኝ ነበር፡፡ አሳዎች በብዛት ስለነበሩ በቀን ውስጥ እስከ 200 ዶላር እሰራ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ አሁን በሀይቁ ውስጥ አሳ ማግኘት ስለመቻሌ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲ የአሳዎች መጠን እየቀነሰ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እኛ ለአሳ አጥማጆችን በጣም አሳስቦናል፡፡ ኑሯችንን የምንደጉምበት ሌላ ነገር የለንም›› በማለት ኦንያንጎ ይናገራል፡፡

በቪክቶሪያ ሀይቅ የተከሰተው ውሀ መጣጭ አረም (በኢትዮጵያ እምቦጭ ተብሎ የሚታወቀው) ለኦንያንጎ ከባድ ራስ ምታት ሆኖበታል፡፡

ሀይቁ ዙሪያውን የሚኖሩ ሰዎች ለግብርና ስራዎች፣ ለቤት ውስጥ የውሀ አግልግሎት፣ ለሀይድሮፓወር፣ ለአሳ እርባታ እና ቱሪዝም ለመሳሰሉት ተግባሮች ጥቅም በመስጠቱ ርዷል፡፡ አሁን ላይ ግን በአሳዛኝ ሁኔታ ደርቋል፡፡

‹‹አሳ እርባታ የምተዳደርበት ብቸኛው ሙያዬ ነው፡፡ ሙያውን የወረስኩት ከዚህ በፊት በጣም ጎበዝ አሳ አርቢ ከሆነው ከወላጅ አባቴ ነው፡፡ ድሮ ድሮ በሀይቁ ውስጥ ብዙ አሳዎች ነበሩ፤ ውሀውን የሚያደርቀው አረምም አልነበረም›› ሲል ኦንያንጎ አሁን ላይ ነገሮች እንዴት እንደተቀየሩ ያስረዳል፡

ኦንየንጎ አንዳችም አሳ ሳያገኝ የሚመለስበት ጊዜም አለ፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት እንዲህ እንደአሁኑ አረም ሀይቁን ሳይሸፍነው ግን ምንም አይነት ችግር ተሰምቶ አያውቅም ነበር፡፡

አረም የሀይቆችን ኤኮሲስተም እንዲራቆት አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱት መካከል አንደኛው ሆኖ ይጠቅሳል፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ ብክለት፣ ዘላቂ ያልሆነ የአሳ እርባታ እና የአየር ንብረት ለውጥ ናቸው፡፡