አዲስ አባባ፣ ግንቦት19፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሲዳማ እና በምእራብ አርሲ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ23 ሰዎች ህይወት አለፈ።

አደጋው የተከሰተው ትላንት ምሽት ሁለት ሰአት ጀምሮ ለረጅም ሰዓት ከባድ ዝናብ በመጣሉ መሆኑ ተገልጿል።

ከሟቾቹ መካከል 16ቱ ሴቶች ሲሆኑ፥ በሌሎች ስድስት ሰዎች ላይም የአካል ጉዳት እንደደረሰና የህክምና እረዳታ እየተደረገላቸው መሆኑም ታውቋል።

በአደጋው በግምት ስድስት ሄክታር መሬት ላይ የመሬት መንሸራተቱ የተከሰተ ሲሆን፥ ከ30 በላይ የቤት እንስሳትም መሞታቸው ነው የተገለጸው።

የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝም እና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ አቶ ጀጎ አገኝሁ እንደተናገሩት የዞን አመራሮች አደጋዉ በተከሰተባቸዉ የጭሬ እና የናንስቦ ወረዳዎች የአደጋዉን ሁኔታ ለማየት እና ድጋፍ ለማድረግ ዛሬ ጥዋት ወደ ስፍራዉ አቅንተዋል።